*/

*/

Source

የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሕዳር 17 ይካሄዳል

የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያዘጋጁት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ሕዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ። 

የሕወሓት የጥፋት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በክልሉ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።

በኪነጥበብ ባለሙያዎች "ጥበብ ለአገር ክብር" በሚል ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋመው ኮሚቴ አባል አርቲስት ደበበ እሸቱ ሕዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም "የአገር ልጅ የማር እጅ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚከናወን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዕለቱ በሁሉም ክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ታዋቂ ግለሰቦች የሰላም ሚኒስቴር ማህተም ያረፈበት የድጋፍ ቃል ማስገቢያ ወረቀት በነጠላ፣ በዣንጥላ፣ በመሶብና በአገልግል ይዘው በመዞር ቃል የማስገባት ተግባር ይፈጽማሉ ብለዋል።

የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣መስሪያ ቤቶች ፣ ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎች፣አምራቾችና ሌሎች ቦታዎች የቃል መግቢያ ወረቀቱን ይዘው እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

ሙሉ ቀን ወረቀቱን ይዞ በመዞር የሚቻለውን ያህል ገንዘብ ቃል በማስገባት ቃል የገቡ ሰዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሒሳብ ቁጥር 1000354217019 መላክ እንደሚችሉ ነው አርቲስት ደበበ ያስረዱት።

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የንግድ ባንኩን CBETETA ዓለም አቀፍ ስዊፍት ኮድ ተጠቅመው ገንዘቡን መላክ ይችላሉ ብለዋል።

የሚሰበሰው ገንዘብ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማሰባሰብ የተቋቋመውና በሰላም ሚኒስቴር ሰብሳቢነት ለሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ ገቢ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ድጋፉ ከመከላከያ ሰራዊት በተጨማሪ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ተገደውና ያለ እድሜያቸው ወደ ውጊያ ገብተው ጉዳት ለደረሰባቸው ወጣቶች፣ ልጆችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚውልም ገልጸዋል።

"ማር ምግብ ሆኖ ይበላል ምግቡ ሲያልቅ ሰሙ ብርሃን ይሆናል እኛ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ወደፊት የሚታየን የኢትዮጵያ ብርሃን ነው" ብለዋል አርቲስት ደበበ።

"ለአገር መከላከያ ሰራዊት ክብር እቆማለሁ" በሚል መሪ ቃል ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ለመከላከያ ሰራዊት ክብርና ድጋፍ ለመግለጽ የተዘጋጀው መርሃ ግብር ውጤታማ እንደነበርም አውስተዋል።

በቀጣይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መከላከያ ሰራዊት የሕግ ማስከበር ስራ በሚያከናውንባቸው ቦታዎች በመሄድ አጋርነታቸውን እንደሚገልጹም ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ በአገልግል ምግብ ይዘው ወደ ቦታው እንደሚያቀኑም በመግለጽ።

የኪነጥበብ ባለሙያዎች ድጋፍና አጋርነት የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጠናቀቀ በኋላም ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራዎችም እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በቀጣይ የተቋቋመው ኮሚቴ ቀጣይ በሚኖሩ መርሃ ግብሮች በመወያየት ያሉ ዝግጅቶችን ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግም አክለዋል።
(ኢዜአ)

Report Page