*/

*/

Source

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና የጽንፈኛው ህወሃት ምላሽ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና የጽንፈኛው ህወሃት ምላሽ በሚመለከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ከዚህ ቀደም በነበረው ሂደት ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጠ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወርሃ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ላይ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ለትግራይ እንደ ሁልጊዜው በማክበርና በሰላምና ልማት ላይ እንዲያተኩር ጥሪ በማቅረብ ህወሓትም እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በሰላምና አገራዊ ፖለቲካ ዙሪያ በጋራ እንዲሰራ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

ፓርቲና ህዝብ የተለየ መሆኑን ሁሉም እንዲገነዘብ ሲመክሩና ሲያስረዱ ቆይተዋል፤

ከዚህ አኳያ ለህወሓት በተደጋጋሚ በሰላማዊ መልኩ እንዲንቀሳቀስና ለውጡን ለትግራይ ህዝብ ሰላም እንዲጠቀምበት ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ በታች ዋና ዋናዎቹ እንደ አብነት ቀርበዋል።

ሚያዚያ 5 ቀን 20 10 ዓ.ም፣

• ወደ መቀሌ በማምራት ከህብረተሰቡ ጋር ውይየት አደረጉ፤
የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መንግስታቸው ከክልሉ አመራር ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ገልጸው፤ የትግራይ ህዝብም በሰላም እና ልማት ላይ እንዲያተኩር፣ ክልሉን የሚመራው ህወሓትም በህዝቡ የፀረ ድህነት ትግል ላይ አትኩሮ እንዲሰራ ጥሪ አቀረቡ። የክልሉ ነዋሪዎችም ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ለውጡን ተከትሎም ስጋት አድሮባቸው የነበሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን አበረታትውና ጥያቄያቸውን ተቀብለው ተመለሱ።

ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም

• ወደ አክሱም በማቅናት በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ፣
በአደጋ ላይ ያሉትን የአክሱም ሐወልቶች የጎበኙ ሲሆን ሃውልቶቹ በሚጠበቁበት ሂደት ላይ ከጣልያን መንግስት ጋር ንግግር እያደረጉ መሆኑን ተናገሩ።

ህዝቡ ሰላም፣ፍቅር ይቅርታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየታዩ ያሉ ፖለቲካዊ የጸጥታ ችግሮች እንዲፈቱ፣ ክልሉን የሚመራው ህወሓትም ለሰላም በጋራ እንዲሰራ ጥሪ አቀረቡ።

የካቲት 04 ቀን 2011 ዓ.ም

• ማናቸውንም አይነት ችግሮች በሀገር በቀል መፍትሄ እንዲፈቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በማቋቋም ጥሪ አቀረቡ፤
በትግራይ ክልል መንግስትና አጎራባች አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶች በሀገር ውስጥ ከተለያዩ ወገኖች በተውጣጡ ታዋቂ ሰዎች የጋራ ሽምግልና ጥረት እንዲፈቱ በህዝብ የተመረጡ ገለልተኛ የአገር ሽማግሌዎች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ኮሚሽን እንዲቋቋም አደረጉ።

ለዚህም ሁሉም ወገን፣ በተለይም የትግራይ መንግስት እንዲተባበር ጥሪ አደረጉ፤
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፤ እውነት እና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅን ለማውረድ እንዲያግዝ የተቋቋመ ነው።

በወቅቱም፣ የኮሚሽኑ አባላት ከዘር፣ ከሀይማኖት እና ከመድሎ በፀዳ መልኩ ስራቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ አደራ አስተላለፉ።

መንግስትም በእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ስራ ጣልቃ እንደማይገባ ቃል ገቡ።
በተመሳሳይ በክልሎች መካከል የሚነሳን የማንነትና ወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሰላም የሚፈታ የወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚቴ አዋቀሩ፤

ነገር ግን ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በዚህ ወቅት ሂደቱን አጣጥሎ፤ እንደማይቀበልም በይፋ አሳውቆ ነበር።

ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም

• 50 አባላትን ያካተተ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የሀገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ተላከ፣
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለው መልካም ያልሆነ ግንኙነት በንግግር እንዲፈታ አንድ የሽማግሌዎች ቡድን ወደ መቀሌ ላኩ፤

ቡድኑ በመቀሌ ከትግራይ ክልል መንግስትና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ቢወያዩም የወቅቱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል ለቡድኑ ይሁንታ ነፈጉት፤

ይልቁንም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እስካሁን ድረስ የት ነበራችሁ፤ የሚያስፈልገው እርቀ ሰላም አይደለም በሚል በሽማግሌዎች ጥረት ላይ ውሃ ቸለሱ፤ የቡድኑ አባላትም በህወሓት ጀሌዎች ስድብና ማዋረድ ደረሰባቸው፤

ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም

• ህወሓትና ጥቂት ደጋፊዎቹ ለውጡን እንደ እድል በመጠቀም በጋራ እንዲሰሩ፣ ካልተገባና አገር አፍራሽ የፖለቲካ ትርፍ ጉዞ እንዲታቀቡ በምክር ቤት ቆይታቸው መከሩ፤

ለህዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ “ የኢህአዴግ” ን ውህደት አሃዳዊ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ሩጫ ነው እያሉ ህዝብን የሚያደናግሩ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ ኢህአዴግ ፓርቲ እንጂ ሀገረ መንግስት እንዳልሆነ አስረዱ።

ዜጎችም ሆነ ብለው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እኩይ ተግባር ውስጥ በገቡ አካላት እንዳይደናገሩ መከሩ።

ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም

• መንግስት በዜጎች ህይወት ላይ በመቆመር ጥቅማቸውን ለማስመለስ የሚሰሩትን እንደማይታገስ አሳሰቡ፣

በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ ረብሻ የ86 ዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስመልክተው ባስተላላፉት መልዕክት በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተሸፍነው ያጡትን ጥቅም ለማስመለስ ኢትዮጵያውንን በብሔር ከፋፍሎ ለማጫረስ በስውር የሚሰሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ።

የመንግስትን ሆደ ሰፊነት እንደ ፍርሃት በመቁጠር ህግን በሚጥሱ አካላት ላይ መንግስት እንደማይታገስ አጽንኦት ሰጥተው ገለፁ።

ሚያዚያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም

• የትግራይ መንግስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን በማክበር የትግራይን ህዝብ ከኮሮና በመጠበቅ ህግ እንዲያከብር አሳሰቡ፤

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሀገራዊው ምርጫ ማራዘምን ተከትሎ ህወሃት ውሳኔውን እንደማይቀበለው መግለጹን፤ ተከትሎ ባስተላላፉት መልዕክት የትግራይ መንግስት የምክር ቤቶችን ውሳኔ እንዲያከብርና ኮሮና በተስፋፋበት ወቅት የጨረባ ምርጫ ማካሄዱ ዞሮዞሮ ጉዳቱ የህዝብ መሆኑን ተገንዝቦ ለህግ ተገዢ እንዲሆን አሳሰቡ።

ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ/ም

• ህወሓት አንድ ፓርቲ እንጂ ህዝብ አለመሆኑን፣ በህዝቡም ሊነገድበት እንደማይገባ፣ መንግስት ለትግራይ ህዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስታወቁ፤

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ የህወሃት ተወካዮች መንግስት ትግራይን ያገለለ ስራ እያከናወነ አስመስለው ቅሬታ ባቀረቡበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለትግራይ ክልል የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ከፍ እንዳለና ለዓመታት ሲጓተት የነበረው የመቀሌ ውሃ ፕሮጀክት እንዲያልቅ መንግስት ከፍተኛ ብር መድቦ እየሰራ መሆኑን ይፋ አደረጉ፤

“የትግራይ ህዝብ ህዝባችን ነው፤ ህወሃት አንድ ፓርቲ እንጂ ሰላም ወዳዱን ትየግራይን ህዝብ አይወክልም” ሲሉ በተደጋጋሚ በህዝብ ተወካዮች አባላት ፊት ተናገሩ።

ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም

• ያለችን አንድ ሀገር ነች፤ ልዩነቶችን በሰከነ አግባብና በሰለጠነ ውይይት እንፍታ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፤
ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለችን አንድ ሀገር መሆኗን ተረድተው ልዩነቶችን በሰከነ አግባብና በሰለጠነ ውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሀምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም

• አንድ እግራቸውን የትጥቅ ትግል ሌላኛ እግራቸውን ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ አድርገው ህዝብን የሚያደናግሩ አካላት እንዲጠነቀቁ አሳሰቡ፤

ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት አንድ እግራቸውን የትጥቅ ትግል ሌላኛ እግራቸውን ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ አድርገው ህዝብን የሚያደናግሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ አሳስበዋል።

የ2013 አዲስ ዓመት ዋዜማ፣

• ህወሓት መንግስት የሀይል አማራጮችን እንዲወስድ ከሚያነሳሱ ትንኮሳዎች እንዲታቀብ አሳሰቡ፤

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግስት ለትግራይ ህዝብ ጦርነት ሳይሆን ልማትና ብልጽግና እንደሚያስፈልገው በይፋ ተናግረዋል።

መንግስታቸውም የትግራይን ህዝብ ከመርዳት ባለፈ ምንም አይነት የግጭት ፍላጎት እንደሌለውም ገልፀዋል።

ነገር ግን መንግስት የተለያዩ የሃይል አማራጮችን እንዲወስድ ህወሃት ትንኮሳ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ የትግራይ ህዝብን በስሙ እየነገዱ ወደ ግጭት ሊወስዱት እየሰሩ ያሉ አካላት እንዳሉና ህዝቡም ይህን አጥብቆ እንዲታገል በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

ሆኖም፣
➢ በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን በክልሉ ያሉ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ለስራ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ውቅት ህጻናትን ጎዳና ላይ እያስተኙ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

➢ የሰራዊቱ አባላት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ያልተፈለገ ፍተሻ በማድረግም ከፍተኛ እንግልት ሲያደርጉ ቆይታዋል።

➢ የመከላከያ ሰራዊቱ ይህን ሁሉ ትንኮሳ በትዕግስት ሲያልፍ ቆይቷል።

➢ ይህ አልበቃ ብሎ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አዛዥን በመቀሌ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ በማገት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ አድርገዋል።

ጥቅምት 23 ቀን 20 13 ዓ/ም

➢ የህወሓት ጁንታ ጥቃት ከመፈጸሙ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ የጽንፈኛው ቡድን መሪ የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጦርነት ትግራይ ላይ እንደማይቀርና ህዝቡ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅረቡ።

ወደ ትግራይ የሚመጡ ማናቸውንም አካላት “እንቀብራቸዋለን” ሲሉ የጦር አውርድ ነጋሪት በአደባበይ ጎሰሙ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም

➢ ጽንፈኛ ቡድኑ ያደራጃቸው የልዩ ሀይሉ ታጣቂዎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ ከወገን የማይጠበቅ ዘግናኝ ጥቃት በሌሊት ፈጸሙ።

➢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጽንፈኛ ቡድኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም ቀይ መስመር እስኪጥስ ድረስ ሃሳባቸው አንድ ነበር "ሰላም፤ይቅርታ፣ እርቅና ብልጽግና"።

ይህን ሃሳባቸውንም በአገኙበት አጋጣሚ ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

➢ ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በሰሜን እዝ አባላት ላይ አሳፋሪ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ( በነገራችን ላይ ጽንፈኛ ቡድኑ ጥቃት መፈጸሙን የቡድኑ አፈቀላጤ ሴኮ ቱሬ ጌታቸው ማመናቸው ይታወሳል) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ

ባስተላለፉት መልክት መንግስት ለሰላም ሲል በሆደ ሰፊነት በርካታ ትንኮሳዎችን ማለፉን ጠቁመዋል። መንግስት ይህን ያደረገውም “የትግራይ እናቶች እስከ መቼ ያለቅሳሉ” በሚል መርህ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ጥቅምት 25/2013 ዓ/ም

• ቀዩ መስመር ስለታለፈ፣ የሰላም ጥሪው ዋጋ ማጣቱን በመግለፅ ህግ የማስከበር እርምጃ ግድ መሆኑን አሳወቁ፤

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ንጋት 11 ሰዓት ላይ በሰራዊታችን ላይ በህወሓት ጁንታ ያልተጠበቀና ዘግናኝ ጥቃት መፈፀሙን በሀዘን አስታወቁ፤ ቀይ መስመር የታለፈ መሆኑን፣

ለረጅም ጊዜ ለህወሓት ቡድን የሰላም ጥሪ ሲደረግ ቢቆይም፣ ይህን ባለመቀበልና የእናት ጡት ነካሽ በመሆን የማይደፈረውን የሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነት አስጠባቂ የሆነው ሀይላችን ተደፈረ ሲሉ ገለፁ፤

መንግስት በዚህ አረመኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላለፉ፤ መንግስት በትግራይ ህዝብ ላይ ግን የማይለወጥ አቋም እንዳለውና የትግራይ ህዝብንና የህወሓት ጁንታን መላው ህዝብ ለያይቶ እንዲመለከትም ለመላው ህዝብ አሳሰቡ፤

ህዳር 4 ቀን 2013 ዓም

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት የህግ ማስከበር እርምጃውን ተከትሎ የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትና ሚሊሻዎች በሶስት ቀናት ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡም ጊዜ ገደብ ሰጥተዋል፤ በርካታ ሰላም ወዳድ የክልሉ ጽጥታ አካላትም እድሉን ተጠቅመዋል።

አሻፈረኝ ብለው በቀሩት ላይ በሚወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ ወቅት ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱም የመከላከያ ሰራዊቱ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ኦፕሬሽኑን እንዲያከናውንም ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

በተቃራኒው ጽንፈኛው የህወሃት ጁንታ በአማራ ክልል ርእሰ መዲና ባህርዳር እንዲሁም በጎንደር ከተማ ንጹሃን ላይ ትኩረት ባደረገ መልኩ ሮኬቶችን ተኩሷል፤ በመሰረት ልማት ላይም ጉዳት አድርሷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Report Page