*/

*/

Source

ማህበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የትህነግ ህገወጥ ቡድን አሰልጥኖ የሚልካቸውን ቅጥረኞች በመከታተል ለፀጥታ አካላት መረጃ እየሰጡ መሆኑንም የወልደያ እና የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) ማህበረሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መከላከል እንደሚገባው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል፡፡ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነውን ሠላም ለመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ኮሚሽኑ አስገንዝቧል፡፡

ከአብመድ ጋር በስልክ ቆይታ የነበራቸው የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ አቶ ይርሳው ደምሴ ማኅበረሰቡ ሠላሙ ተጠብቆ እንዲኖር በንቃት አካባቢውን እየጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

የትህነግ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ከፈጸመው ክህደት በተጨማሪ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች መሰሎቹን አሰማርቶ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመከላከልም ሕዝባዊ አደረጃጀቶችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ የወልድያ ከተማ ነዋሪው አቶ እያሱ ደሳለኝ አሁን ላይ የአካባቢያቸው የፀጥታ ሁኔታ የተሻለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ባደረገው ተሳትፎም 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ማህበረሰቡ ከፖሊስ፣ ከክልሉ ልዩ ኃይል እና ከአካባቢ ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት የሚሰራበት አደረጃጀት መመቻቸቱንም አቶ እያሱ ነግረውናል።

የትህነግ ህገወጥ ቡድን በግልጽ ከሚሰራው ጥፋት በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች አሰልጥኖ የሚልካቸውን ቅጥረኞች ማኅበረሰቡ በመከታተል ለፀጥታ አካላት እየጠቆመ እንደሆነም አቶ እያሱ ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የስልጠና እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክትር ዐብይ ሙሉጌታ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ያሉ አደረጃጀቶችን በማጠናከር እና አዳዲስ መረጃዎችን በማድረስ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ እንዲጠብቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ማህበረሰቡ ባደረገው ጥቆማም በወልድያና ባሕር ዳር ከተማ ለሽብር የተዘጋጁ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ቤተ እምነቶች በፌዴራል ፖሊስ፣ በድርጅቶችና በራሱ በማኅበረሰቡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡም ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ትብብር አጠናክሮ በማስቀጠል አካባቢውን ከሕወሓት ቅጥረኛ ቡድን ሊጠብቅ እንደሚገባ ዋና ኢንስፔክትር ዐብይ ሙሉጌታ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ
በዌብሳይት
በቴሌግራም
ትዊተር

Report Page