*/

*/

Source

"150 ጥይት ተስጥቶኝ አንድም ጥይት ሳልተኩስ ነው እጄን የሰጠሁት ምክንያቱም በዚህ ውጊያ አላምንበትም"

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 07/2013 ዓ.ም (አብመድ)
አብረኸት የጁንታው ታጣቂ የነበረችና እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ከሰጡ ውስጥ አንዷ ነች። ገና የ21 አመት ወጣት ናት፡፡ ወጣቷ በ2011 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ስልጠና ወስዳለች፡፡

የኢፕድ ድርጂት እንደዘገበው የኢትዮጵያ መካላከያ ሰራዊት አባል ሁና ነገሌ ቦረና ተመድባም ግዳጇን እየተወጣች ሳለ በጠና ታማ ከውትድርናው ዓለም ተሰናብታ ወደ ቤተሰቦቿ መመለሷን በስፍራው ተገኝቶ ላነጋገራት ገልጻለች።

የአብረኸት ህመም መጥናት ከምትወደው መከላከያ ቢለያትም ከጁንታው ዕይታ ግን መሰወር አልቻለችም። በጠላ ንግድ የሚተዳደሩትን እናቷን እያገዘች ኑሮን ብትቀጥልም፤ የጁንታው አባላት የአብረኸትን ወታደርነት ያውቁ ነበርና የጁንታውን ታጣቂ እንድትቀላቀል በእናቷ በኩል ግፊት ማድረግ ጀመሩ።

ጁንታው የአብረኸትን እናት ሌት ተቀን በማስፈራራታቸው ልጃቸውን ሳይወዱ በግድ ለታጣቂው አስረከቡ፤ አብረኸትም ቤተሰቦቼን ለአደጋ ከማጋልጥ በሚል ታጣቂውን ተቀላቀለች።
“ሌላ ስራ በቀላሉ ማግኘት ስላልቻልኩና ጫናውና ማስፈራሪያው ሲበዛብኝ ታጣቂውን ተቀላቀልኩ። የቤተሰቡ አባላት ሰባት ነን ፤ አባቴ በህይወት የለም፡፡ እናቴ ብቻዋን ነው ጠላ ሽጣ ያሳደገችኝ፡፡ እሷን ለማገዝ ስልም ነው ወደዚህ የገባሁት” ስትልም ነው የታጣቂው አባል የሆነችበትን አጋጣሚ የምታስታውሰው።

አብረኸት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ እየወሰዱት ባለው ህግ የማስከበር እርምጃ ላይ እጇን የሰጠችው አንድም ጥይት ሳትተኩስ መሆኑን ትናገራለች፤ “150 ጥይት ተስጥቶኝ አንድም ጥይት ሳልተኩስ ነው እጄን የሰጠሁኝ። ምክንያቱም በዚህ ውጊያ አላምንበትም። እየሞተ ያለውም የደሀው ልጅ ነው። እጄን ከሰጠሁ በሁዋላም ቢሆን ሶስት ቀን ሙሉ የሰራዊቱ አባላት ከሚበሉትና ከሚጠጡት እያካፈሉኝ ቆይቻለሁ።

በትግራይ ክልል በየአካባቢው ያለው ወጣት ተገዶ ወደ ግዳጅ እንዲገባ ተደርጓል የምትለው ወጣቷ፤ ስልጠና የሚሰጠውም የይድረስ ይድረስ መሆኑን አልሸሸገችም፤ “ለአጭር ጊዜ ክላሽ እንዴት እንደሚፈታና እንደሚገጠም፣ ኢላማ እንዴት እንደሚመታ አሳይተው ብቻ ነው ወደ ጦርነት የሚማግዷቸው፡፡ ይህ ደግሞ የህወሓት አመራሮች ለትግራይ እናቶችም ሆነ ወጣቶች ደንታ እንደሌላቸውና የራሳቸውን የስልጣን ጥም ለማርካት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ያሳያል” ነው ያለችው አብረኸት፡፡

“የህወሓት አመራሮች፤ የትግራይን ህዝብ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እንደሚጠላው፣ የትም ሄደው በሰላም መኖር እንደማይችሉ አድርገው ወጣቱንንም ሆነ ህጻናትን ጭምር ይሰብካሉ። ሁሉም የትግራይ ህዝብ የዚህ አይነት አስተሳብ ስላለውና ህወሓትን ስለሚፈራ የሚሉትን ለማድረግ ይገደዳል። ይህ ሰላም የማይወድ ድርጅት ውጤት ለማያመጣ ነገር ወጣቱን እያስፈጀ ነው” ብላላች አብረኸት።

የህወሓት ጁንታ ወጣቱን መስዋዕት የሚያስከፍሉት የማይሆን ነገር እየሞሉት፣ እያስገደዱትና፣ በገንዘብም እያታለሉት ጭምር መሆኑን አብረኸት ተናግራለቸረ።

የትግራይ ህዝብ መከላከያን እንዲወጋ አይፈልግም፤ ምክንያቱም መካላከያ የትግራይ ህዝብን ደህንነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ ትምህርት ቤት እየሰራ፣ ጤና ጣቢያ እየገነባ የኖረ ወገን ነው፤ የምትለው አብረኸት፤ “ወርቅ ለአበደረ ጠጠር እንዲሉ እኛን አታለው እንደ ቤተሰብ የምናየውን መከላከያ ሰራዊትን እንድንወጋ አድርገውናል” ያለችው በከፍተኛ ጸጸት ውስጥ ሆና ነው።

“የህወሓት ቡድን እንደሚለው መከላከያ እኛን ቢጠላን ኖሮ እንዴት ትግራይን ይጠብቃታል” ስትልም ትጠይቃለች። “እኛ ምንግዜም ኢትዮጵያዊ ነን፤ አጸያፊ ስራ እስካልሰራን ድረስ ህዝቡ ዝም ብሎ አይጠላንም፡፡ በመሆኑም የትግራይ ወጣቶች ዓላማ የሌለው ጦርነት ውስጥ መግባት የለባቸውም። ለመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን በመስጠት በሰላም መኖር ይኖርባቸዋል” ስትል ሀሳቧን ቋጭታለች።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ
በዌብሳይት
በቴሌግራም
ትዊተር

Report Page