*/

*/

Source

የማይካድራውን ጭፍጨፋ በማስተባበር የተጠረጠረች ወታደር እና የጦር መሳሪያዎችን ለህወሓት በማቅረብ የተጠረጠረ ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀረቡ
*********************** (ኢ ፕ ድ)

“በማይካድራ በግፍ የተጨፈጨፉ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው ተገቢ ነው” በማለት ስታስተባበር ነበረች የተባለችው ወታደር እና ከውጭ አገር ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎችን ለቡድኑ ሲያቀርብ ነበር የተባለ ነጋዴ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ አባል ታጎስ ገብረትንሳኤ በተባለችው ተጠርጣሪ ላይ በተሰራ የምርመራ ስራ ተጠርጣሪዋ በወቅቱ ‘በማይካድራ በቦታው ሆና በግፍ የተገደሉ ንጹሃን ዜጎች መገደል ተገቢ ነው’ በማለት ሌሎችም እንዲገደሉ በአካባቢው በየወረዳዎቹ እየዞረች ስታስተባብር እንደነበር አረጋግጫለሁ ብሏል።

ቃል የመቀበል ስራ መስራቱን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ግለሰቧ የተለዋወጠችውን መልዕክት ሞባይሏ እንዲመረመር ለሚመለከተው አካል መላኩንም ገልጿል።
በማይካደራ የተጨፈጨፉ ዜጎችን አስከሬን እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን የመለየት ስራ እየሰራ መሆኑን በመጥቀስም ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዋ ምንም ዓይነት ልብስ ይዤ አልመጣሁም በማለት ለፍርድ ቤቱ የገለጸች ሲሆን፥ ልብሷ የት እንዳለ ለቀረበላት ጥያቄም ተጠርጣሪዋ ማይካድራ ነው ያለው ስትል ምላሽ ሰጥታለች።

ችሎቱም መርማሪ ፖሊስ እያከናወነ ካለው ሰፊ ምርመራ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገዋል ሲል 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶለታል።

በዚሁ ችሎት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለህወሓት የጸረ ሰላም ቡድን በማቅረብ የተጠረጠረው ጀማል አደም እና ዓለም ደስታ ሃየሎም የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ዛሬ ቀርበዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ባለሙያ ተጠርጣሪዎቹ ሁለቱም ነጋዴዎች ሲሆኑ ከህወሓት የጸረ-ሰላም ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና በተለይም ከዶክተር አዲስ ዓለም ጋር በመሆን ሲሰሩ ነበር ብሏል።

በተለይም ጀማል የተባለው ተጠርጣሪ በርካታ ግዢ የሚያቀርብ ሲሆን ለቡድኑ በርካታ የጦር መሳሪያ ሊያደርሱ ሲሉ መያዛቸውንም መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

1ኛ ተጠርጣሪ ዓለም ደስታ እኔ ነጋዴ ነኝ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የለኝም ብለዋል፤ 2ኛ ተጠርጣሪ ጀማል አደም እኔ የተያዝኩት ወደ ዱባይ ለመጓዝ በተዘጋጀሁበት ወቅት አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ነው በሚል ምንም አላውቅም ሲሉ ገልጸዋል።
መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ከህወሓት ጸረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በምስጢር በመገናኘት ሲሰሩ ነበር ሲል ጠቅሷል።

ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምደብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለመርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን ፈቅዶለታል ሲል የኤፍቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

Report Page