*/

*/

Source

በብዙ የአፍሪካ አገሮች እንዳየነው መሪዎች የወታደሩን ድጋፍ ለማግኘት የሚሞከሩት ብዙውን ጊዜ አዛዦችን በጥቅም በመያዝ ነው። በጥቅም የተያዘ ጄኔራል ደግሞ ከሳሎን ቤት ውሻ ተለይቶ አይታይም። የሳሎን ቤት ውሻ በጌታው ላይ መጮህ የሚጀምረው፣ እንክብካቤ የቀነሰበት ወይም እየተገለለ የመጣ ከመሰለው ነው። በግብጽ በሆስኒ ሙባረክ ላይ የተነሱት ጄኔራሎች፣ በሳሎን ቤት ያደጉ ቅምጥሎች ነበሩ።

መለስ ዜናዊ ደግሞ ታማኝነትን ለማግኘት ይሞክር የነበረው፣ ጄኔራሎቹ በሙስና እንዲዘፈቁ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወይም አይቶ እንዳላየ በማለፍ ነበር። ጄኔራሎቹ ታማኝነታቸው የጎደለ ወይም የሚያፈነግጡ ከመሰለው፣ የሙስና ፋይላቸውን ከፍቶ ያስደነግጣቸው ነበር። በሙስና የተዘፈቀ ጄኔራል ማደንዘዣ የተወጋ አንበሳ ማለት ነው። አይጥም ይሁን ድንቢጥ እንደልቡ ቢጫወትበት ንቅንቅ አይልም። ስዬ አብርሃና ታምራት ላይኔ የዚህ ዘዴ ሰለባዎች ነበሩ።

አብይ አህመድ እንዲህ አይነቱን መንገድ አለመከተሉ ሊያስመሰግነው ይገባል። መቀሌ ላይ ለጄኔራሎቹ ባደረገው ንግግር፦“ ይህ ሰራዊት የብልጽግና ሰራዊት አይደለም፤ የአብይ ሰራዊት አይደለም፤ እኛ ከእናንተ የምንፈልገው ጠንካራና ፕሮፌሽናል አርሚ እንድትሆኑ እንጅ ለአንድ ፓርቲ የምትገዙ እንድትሆኑ አይደለም። ኢትዮጵያ ከብልጽግና በላይ ናት። ከፓርቲ በላይ ናት።" ብሏል። አብይን የማቃወም ጄኔራል ቢኖር እንኳን፣ ይህን በሞራልም ሆነ በመርህ ደረጃ ትክክል የሆነን ንግግር ሊቃወም አይችልም። አንድ ጄኔራል ታማኝነቱ ለአገሩ ብቻ ካደረገ፣ የማንም መሪ ወይም የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የሳሎን ቤት ውሻ ሊሆን አይችልም። ክብርንና ሙያን አዋርዶ የሳሎን ቤት ውሻ የሚያደርገው ደግሞ ሙስና ነው። ከሙስና የጸዳ ጄኔራል፣ ራሱንና ሙያውን ብቻ ሳይሆን፣ አገሩንም በጽናት ያሰከብራል።

አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ፣ ጠንካራ ሰራዊት ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ የህግና የአስተዳደር መሻሻሎችን ወይም የፖለቲካ ለውጥ ማድረግም ያስፈልጋል ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከዚህ በላይ ምቹ ጊዜ ያለ አይመስለኝም። በብዙ አገሮች ወሳኝ የሚባሉ የህግና የአስተዳደር ለውጦች የተደረጉት፣ መሪዎች ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ባገኙበት ወቅት ነበር። በአሜሪካ ባርነትን ያስቀሩት 13ኛና 14ኛ ድንጋጌዎች የወጡት፣ የእርስበርስ ጦርነቱ በተጠናቀቀ ማግስት ነበር። በኢትዮጵያ በብሄር ፖለቲካ፣ በህገመንግስት፣ በልዩ ሃይል እና በመሳሰሉት ከፋፋይ እና አደገኛ ህጎችና አስተሳሰቦች ላይ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ከዚህ በላይ አመቺ ጊዜ የሚኖር አይመስለኝም።

"በትርምስ መሃል ጠንካራ መሪ ይወለዳል" እንዲል ማኪያቬሊ፣ በዚህ ትርምስ መሃል፣ አብይን ጨምሮ፣ ብዙ ጠንካራ መሪዎች ተወልደዋል። እነዚህ መሪዎች በጦሩ ሜዳ ላይ ያገኙትን ድል በፖለቲካው ሜዳ ላይ ደግመው እንዲያሳዩን፣ ከምኞት ባሻገር፣ በሰለጠነ መንገድ ግፊት ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ።

ፋሲል የኔዓለም (የኢሳት ማኔጂንግ ኤዲተር)

Report Page