*/

*/

Source

« ንጉሡ ውበታችሁን ወ’ዷልና ልጆቼ ስሙ ወገኖቻችሁንና የአባታችሁን ቤት (እ)ርሱ»
━━━━━━━✦༒⛪༒✦━━━━━━━

እስመ ንጉሥ ፈተወ ስነክሙ ስምኡ ውሉድየ ወአጽምዑ እዝነክሙ ርስኡ ሕዝበክሙ ወቤተ አቡክሙ

━━━━━━━✦༒⛪༒✦━━━━━━━

ቀኑ «በዓታ ለማርያም» ይሰኛል። የአብ መርዓት፣ የወልድ ወላዲት፣ የመንፈስ ቅዱስ ጽርሐ ቤት ፣ እመ እግዚአብሔር ጸባት፣ የቅድስት ሥላሴ ታቦት… ድንግሊቱ ብላቴና ቅድስት ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባቷን የምንዘክርበት የከበረ ቀን ነው።

በእርግጥ እንደ ቤተክርስቲያናችን መጽሐፈ ግጻዌ (Book of Exposition) በዓታ የሚባለው ስለ ሁለት ምክንያቶች በዓመት ሁለት ጊዜ ይታሰባል።

(ዛሬ) ታህሣሥ ፫ ቀን የሚታሰበው ነው።

ከንጹሐኑ ቤተሰብ ከቅድስት ሐና እና ከቅዱስ ኢያቄም ንጽሕት ድንግል ማርያም ግንቦት ፩ ተወልዳ «ንጽሕት እምንጹሐን» ስትሰኝ ሦስት ዓመት በእናት አባቷ ቤት ቆይታ «ቅድሳት ለቅዱሳን» እንዲል ለመቅደስ የምትገባው ቅድስቲቱ ድንግል ወደ መቅደሰ ኦሪት ገብታ ቡሩክ የሆነ አረጋዊው ጻድቅ ዮሴፍ «ቡሩክ ዘነስአ እመቅደስ» ተሰኝቶ እስኪወስዳት በንጽሕና በቅድስና መኖሯን የምናስብበት ታላቅ ዕለት ነው።

በዚህ ዕለት መምህራኑ ከመዝሙር "እስመ ንጉሥ ፈተወ ስነኪ ስምዒ ወለትየ ወርኢ ወአጽምዒ እዝነኪ ርስኢ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ ⇝ ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና" ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት በእርሷ መፈጸሙን ይመሰክራሉ።

ትንቢቱ ግን በእርሷ ብቻ የሚቀር አይደለም ቀድሞ ለቤተ እስራኤል ዛሬም ሊመስሏት ለሚጋደሉ ሁሉ የሚነገር ነው።

ለቀደሙት ሲነገር፦ ☞ ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ፡፡ [ስምዑ አሕዛብ ወርእዩ ወክሥቱ አልባቢክሙ] ☞ ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ፡፡ [ወኅድጉ ዘትካት ልማደ ወሰጊደ ለጣዖት] ☞ እስመ ፈተወ ንጉሥ ሥነኪ፡፡

[ፈጣሪሁ ለአዳም ለብሰ ሥጋሁ]

🍁 ህዝቦች ሁላችሁ ስሙ ተመልከቱ ልባችሁንም ክፈቱ የቀደመውን ልማድ ለጣኦት መስገድ ተዉ ፈጣሪያችሁ የፍጡሩን የአዳምን ሥጋ ለብሶ ሊያድናችሁ ወ’ዷልና። 🍁

በዚህ የትንቢት ቃል ለእኛ የተነገረውን መልእክት ቅዱሱ #አፈወርቅ_አባ_ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት ዘቁስጠንጥንያ የዓለም መምህር በተግሳጽ ፲፬ እንዲህ ይመክረናል።

⇨ ዘበእንቲአነ ይቤ ዳዊት ነቢይ በመዝሙር (ስለእኛ ዳዊት ነቢይ በመዝሙር እንዲህ ይላል)

☆ "እስመ ንጉሥ ፈተወ ስነኪ ስምዒ ወለትየ ወርኢ ወአጽምዒ እዝነኪ ርስኢ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ" (ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና)

✧ ወእመ ትቤለኒ ምንት ውእቱ ዘትረስእ ፣ እብለከ ረሲአ ኃጣውእ ውእቱ (የምትረሳው ምንድነው ትለኝ እንደሆነ ኃጢዓትን ነዋ! ኃጢዓትን መርሳት ነው ብዬ እመልስልሃለዉ)

✧ ርኢከኑ ኦ ፍቁር ርኅቀተ ፍኖት ዘይፈቅድ ትኩን ማእከሌነ ወማእከለ ኃጢአት ( እንግዲህ በእኛና በኃጢዓት መካከል ያለውን የመንገዱን ርኅቀት ተመልከትልኝማ የአባትሽን ቤት አታስቢ አላለም እርሺ አለ እንጂ )

✧ እስመ ኢይዜከር ዘኢይሔሊ (ነቅዓ ኃልዮ ከሌለ ቁርጽ ሃልዮ የለምና የማያስቡትን አያስታውሱትማ)

☆ ወዘኢይኄሊ ኢይትናገር (ቁርጽ ኃልዮ ከሌለ ነቢብ የለም ያልታሰበ ሊነገር አይችልማ )

☆ ወለእመኢተናገረ ኢይገብር (ነቢብ ከሌለ ገቢር የለም ያልተናገረውን አይሰራማ)

↪ የማይናገረውን አያስበውም ያላሰበውን አይናገረውምና ያልተናገረውን አይሰራውምና፤

☆ ወእመሰ ከመዝ ውእቱ ይደልወነ ንስማእ ዘይቤ ርስኢ (እንግዲህ እርሺ ያለውን በዚህ መልኩ ልንሰማው ይገባል)

☆ ወንርሳእ እከያቲነ ወአኮ ኃጣውኢነ
(ኃጢአታችንን እንርሳው ሰርተን እንዘንጋው ግን አላለም)

☆ እስመ ይቤ ተዘከር ኃጣውኢከ ቅድመ ከመ ኢይዘከር አነ
(እኔ እንዳላሳብብህ ቀድመህ አንተ አስበው ይላልነ ቀድሞ እንሰራው የነበረውን እንዳንሰራው ልንረሳው ይገባናል)

☆ እመቦ ዘይብል በአይቴ ይትከሃል ረሲዓ እከያት
(ከሃልዮ ኃጢአት በምን ነገር መዳን ይቻላል የሚል ቢኖር)

☆ ንብሎ እዎ ይትከሃል በተዘክሮ ሰናያት ወተዛውኦ በነገረ እግዚአብሔር ልዑል
(በጎውን ነገር በማሰብ የልዑል እግዚአብሔርን ነገር በመጫወት አዎ ይቻላል ብለን እንመልስለታለን)

ዛሬ እመቤታችን የአምላክ እናት ልትሆን የእናት አባቷን ቤትና ወገኖቿንም ሁሉ ረስታ ውበቷን የወደደውን ንጉሥ ፈጣሪዋን ሰምታ ወደ መቅደስ እንደገባች ፤

እኛም፦

« እስመ ንጉሥ ፈተወ ስነክሙ ስምኡ ውሉድየ ወአጽምዑ እዝነክሙ ርስኡ ሕዝበክሙ ወቤተ አቡክሙ ⇨ ንጉሡ ውበታችሁን ወ’ዷልና ልጆቼ ስሙ ወገኖቻችሁንና የአባታችሁን ቤት (እ)ርሱ»

ኃጢዓትን ረስተን (ከግብር አባታችን ከዲያቢሎስና በሥጋ ከሚለያየን ወገንተኝነት ተለይተን) ለቅድስና ሥራ ጥንተ ተፈጥሯችንን፣ በራሱ አምሳል የፈጠረውን ሰውነታችንን ወደወደደው ንጉሥ መቅደስ እንገባ ዘንድ የበቃን ያድርን።

✍️๏ ከቴዎድሮስ በለጠ 🖊 ታኅሣሥ በዓታ ፳፻፲፫ ዓ.ም. ከታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም።

Report Page