*/

*/

Source

ህወሃት ህፃናትን በውጊያ ላይ ለምን አሰለፈ?

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) ወደ ጦርነት የሚገባ ማንኛውም አካል በያንዳንዱ ድርጊት ዓለም አቀፍ ክልከላዎችን የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ከክልከላዎች ውስጥ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በጦርነት ማሰለፍ ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ በህግ እንደሚያስጠይቅ ተቀምጧል፡፡ ሀገራት ደግሞ እነዚህን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ተቀብለዋል፡፡ ከሀገራቱ መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡

የባሕርዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ አስተባባሪ ባየህ እምቢአለ በሰጡን ማብራሪያ ህፃናትን ለጦርነት ማሰለፍ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጅ ህውሃት በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ህፃናትን በጦር ግንባር በማሰለፍ ዓለም ዓቀፍ ህግን ጥሷል ብለዋል፡፡

ለመሆኑ ህወሃት ህፃናትን በውጊያ ላይ ለምን አሰለፈ? ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡን የህግ ባለሙያው ባየህ እምቢአለ መንግስት በሚወስደው ርምጃ ህፃናት እንደተገደሉ አድርጎ ለዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ አቤቱታ በማሰማት ድጋፍ ለማግኘት የታሰበ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ ላለመሆንና ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ህፃናትን ወደ ጦርነት አስገብተዋቸዋል ነው ያሉን፡፡

ከዓለም አቀፍ ሕጎች ውስጥ ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች፣ የአፍሪካ ህፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር፣ የሕፃናት መብት ድንጋጌ እና ዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎች ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በጦርነት ማሰለፍ ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ በህግ እንደሚያስጠይቅ ተቀምጧል፡፡

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ህግ እንዲሆኑ መቀመጡን የህግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ የወንጅል ህግ 270/13 ላይም ዕድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸውን ህፃናት ለጦርነት ማሳተፍ እስከ እድሜ ልክ ወይንም በሞት እንደሚያስቀጣ መቀመጡን ነው ያስረዱት፡፡

ይሁን እንጅ ይህን ሁሉ ህግ እያወቀ ህውሃት 18 ዓመት ያልሞላቸውን ህፃናት ጭምር በጦር ግንባር ማሰለፉ ዓለም አቀፍ ወንጀል መሆኑን ነው የህግ ባለሙያው የገለጹት፡፡
ዓለም አቀፍ ህግን ጥሶ ወንጀል የፈጸመን ቡድን ለህግ የማቅረብ ደግሞ የመንግስ ኃላፊነት መሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

ሕፃናትን በጦርነት ያሰለፉ ቡድኖች ወንጀሉ በተፈጸመበት ሀገር ለህግ ባይቀርቡ እንኳ ወንጀሉ ዓለም አቀፍ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያስጠይቅ የባሕርዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ አስተባባሪ ባየህ እምቢአለ አስገንዝበዋል፡፡

በዳግማዊ ተሰራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ
በዌብሳይት
በቴሌግራም
ትዊተር

Report Page