*/

*/

Source

ሰበር ዜና!

በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ በፋርዘይት ቀበሌ ለጥፋት የሚውል ከፍተኛ ገንዘብ መከፋፈሉን፣ ለገንዘብ ብለን ወገናችን አንገድልም ያሉ የጉምዝ ተወላጆች አጋለጡ፤ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መንግስትና ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳሰቡ።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ ሸዋ

በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ፋርዘይት ከተባለ ቀበሌ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል የደረሰው መረጃ እንዳመለከተው ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለጥፋት ሀይል ለተሰማሩ የጉምዝ ታጣቂዎችና ተባባሪዎቻቸው ሲከፋፈል ማምሸቱን ያሳያል።

ዛሬ ህዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የተለቀቀለት የጉምዝ ታጣቂዎች ተባባሪ ለበርካታ ተባባሪ አካላት ለማከፋፈል ሲሞክር ለገንዘብ ብዬ ቀይን/አማራን አልገልም በማለት ቅሬታ የተሰማቸው ግለሰቦች መረጃውን አሹልከው ማውጣታቸው ተገልጧል።

የአማራ ሚዲያ ማዕከልም በዛሬው እለት የተከፋፈለውን ገንዘብ በተመለከተ ለገንዘብ ብየ አብሮን እየበላን፣እየጠጣን ያለውን ሰው አልገልም በሚል መረጃ ያካፈሉንን የጉምዝ ተወላጆች በቀጥታ የስልክ መስመር አግኝተን አነጋግረናል ከደህንነት አኳያ ግራ ቀኙን በማየትና ሁኔታዎችን በመገምገም እንደአስፈላጊነቱ የምናጋራ ይሆናል።

የገንዘቡ ምንጭ በትክክል ከየት እንደሆነ በትክክል ለማወቅ እንደማይችሉ የገለፁት ምንጫችን አንድ መኪና የሚያስገዛ ገንዘብ እንሰጣቹሀለን በማለት በርካታ የጉምዝ ወጣቶችን እያታለሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀበሌ መዋቅር ላይ ሆነው በሁለት ካራ የሚበሉ አካላት እንዳሉም ተጠቁሟል።

ይህ መረጃ የደረሳቸው የፋርዘይት ቀበሌ ነዋሪዎች ገንዘቡ ውስጥ ለውስጥ ስለመከፋፈሉ መስማታቸውን ተከትሎ በሽብር ተግባር የተሰማራው ቡድንና ተባባሪዎቹ ጉዳት እንዳያደርሱብን መንግስት በአስቸኳይ ችግራችን ተረድቶ አስፈላጊውን ማጣራትና ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስበዋል፤ ቀድማችሁ ድረሱልንም ብለዋል።

ይህ መረጃ እየደረሰው እና እየሰማ በዝምታ የሚያልፍ የክልሉ መንግስትም ሆነ ኮማንድ ፖስት ቀድሞ ባለመከላከሉና ሀላፊነቱን ባለመወጣቱ ለሚደርሰው በደል ተባባሪና ተጠያቂ እንደሆነ መገንዘብ አለበት ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በተመሳሳይ በዛሬው እለት ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ አንድ የፖሊስ አባልና በድባጤ ወረዳ የአቅም ግንባታ አመራር ለስራ ጉዳይ ከተመደቡበት ሲርበን ቀበሌ መሄድ ትተው ወደ ቀዮች በሚገኙበት ቀበሌ በመሄድ ህዝቡን በመሰብሰብ በቦንብ ጥቃት ለማድረስ በዝግጅት ላይ ሳሉ የኮመድ ባዚና ግርዝ ቀበሌ ነዋሪዎች አስረው ለመንግስት አስረክበዋል።

በሳስማንደን ቀበሌ ትናንት ሌሊት የጦርነት ፊሽካ ሲነፉ አድረዋል፤ በመጨረሻም እርስ በርስ ተገላግለውና የህዝቡን ቅድመ ዝግጅት አደገኛ መሆኑን ተመልክተው ጥቃት ሳይፈፅሙ መሸሻቸው ተሰምቷል።

ሌላው በሳስማንደን ቀበሌ ዛሬ ከሰዓት አንድ የጉምዝ የተለቀቀ ቤት ባልታወቀ አካል መቃጠሉን ተከትሎ ያልታወቁ 6 ፀጉረ ልውጥ ሰዎች አመሻሹን በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፤ ቀን ላይም የጉምዝ ታጣቂዎች መንገድ ለመዝጋት ሲሞክሩ መከላከያ ደርሶ 3 ስለመግደሉ የገለፁት ምንጫችን ስጋት ስለመኖሩና ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

የፋርዘይት ነዋሪዎችን ጥቆማ መሰረት በማድረግ የድባጤ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደበሌ በልጋፎን ያነጋገርን ሲሆን እሳቸውም መረጃው ቀድሞ እንደደረሳቸው በማረጋገጥ ለኮማንድ ፖስቱ መረጃውን እንዲደርስ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

በልዩ ሀይል ስም ተደራጅቶ በአልባሳ ቀበሌ ከጉምዝ ታጣቂዎችና ከተባባሪዎቻቸው ራሱን ሲከላከል የነበረውን የአቶ ወርቁ በቀለን መሳሪያ ከልጃቸው በመንጠቅ ለጥፋት ሀይሎች ያስረከበና ጉዳት ያደረሰ አለ ወይ? በሚል ለተነሳባቸው ጥያቄ አቶ ወርቁ መቁሰላቸውን ተከትሎ ልጃቸው ጉዳት እንዳያደርስ በሚል መሳሪያውን በልዩ ሀይል የተነጠቀ መሆኑን ስለመስማታቸው ተናግረው በተባለው አግባብ ቅሬታ ካለም እናጣራለን ብለዋል።

ነገር ግን የአልባሳ ቀበሌ ነዋሪ እንደሚሉት የአቶ ወርቁ በቀለ የተባሉ ነዋሪ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ሲከላከሉበት የነበረውን መሳሪያን እሳቸው ተመተው ሲቆስሉ ልጃቸው ትጥቃቸውን በማንሳት ተታኩሷል።

ህግ አስከብራለሁ ብሎ በመሀል የገባው የጉምዝ ልዩ ሀይል ግን ከአቶ ወርቁ ልጅ ነጥቆ ለሌላ የጉምዝ ታጣቂዎች ተባባሪ እንደሰጠና መሳሪያውን ቀምቶ ልዩ ሀይሉ ከመውጣቱም በአቶ ወርቁ በቀለ 2 ልጆች ላይ ጥቃት መፈፀሙንና መቁሰላቸውን፣የታረደ፣በቀስት የተመታ ስለመኖሩ ጠቅሰው ልዩ ሀይሉ አስገድሎናል፤ ሚዛናዊ ናቸው ብለን ለማመንም ተቸግረናል ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ደበሌ አያይዘውም የኦነግ ሸኔና የጉምዝ ታጣቂዎች እንዲሁም ጉህዴን የተባለ ድርጅት እያሰለጠነ በንፁሀን ላይ ጥቃት እያፈፀመ መሆኑን ገልፀው በድባጤ ጋሌሳ ቀበሌ ላይ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ህዳር 6ለ7 ንጋት ላይ አንድ ሽፍታን አስፈትተው መውሰዳቸውን፣ሌሎች በርካታ እስረኞችም እንዲያመልጡ ማድረጋቸውን፣ የፖሊስ፣የብድርና ቁጠባና የቀበሌ አስተዳደር ቢሮ ሰነዶችን ስለማቃጠላቸውም አውስተዋል።

ከአልባሳ፣ከሙዘንና ከሌሎች ቀበሌዎች እየተፈናቀሉ ላሉ አማራዎችም እስካሁን የጋሌሳ ቀበሌ ነዋሪዎች ከሚያደርጉት እገዛ ባለፈ በመንግስት ድጋፍ አለማድረጉን አምነው የሚመለከተው አካል በተለይም የአደጋ ስጋትና መከላከል ተቋም እንዲሰራ አቅጣጫ ተሰጥቶት እንቅስቃሴ ላይ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

Report Page