*/

*/

Source

‹‹ ትህነግ በጫካ እንዲወልዱ የፈረደባቸው እናት ሰቆቃ ››

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 13/ 2013 ዓ.ም (አብመድ) ትህነግ በተቀደሰችው ምድር የረከሰ ነገር ሲያደርግ ኖረ፤ በጅምላ ቀብሯል፣ ከቀያቸው አፈናቅሏል፤ ማንነት ቀምቷል፤ በድቅድቅ ጨለማ በተመላ እስር ቤት ውስጥ በንፁሃን የግፍ ማዕበል አውርዷል፡፡ ዘመኑን በክፉ የዋጀው ትህነግ የፍጻሜው ዘመን ሲደርስ የማይደፈረውን ደፈረ፡፡ የኢትዮጵያን አጥር ሰብሮ ቢሻው ጠላት እንዲገባ ካለበዚያም ኢትዮጵያን ለተጨማሪ ዓመት ረግጦ ሊገዛ ከጀለ-ተስፋ ብቻ ሆነበት እንጂ፡፡

የውሸት ዘመን ሲያልቅ፣ የእውነት ዘመን ሲመጣ፣የኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ሲሰማ የማይነካውን የነካው ትህነግ ራሱ የሰራውን የጨለማ ቤት ሊያዬው የተቃረበ ይመስላል፡፡ በጫረው እሳት እየተለበለበ ነብስ አውጪኝ የሚፈረጥጠው ትህነግ ከሞት አፋፍ ላይ ሆኖም ከክፉ ሥራው አልተማረም፡፡ ጠመንጃ የያዘውን ጦረኛ መጋፋት ሲያቅተው ምርኩዝ ያልያዙትን ንጹኃንን መርጦ በግፍ ገደላቸው፡፡ በሰቆቃ ድምፅ አጅቦ ጨፈጨፋቸው፡፡ የማይካድራ የግፍ ነብሶች በዚያች ምድር እንደጮኹ ይኖራሉ፡፡ የትህነግ የጨለማ ሠራዊቶች ደግሞ ወደ ጨለማ ይወረወራሉ፡፡ ካለበዚያም ግፍ በሰሩባት ቅድስት ምድር ውስጥ ይቀበራሉ፡፡

የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የሚተፋውን እሳት አልችል ያለው የትህነግ የግፍ ሠራዊት ወደኃላ ሲሸሽ በፊቱ ያገኛቸውን ከወትሮውም አምርሮ የሚጠላቸውን ለኢትዮጵያ መልካም እሳቤ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን የግፍ ማዕበል አፍሶባቸዋል፡፡ ግፍ መስፈር የማይሰለቸው ይህ የእኩይ ስብስብ በሁመራ ሆስፒታል የነበሩ ንጹሃን ኢትዮጵያዊያን በሰቆቃ እንዲሞቱ ፈርዶባቸዋል፡፡ በትህነግ ምክንያት የሰቆቃው ተካፋይ የነበሩት በምጥ የተያዙት የተስፋዓለም ገብረ ሚካኤል ባለቤት ያቺ ቀን ለእሳቸው ከባድ ነበረች፡፡

በምጥ የተያዙት ንጹህ እናት በትህነግ ሌላ ምጥ ተሰጣቸው፡፡ ትህነግ በልጉዲ ግንባር በእሳት ላንቃ፣ በማይስት አፈሙዝ ሲገረፍ የተስፋዓለም ባለቤት በማይካድራ ጤና ጣብያ በምጥ ተይዘው ተኝተው ነበር፡፡ እግር አውጪኝን ከልጉዲ የፈረጠጠው የእኩይ ስብስብ በማይካድራ ከተማ አማሮችን ብቻ ለይቶ መጨፍጨፍ ጀመረ፡፡ በምጥ የተያዙት እናት ተደራቢ ምጥ መጣባቸው፡፡ በዚያች ጤና ጣብያ የትህነግ ደቀ መዝሙሮች ነበሩና ተስፋ ዓለምና ምጥ የተያዙት ባለቤታቸው ከጤና ጣብያው እንዲወጡ አደረጓቸው፡፡

ሁለት ልጅ አሳይተዋቸው ሶስተኛውን ከውድ ባለቤታቸው የሚጠብቁት ተስፋ ዓለም ባለቤታቸውን ይዘው ከግፍ ለማምለጥ እንደ ዱር እንስሳ ወደ ጫካ ኮበለሉ፡፡ በዚያ በረሃ ውስጥ፣ ማርያም ትማርሽ የምትል ሴት፣ ደም እንዳይፈስሽ የሚል የጤና ባለሙያ፣ አፋቸውን የሚያርሱበት ንፁህ ውሃና ቁራሽ እንጀራ አልነበረም፡፡ በጭንቅ ቀን የመጣው ምጥ በዚያው በረሃ ውስጥ መጣ፡፡ በበረሃ ውስጥ የተወሸቁት ነብሶች እትብት የሚቆርጡበት ምላጭ እንኳን አልነበራቸውም፡፡ ያለ ምንም ብቻቸውን ወደ በረሃ የሸሹት ተስፋዓለም ልጃቸውንና ወላጅ እናታቸውን የግፍ ፅዋ በፈሰሰባት ከተማ ጥለው ነበር የሸሹት፡፡ በዚያች ከተማ ምን ሊሆኑ እንደሚችል መገመት አይቻልም፡፡ ያቺ በደል የሌላባት ለምድር አዲስ የሆነች ነብስ በጫካ ተወለደች፡፡ በጭንቅ ቀን ጭንቅ ነገር የገጠማቸው ተስፋ ዓለም ከበረሃ ወጥተው ባለቤታቸውን ይዘው ወደሁመራ ሆስፒታል ቢሄዱም በማይካድራ የቀሩት ውድ እናታቸውና ልጆጃቸው ምን ላይ እንዳሉ አላወቁም፡፡

በበረሃ የወለዱት እናት በሁመራ ሆስፒታልም ጉሮሯቸውን የሚያረሰርስ፣ አንጄታቸውን የሚያርስ ምግብ አላገኙም፡፡ ለነብስ ማደሪያ የሚሆን ከአማራ ልዩ ኃይል ብስኩትና ኮቸሮ ቢቸራቸውም ለአራስ እናት ግን ከጎሮሮ የሚወርድ አልነበረም፤ ብቻ ግን ከሞትና ከበረሃ ይሻላል፡፡

በሁመራ ሆስፒታል የነበሩት የትህነግ ደቀ መዝሙር የጤና ባለሙያዎች መምህራቸውን ተከትለው ሲኮበልሉ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የተደረጀው የጤና ባለሙያ ቡድን ከጭንቅ የተረፉትን እናት እየተንከባከበ ነው፡፡ ትህነግ ደቀመዝሙሮቹን ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ ሲያዝዝ በዚያ ሆስፒታል የነበሩ 22 ታካሚዎች ላይመለሱ አሸለቡ፡፡ ሌላ ግፍ ሌላ በደል፡፡

ንጹኀን በግፍ አለቁ፣ ያልጠበቁት ወጀብ ወሰዳቸው፤ ዳሩ ግን ክፉውን ሁሉ ያደረገው ትህነግ በማይስት አፈሙዝ እየተገረፈ፣ ግብዓተ መሬቱ ሊፈፅም የተቃረበ ይመስላል፡፡ ከትህነግ መቃብር በኋላ በጥቁር ደመና ተጋርዳ የነበረችው የኢትዮጵያዊያን ፀሐይ ደመናዋን ገፋ በእኩል ታበራለች፡፡ እኩል ታበቅላለች፣ እኩል ትመግባለች፡፡ ያ ቀን ሩቅ አይደለም፡፡

ከስፍራዉ መረጃውን ወንዳጥር መኮንን አደረሰን ታርቆ ክንዴ አዘጋጀው፡፡

Report Page