*/

*/

From

ስለ ደቂቀ እስጢፋኖስ አቋም… ባለቺን መነጽር፣እናነጻጽር፤4ቱን አንጻር!
ክፍል-2

2.6 እውን ደቂቀ እስጢፋኖስ መጎንበስ ያለበት ሰላምታ አይሰጡም?ለታቦት አይሰግዱም ነበር?!

ፕ/ር ጌታቸው በገጽ 29 ደቂቀ እስጢፋኖስ ‹‹ስግደትን ከአምልኮ ጋር ስላያያዙት ከሰው ጋር ሰላምታ ሲሰጣጡ እንኳ አንገታቸውን ሰበር አያደርጉም ነበር ›› ይሉናል፡፡በገጽ 100 ኅዳግ እንዲሁ ደቂቀ እስጢፋኖስ ለታቦት ስለመስገድ ያላቸውን አመለካከት ‹‹ከመስቀል ጋራ ካመሳሰሉት ለታቦት እንደማይሰግዱ መገመት ይቻላል›› ሲሉ በእኔ እምነት አሳሳች ግምት ይሰነዝራሉ፡፡የተረጎሙት ገድል ግን በገጽ 199 ለንጉሥ ዘርዐያዕቆብ መስገድን እንደ ባዕድ አምልኮ የሚመለከቱት ደቂቀ እስጢፋኖስ በገጽ 128 ለተአምረ ማርያም እጅ ሲነሱ፣በገጽ 232 እና 274 ቤ/ክ ሲሳለሙና አበምኔታቸውን እጅ ሲነሱት እናገኛቸዋለን፡፡የእነሱ እጅ መንሳት መጎንበስ የሌለበት ነው እንዳይባል ደቂቀ እስጢፋኖሳዊው አባ ዕዝራ እና የማኅበረ-እስጢፋኖስ አለቃ ሲገናኙ የነበረው የእጅ መነሳሳት አይነት ‹‹ያዕቆብ ያባቱን እጆች እንደሳመ ‹አጎንብሶ› የአባቱን እጅ ሳመ›› በሚል ተገልጹዋል(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.310)፡፡ፕ/ር ጌታቸው ግን በመግቢያቸው ያስቀመጡት መደምደሚያ እንዳይፈርስባቸው በሚያስመስል መልኩ ‹‹መጎንበስ›› ያለበትን የአባ ዕዝራ ስግደት በኅዳግ ማስታወሻ ይሞግቱታል--‹‹ማጎንበስ ጀመሩ›› በሚል ስሜት!ታቦትና ደቂቀ እስጢፋኖስ ስላላቸው ግንኙነት ወረድ ብዬ የተወሰኑ ማስረጃዎችን ከገድላቸው አቀርባለሁ፡፡ፕ/ር ጌታቸው በገጽ 100 ኅዳግ የከፈቷትን የጥርጣሬ መስኮት ለመዝጋት ያህል ግን የአባ ዕዝራን ቃል ልዋስ፤‹‹‹አንተ (እግዘኢአብሔር) እንደረዳኸንና እንዳስደሰትከን ጠላቶቻችን ይዩ እና ይፈሩ› (መዝ 85 ቁ 17)አለ፡፡እንደዚህ ብሎ ሰገደ፤ታቦቶቹንም እጅ ነሣ››(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.308) የሚል ንባብ መኖሩን ጠቁሜ ብቻ ልለፍ፡፡

2.7 እውን የደቂቀ እስጢፋኖስ ስራዎች በንጽጽር የእመቤታችንን ስም እምብዛም አያነሱም?!

አባ እስጢፋኖስ ለተከታዮቹ በምሳሌያዊ መንገድ ቃለ-ምዕዳን ሲያስተላልፍ ‹‹…እስራኤልን ለበዓሉ ዕለት በብዙ መግለጫ ጋበዛቸው፡፡የግብዣው ጊዜ ሲደርስ በአስደናቂ መገለጥ ያለሰው ዘር ከንጽሕት ድንግል የዳዊት ልጅ ሰው ሆኖ ከዓለም በፊት ያዘጋጃትን ምክሩን ፈጸማት›› ይላል (ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.86)፡፡ተርጓሚው ፕ/ር ጌታቸው ደግሞ በኅዳግ ማስታወሻ ቁጥር 97 ‹‹ከዘመኑ የቤተክርስቲያን ስነ ጽሑፍ ጋራ ሲተያይ በእስጢፋኖሳውያን ዘንድ የማርያም ስም ብዙም አይታይም›› ይላሉ፡፡በቀደመው ንባቤ ይሕን የፕ/ር መደምደሚያ በየዋህነት እንዳለ ተቀብዬ አንጸባርቄው ነበር፡፡እየቆየ ግን መደምደሚያቸውን እጠረጥረው ጀመር፡፡ስጠረጥር ለማነጻጸር ተነሳሁ፡፡እድሜ ለዳንኤል ክብረት ‹‹አራቱ ኃያላን›› መጽሐፍ!አነጻጸርኩት!እሳቸው ካሉት የተቃረነ መደምደሚያ ላይ ደረስኩ!ላሳይ….

(2.7.1) በአባ አኖሬዎስ ገድል ውስጥ በእኔ ፍለጋ የእመቤታችን ስም በቀጥታ ሲነሳ ያገኘሁት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤እሱም ጸሎተ-ማርያምን ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ቁ 52 ጋራ በማስተባበር በገጽ 324፡፡በተቀረ በክርስትና ስም መጠሪያነት በገጽ 335 እና 340 የእመቤታችን ስም አገልግሎት ላይ ውሏል፤እንጂ የአባ አኖሬዎስ ገድል ስሟን ደጋገሞ ሲያነሳ አላጋጠመኝም፡፡

(2.7.2) በአባ ፊልጶስ ገድል (የፍልሰቱን ሳይጨምር) ውስጥ የእመቤታችን ስም በ6 አጋጣሚዎች መጠራቱን አንብቤያለሁ፡፡አባ ፊልጶስ ‹‹እመቤቴ ሆይ ልመናዬን ስሚኝ፣በዚችም ሰዓት ኃጥዕ ባሪያሽን ከተስፋዬ አታሳፍሪኝ…›› እያለ ጠበል በመርጨት በላዩ ላይ ባደረው መንፈስቅዱስ ኃይል ድውያንን ይፈውስ፤አጋንንትን ያወጣ እንደነበር ተጠቅሷል (ዳንኤል ክብረት፡ገ.203)፡፡በተጨማሪም በአባ ፊልጶስ ገድል ውስጥ በገጽ 220፣233፣252፣274 እና 278 የእመቤታችንን ስም እናገኘዋለን፡፡

(2.7.3) ወደ ደቂቀ እስጢፋኖስ ገድላት ስንመለስ ከገጽ 57 እስከ 115 በሚዘልቀው የአባ እስጢፋኖስ ገድል ውስጥ የእመቤታችን ስም በ4 አጋጣሚዎች በራሳቸው አነሳሽነት ቀጥታ በበጎ ተነስቶ እናገኘዋለን፡፡በገጽ 69 አባ እስጢፋኖስ በመንፈሳዊ ተመስጦ ውስጥ ሆኖ ‹‹ቅድስት ድንግል ማርያን እስኪያያትና ቃሏን እስኪሰማ ድረስ የተመሰገነች ሰማያዊ ምስጢር የሚያይ›› ሆኖ እንደነበር ተጽፏል፡፡በገጽ 85 እና 86 አባ እስጢፋኖስ ስለጌታ ሰው መሆን ሲያስተምር ‹‹ከንጽሕት ድንግል ተወለደ›› ይላል፡፡በገጽ 110 ፕ/ር በኅዳግ ማስታወሻ ቢገዳደሩትም የአባ እስጢፋኖስ አስኬማ የእመቤታችን ንጽሕና አምሳል ሆኖ ቀርቧል፡፡ፕር ግን ‹‹አርያም›› ለማለት ፈልጎ ነው ‹‹ማርያም›› ያለው ምክንያቱም አስኬማ በእመቤታችን አይመሰልም የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡እኔ እስከማውቀው በአብነት ተማሪ ቤት ያሉ ደቀመዛሙርትና ሕጋውያን (ባለትዳር) ቀሳውቅስትም ቆብ ያደርጋሉ፡፡ሆኖም እነሱ የሚያደርጉት ቆብ እንደ መነኰሳት ድፍን ሳይሆን መሀሉ ላይ በመሀል አናት ትይዩ ቀዳዳ ሊኖረው ግድ ነው፡፡የመነኰሳት አስኬማ ግን ከላይ ድፍን ነው፡፡የድንግልናቸው ምልክት ነው!የእመቤታችን ንጽሕና እና ድንግልና ከአባ እስጢፋኖስ ኅትምት(ድፍን) አስኬማ ጋር መነጻጸሩም በዚህ መንገድ ከእሷ ንጽህና ተነጻጽሮ ሊታይ ይገባል እንጂ በኅዳግ ማስታወሻ ደቂቀ እስጢፋኖስን ወደ ፀረ-ማርያም ካምፕ መጎተት ደግ አይደለም፡፡

(2.7.4) በገድለ አበው ወኃው ውስጥ ታሪካቸው በሰፈረው የእነ ንግስተማርያም ገድል የእመቤታችን ስም ከገጽ 146 እስከ 149 በስፋት ይነሳል፡፡እሱ በሰጊድ ዙሪያ በነበረው ክርክር ስለሆነ እንለፈው፡፡ነገር ግን በገጽ 140 ‹‹የአምላክ እናት ሆይ እነሆ ከምሕረትሽ ጥላ ስር ተደግፈናል፤በጭንቅ ጊዜ ልመናችንን አትናቂ›› የሚሉ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ተማጽኖዎች ልቦናችንን ያንሰፈስፉታል፡፡በገጽ 152 እና 154 ‹‹አክሊለ-ምክሕነ--የትምክታችን አክሊል›› እያሉ ስሟን በውዳሴ ሲጠሩት ስንሰማ እንደነግጣለን፡፡ይሄ ማስረጃ 100 በማይሞሉ የገድላቱ ገጾች በዳሰሳ የተገኘ ነው፡፡ከዚህ አንጻር ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ‹‹ከዘመኑ የቤተክርስቲያን ስነ ጽሑፍ ጋራ ሲተያይ በእስጢፋኖሳውያን ዘንድ የማርያም ስም ብዙም አይታይም›› በሚል የደረሱበት መደምደሚያ ተጨባጭ ንጽጽር ተሠርቶ የቀረበ አልመስሎኝም!ቢያንስ የእመቤታችን ስም ከገድለ አባ አኖሬዎስና አባ ፊልጶስ ጋር ሲነጻጸር በደቂቀ እስጢፋኖስ ገድላት በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡በአባ ዕዝራ ገድል ውስጥማ ስለእመቤታችን ክብርና ውዳሴ ያለው ማስረጃ የትየለሌ!

(2.7.5) በዚህ ረገድ (በሰጊዱና በውግዘቱ ጉዳይ ልዩነት ቢኖረኝም) በእመቤታችንና ደቂቀ እስጢፋኖስ ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ዙሪያ መ/ር ካሕሳይ እንደሚባለው ደቂቀ እስጢፋኖስ ‹‹ፀረ-ማርያም›› እንዳልነበሩ ማሳያዎችን በመደርደር አስመስጋኝ ሥራ ሰርተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ከላይ የጠቀስኳቸውን ስሟን የሚያነሳሱ ድርሰቶቻቸውን፣አባ ገ/ማያም የተባለ የደቂቀ እስጢፋኖስ መነኵሴ ‹‹እኔ የማርያም ባሪያ ነኝ›› ማለቱን(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.156)፣የመሰረቷቸው ገዳማት ሁሉ በእመቤታችን ስም መሆናቸውን፣በጻፏቸው መጻሕፍት ሁሉ የምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል መኖሩን፣አንቀጸብርሃንና ውዳሴማርያም መድገማቸውን፣ወዘተ…በመጥቀስ ፀረ-ማርያም እንዳልሆኑ ተከራክረዋል (ካሕሳይ፡ገ.55)፡፡አባ እስጢፋኖስ ስለ እመቤታችንና ስለመስቀል የደረሰው 38 ገጽ ድርሰት ብለው ከድርሰቱ ቆንጥረው ያቀረቡልን በውብ የግእዝ ቋንቋ የተከሸኑ ምንባባት ምናልባት በትክክል የእሱ ስለመሆናቸውና በገድሉ ላይ ከተንጸባረቀው አቋሙ ጋር ስለመጣጣማቸው ተመሳክሮ የሚቀርብ ሰፋ ያለ ጥናት የሚፈልጉ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ድርሰቶቹ ግን ሲያምሩ! ግእዙ…ንህነሰ ኢኮነ ጸላእያነሃ ለማርያም…ብሎ ነው የሚጀምረው::እሱን ብዙዎች አንባቢዎቻች ለግእዝ ሩቅ ናቸው ብየ ስለምገምት አማርኛውን ብቻ ጥቂት ልጥቀስ፤‹‹….እኛ ከመጠራጠር የተነሳ ሰዎች እንደሚሉን የማርያም ጠላቶች አይደለንም፡፡ ቃላችንም አይደለም፤አይደለም፤አዎን፤አዎን ብቻ ነው፡፡እኛ ፊታችንን እያማተብን የድንግል ማርያም አገልጋዮች ነን፤ባሮቹዋም ነን፤ፊታችንን በስላሴ ስም እያማተብን አበሳችንን የሚደመስስ ስለወለደችልን እንሰግድላታለን፡፡…..እንዲህ እያልን እመ-ብርሃንን እናመሰግናታለን፡፡ አንቺን ከፍ እናደርግሻለን ፤በስብሐትና በውዳሴም እንሰግድልሻለን፡፡ ዓሳ ከውሃ ወጥቶ በየብስ ለመኖር እንዳይችል ነፍስ የተለየው ስጋም እንደማይንቀሳቀስ፣ከግንዱ የተቆረጠ እንጨትም እንደማያፈራና እንደሚደርቅ ክርስቶስን በወለደች ማርያም የማያምንም ከመጽሐፍ የተፋቀ (የተደመሰሰ) ነው፡፡›› ይሏታል ይሉናል (ካሕሳይ፡ገ.54)፡፡

2.8 እግረ መንገድ ገድላተ ደቂቀ እስጢፋኖስን ከዘመነኞቻቸው ጋራ እናነጻጽር!
ደቂቀ እስጢፋኖስ ከዘመናቸው ጋራ ተቀራራቢ በሆነ ወቅት ከተነሱ መስተጋድላን ጋራ ማነጻጸር ከጀመርን ተጋድሎአቸውን እና ክርክራቸውን ጥቂት ገፋ አድርገን በንጽጽር እንየው፡፡ንጽጽሩ በወቅቱ የነበረውን ጠንካራ ክርስቲያን የሆኑ ግን አምባገነን ነገሥታትና ከእነሱ ጋር ያበሩ የተባበሩ ካሕናተ ደብተራ ባንድ ወገን ሆነው፤በሌላው ወገን ደግሞ ጥብቅ የምንኵስና ሕይወት የሚከተሉ መነኮሳት ተሰልፈው ተጋድሎ ያደረጉበትን የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ታሪክ ለመረዳት ፍንጭ ይሰጠናል፡፡ንጽጽሩን እንቀጥል…

(2.8.1) አጼ አምደጽዮን ዕቁባት ማብዛት አመጣ፡፡ሦስት ሚስት አበጀ፡፡ካሕናተ-ደብተራም ድርጊቱን ከመንቀፍ ይልቅ ‹‹ይደልዎ›› ብለው አጸደቁለት፡፡እነ አባ ፊልጶስ ድርጊቱን ለማውገዝ ከበዓታቸው ገስግሰው ቤተ-መንግሥቱ ሲደርሱም ካሕናተ ደብተራ ስለንጉሡ ሆነው ይሞግቱለት ጀመር፡፡በተለይ ዘአማኑኤል የተባለው የካሕናተ-ደብተራ ወገን ሽንጡን ገትሮ ተከራከረለት--ለንጉሡ፡፡አባ ፊልጶስ ቁጣው ነደደ፡፡ማን ያቁመው!ዘአማኑኤልን ይተገትገው ጀመር፡፡እንዲህ እያለ ‹‹…ዘአማኑኤል ሦስት ሚስት በአንድ ጊዜ እንዲያገባ ለንጉሡ ታዟል አለ እንጂ ለሁሉም አላለም፤በዚህም እግዚአብሔርን ፊት የሚያይ፡፡ስለመንግሥቱ (ንጉሡን) የሚፈራ፤ድኻንም ስለድኻነቱ የተነሳ የሚንቅ አደረገው፡፡በዚህም በአምላካችን ላይ ዋሸ፡፡‹ለነገሥት ሦስት ሚስት ያገቡ ዘንድ ታዝዟል የሚለውን ከየት አገኘው?› ሕግ መሲሓዊት(ክርስቶሳዊት) ከተገለጠች በኋላ?ከመጽሐፈ-ኪዳን ነውን?ወይስ ከወንጌል፣ወይስ ከሐዋርያት መልእክት፣ወይስ ከእነርሱ ጋር ሱታፌ ካለው፣ልሳነ-እፍረትም ከተባለ ጳውሎስ ነውን?ከዲድስቅልያ ነው?ወይስ ከመጽሐፈ-ሲኖዶስ፣ቅድስት ቤተክርስቲያን ከተቀበለቻቸው፡፡…የጽድቅ ቃላትን ከበሚናገሩ መጻሕፍት ሁሉ ይኸንን ትእዛዝ ብንፈልግም አላገኘነውም፡፡…ከሐዲስና ከብሉይ ምስክር በዚህ ነገር ላይ እናመጣ ነበር፤ነገር ግን እንዳይረዝም ብለን ተውነው›› ይላል(ዳንኤል ክብረት፡ገ.268)፡፡በተመሳሳይ አባ እስጢፋኖስ አባ ሲኖዳ የተባለ ዓለማዊነትን የወደደ መነኵሴ ጋር በንጉሥ ዘርዐያዕቆብ የፍርድ አደባባይ ቀርበው ሲከራከሩ ለመነኰሳት ተብሎ የተለየ ሥርዓት አልተሠራም ባለው ጊዜ ‹‹…ምዕመናን በሚስቶቻቸው እንዲጸኑና ልጆቻቸውን በእውነት እንዲያሳድጉ፣ካሕናትም ለመኖሪያቸው አሥራትና በኵራት እንዲወስዱ አዟል›› ሲል ከአባ ፊልጶስ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ መጽሐፈ-ሲኖዶስን ጠቅሶ ይከራከረዋል (ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.89)፡፡

(2.8.2) ንጉሥ ሠይፈአርእድ አባ ፊልጶስን ‹‹እኔ ከማልገዛው ምድር ልትደርስ ትችላለህን?›› ባለው ጊዜ ሲመልስ ‹‹እኔስ ምድር የአንተ ሳትሆን የእግዚአብሔር እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ነገር ግን አባቶቼ ሐዋርያትን እመስላቸው ዘንድ ስደትን እቀበላለሁ›› ይለዋል(ዳንኤል ክብረት፡ገ.292/293)፡፡ተመሳሳይ ጥያቄ ለአባ እስጢፋኖስ ከንጉሥ ዘርዐያዕቆብ ቀርቦለት ‹‹ቤተክርስቲያን የታነጸችው በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ እንጅ በምድር ንጉሦች ላይ አይደለም፡፡ስለዚህ ሞገዶች በማያናውጹዋት ክርስቶስ በገነባልን ቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ እንኖራለን›› ሲል ይመልስለታል(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.110)፡፡

(2.8.3) አባ ፊልጶስ ከሠይፈአርእድ ‹‹የቤተክርስቲያን ሹማምንት ሁሉ ከእኔ ጋር ተባበሩ፤አንተ ብቻ ትእዛዜን ሳትቀበል ቀረህ›› የሚል ቁጣ ደርሶበት ነበር፡፡የአባ ፊልጶስ ምላሽ ግን ‹‹ፈርቼ ሕጉን ከሻርኩማ የመጀመሪያው ገድሌን በከንቱ አደረግሁት፡፡…ዕርፍ ይዞ ወደኋላ የሚያርስ የለም [ሉቃስ 9 ቁ 62]›› የሚል ነበር (ዳንኤል ክብረት፡ገ.291)፡፡በዚሁ መንገድ ለአባ እስጢፋኖስ ከካሕናተ-ደብተራ ጥያቄ ቀርቦለት ሲመልስ ‹‹…ጌታ ሕይወትን ስለመውረስ ለጠየቀው ባለጸጋ ‹ፍጹም ለመሆን ከፈለግህ ሂድና ንብረትህን ሁሉ ሸጠህ ለድኻ ሰጥተህ ና ተከተለኝ› [ማቴ 19 ቁ 21] እንዳለው ቅዱስ ወንጌል ምስክሬ ነው፡፡…ደግሞ ዕርፍ ይዞ ወደኋላ የሚሄድ የለም፤ምክንያቱም መንግስተ-ሰማያት ቀጥታ ናት [ሉቃስ 9 ቁ 62]›› ይላል(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.89)፡፡በደቂቀ እስጢፋኖስ ገድል ውስጥ ንግሥተማርያምን የመሳሰሉ ጠንካራ መነኰሳዪያት እንደምናገኘው ሁሉ በአባ ፊልጶስ ገድል ውስጥም መክብዩና ኦርኒ የተባሉ ጽኑኣት መነኰሳይዪያትን እናገኛለን (ዳንኤል ክብረት፡ገ.287)፡፡

(2.8.4) በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ የደረሰውን ሰቆቃ እና እጅግ ኢ-ሰብአዊ ቅጣት ምን ጥቅስና አመክንዮ ብንደረድር አሳማኝ ልናደርገው አንችልም፡፡በመጠናቸው እነሱ ላይ ከደረሱት ጋራ ይተካከላሉ ባይባሉም እጅግ መሪር ሊባሉ የሚችሉ ቅጣቶች በዚያው ዘመን አካባቢ በተነሱ የመካከለኛው ዘመን መነኰሳት ላይም ደርሷል--ዳንኤል ክብረት በ‹‹አራቱ ኃያላን›› ከገጽ 92-102 እንደተረከው፡፡ለምሳሌ፡- አባ ፊልጶስ በጅራፍ ተገርፈዋል፣በሽመል ተወቅተዋል፣እርቃናቸውን ተደርገው የጺማቸውና የኀፍረተ-ሥጋቸው ጸጉር ተነጭቷል፣ታስረዋል፣ተግዘዋል፣ከታሰሩ በኋላ እንደ ሮማውያን ግላዲያተር የተራቡ ውሾች ተለቀውባቸዋል፡፡እነ አባ በጸሎተሚካኤል፣አኖሬዎስ፣አሮን፣ተክለሐዋርያት፣ሣሙኤል ዘደብረ ወገግ የነገሥታቱ የጭካኔ በትሮች አርፈውባቸዋል፡፡የእነ አባ ቀውስጦስ የንጉሥ አምደጽዮን የሥጋ ዘመዶች መሆን ተግሳጽ በንጉሡ ላይ በሰነዘሩ ጊዜ 400 ግርፋት ከመቀበል፣ጺማቸውን ከመነጨት፣እጅና እግራቸው እንደ ድንኳን አውታር ተወጥሮ ከመታሰር እና በመጨረሻም ጎናቸውን በጦር ተወግተው የሰማዕትነትን ጽዋ ከመጎንጨት አላዳናቸውም፡፡

(2.8.5) ሞትን በሚመለከት ንጽጽር ብንሰራ ደቂቀ እስጢፋኖስ በገጽ 221 እንደሚነግሩን በ‹‹ድብፀር››(አጼ ዘርዐያዕቆብ) እጅ ብቻ 1004 ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን በንጉሡ የግድያ ትእዛዝና በግዞት አልቀዋል፡፡በተመሳሳይ 128 የአባ አኖሬዎስ ተከታዮች፣500 የአቡነ አሮን ተከታዮችና በሺህ የሚቆጠሩ የአባ ፊልጶስ ተከታዮች በአጼ አምደጽዮንና ሰይፈአርእድ ዘመን ሲያልቁ እናገኛለን(ዳንኤል ክብረት፡ገ.98፣287 እና 351)፡፡የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ክርስትና እንደዚህ ነበረ፡፡ነገሥታቱ ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ትንሣኤ እጅግ በመጣጣራቸው፣አምልኮ-ባዕድን በማክሰማቸው፣ክርስቲያኑ ግዛት በሙስሊም ጅሀዲስቶች እንዳይዋጥ ከውጭም ከውስጥም ጠንክረው በመከላከላቸው እናደንቃቸዋለን፡፡የምግባር ጉድለታቸውንና ኢ-ክርስቲያናዊ ቅጣታቸውን ስናይ ደግሞ እንሸማቀቃለን፡፡የሆነ ሆኖ ነገሥታቱ ካለፉ በኋላ እነ አባ አኖሬዎስ፣ፊልጶስ፣አሮን፣ወዘተ ያለልዩነት በቅድስና ሲጠሩ ደቂቀ እስጢፋኖስን በሚመለከት ግን ለምን የተለያየ ሐሳብ ተራመደ?ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡የእኔን አቋም ቀደም ሲል ስለውግዘትና ስግደት ሳነሳ ያንጸባረቅሁ ይመስለኛል፡፡

(2.8.6) በአጠቃላይ በገድል አጻጻፍ ደረጃ የክርክሩ ጭብጥ ከመለያየቱ በቀር በደቂቀ እስጢፋኖስና በአራቱ ኃያላን ያለው አቀራረብ የተመሳሰለ ሆኖ ይታየኛል፡፡ደጋግመው የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች ማቴ 5 ቁ 10፣ማቴ 10 ቁ 39፣ማቴ 16 ቁ 24፣ማቴ 19 ቁ 21፣ማቴ 22 ቁ 2፣ሉቃ 9 ቁ 23፣ሉቃ 9 ቁ 62፣መጽሐፈ-ሲኖዶስና ዲድስቅልያ እንዲሁም የቅዱስ ዳዊት መዝሙራትና የነአባ እንጦንስና መቃርስ የምናኔ ተጋድሎዎች ናቸው፡፡እነዚህ ጥቅሶች በቤተክርስቲያን ሊቃውንት ስለምናኔ እና ምንኵስና በአስረጂነት ሲቀርቡ የምናውቃቸው ናቸው (መ/ብ አድማሱ ጀንበሬ፡ገ.44-46)፡፡ገድላቸውን የሚጽፉበትን ምክንያትም የገድለ አበው ወአኃው ግድል ጸሐፊ በገጽ 221 ሲናገር ‹‹ይኸንን ለኛና ከኛ በኋላ ለሚመጡ ማስታወሻ እንዲሆን እንዳገኘነው ጻፍነው›› ያለ ሲሆን በተመሳሳይ የአባ አኖሬዎስ ገድል ጸሐፊም ‹‹በምስክርነት ካልጻፍንና ካልተናገርን የሚመጣ ትውልድ በምን ያውቃል?...እኛማ እንሞታለን፤እንጣላለንም፡፡የሰው ልጅ ሁሉ እንደሳር ያልፋልና›› (ዳንኤል ክብረት፡ገ.325) ሲል ገድሉን ለመጻፍ ያነሳሳውን ምክንያት ይገልጻል፡፡ለማወቅ የሚጓጓው ሀገራዊ ትውልድ አነሰ እንጂ ገድላትን የመጻፍ ዐላማቸውስ ተጋድሏቸውን ለመጪው ትውልድ ለማሳወቅ ነበር!

2.9 በውኑ ደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፍቅዱስ ብቻ--Bible Only ባዮች ነበሩን?

(2.9.1) በአባ እስጢፋኖስ ገድል ገጽ 65 እንዲህ የሚል ቃል ሰፍሯል፤‹‹ነፍሱን በአምላክ መጻሕፍት ምስከራ በቆመች በጌታ ሥምሪት አሠማራት፡፡ከሰው ጠባይ የሚድንበት ውሳኔዎቻቸውንም መጠበቅ ያዘ፡፡ቅዱሱ ለሚሠራው ሁሉ አስቀድሞ አበምኔቱን ይጠይቅና ፈቃድ ይወስዳል፡፡›› ፕ/ር ጌታቸው ይሕን የገድሉን ጸሐፊ ገለጻ ሲተረጉሙት ‹‹Fundamentalist የሚባሉት እንደሚያደርጉት መጽሐፍ የሚለውን ቃል በቃል መጠበቅና እንደትእዛዞቹ መሄድ ጀመሩ ማለት ነው›› ይሉናል(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.65፣ኅዳግ ቁ.35)፡፡ Fundamentalist የሚባሉት እንደ አባ እስጢፋኖስ ‹‹ዕርፍ ይዞ ወደኋላ የሚያርስ የለም›› በሚል እጅግ የጠበቀ የምንኵስና ሕይወት ስለመከተላቸው፣81ዱ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ፍና-ሐዋርያትንና አሰረ-አበውን ስለመከተላቸው፣በአበምኔት ፈቃድ ስለማደራቸው ግን ፕ/ር አልነገሩንም፤እኛም አላነበብንም፡፡

(2.9.2) አባ እስጢፋኖስ ‹‹ሰንበታትንና ዓላትን በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ እንደተጻፈ እያከበራችሁ…የሐዲስና ብሉይ…ምስከራ ለመጠበቅ የተዘጋጃችሁ ሁኑ›› በማለት ከነባሩ ትውፊትና ቁጥሩ ከ81ዱ ቅዱሳት መጻሕፍት ከሆነው መጽሐፈ-ሲኖዶስ ጠቅሶ ሲያስተምር ፕ/ር ጌታቸው በኅዳግ ማስታወሻቸው ‹‹አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቹ መጽሐፈ-ሲኖዶስን ከተቀበሉ ቅዳሜንም ያከብራሉ፤ገድሉም ይመሰክራል፡፡በመጽሐፈ-ሲኖዶስ ያልተዘረዘሩትን መጻሕፍት ግን በሕግ ደረጃ የሚቀበሉ አይመስልም፡፡›› ሲሉ ለደቂቀ እስጢፋኖስ በመጽሐፋቸው መግቢያ የሰጡትን ሉተራዊ ተዛምዶ ላለማናጋት የሚጥሩ መስለው ይታያሉ(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.77፤ኅዳግ ማስታወሻ ቁጥር 74)፡፡በወጉ በዓል የሚያከብርና መጽሐፈ-ሲኖዶስን የሚቀበል ሉተራዊ ፕ/ር ዐይተው የሚያውቁ ከሆነ መልካም ነው!መጻሕፍትን በሕግ ደረጃ ስለመቀበል ከላይ በተራ ቁጥር 2.8.1 ከሰፈረው የአባ ፊልጶስ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ኦርቶዶክሳውያን አባቶችን እንኳንስ የሕግ መጻሕፍት በሚባሉት 81ዱ እና በሌሎች አዋልድ መጻሕፍት መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ይቅርና ሐዲስና ብሉይ ያላቸውን አንጻራዊ ሥልጣንም ‹ምሳሌያዊት› እና ‹አማናዊት›፣‹ብሉይ›ና ሐዲስ፣‹የተሻረች›ና ‹ፍጽምት› ሕግ እያሉ የክብራቸውን ደረጃ ደርድረው ተረድተው ነው የሚያስቀምጡት፡፡

(2.9.3) ፕ/ር በቦሩ ሜዳ ንጉሥ ዘርዐያዕቆብ የደረሰው መስተበቁዕ ዘማርያም ኑፋቄ አለበት ተብሎ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንዲስማማ ተደርጎ መስተካከሉን ነግረውናል፡፡እኛም በዚሁ ጉባኤ ሦስት-ልደት ባዮች ተአምረማርያምን ለክርክራቸው ጠቅሰው ሲያቀርቡ ከ81ዱ ካልሆነ በቀር ለነገረ-ሃይማኖት መከራከሪያ ተአምረማርያም ሊጠቀስ እንደማይገባ በአጼ ዮሐንስ ተነግሯቸው መረታታቸውን አንብበናል--ቅሉ ይሕ አባባል የመጻሕፍትን ደረጃ ከመጠቆም በቀር ተአምረማርያም ለማነወር እንዳልተነገረ ብናውቅም(አቡነ ጎርጎርዮስ፡ገ.73)፡፡ስለዚህ በኢኦተቤክ ከ81ዱ መጻሕፍት ውጭ ‹‹የሕግ መጽሐፍ›› ተብሎ መጽሐፍ ቅዱስን አክሎ እና ተካክሎ የሚጠቀስ መጽሐፍ እንደሌለ መረዳት አያዳግተንም፡፡ፕ/ር ግን በመግቢያቸው ካስቀመጡዋት መደምደሚያ ፈቀቅ ሊሉ አይሹም፡፡ደቂቀ እስጢፋኖስን Bible Only ባዮች ለማስመሰል የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ለነገሩ ለመጽሐፋቸው ርእስም ያለነገር ‹‹በሕግ አምላክ›› የምትል ተቀጽላ አላበጁለትም!ያ!ባልከፋ፡፡ደቂቀ እስጢፋኖስን አብዮታውያን ለማድረግ ሲሉ ቤ/ክ እንዲያው አዋልድን እና መጽሐፍ ቅዱስን ለይታ የማታውቅ የሚያስመስል አቀራረባቸው ግን ቅር ያሰኛል፡፡እኔ እንዲያ ተሰምቶኝ ቅር ብሎኛል!

(2.9.4) በሕገ-መጻሕፍት አጠቃቀስ ረገድ ደቂቀ እስጢፋኖስ በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች መስተጋድላን አበውም ሆነ በዘርዐያዕቆብ ወገን ከተሰለፉት ተከራካሪዎች የተለየ አቋም ነበራቸው ለማለት የሚያስችል ተጨባጭ መረጃ የለም፡፡ለምሳሌ ንጉሡ አባ እስጢፋኖስን ሲጠራው ‹‹ላገኝሕና ‹በሕጉ ፈለግ› መሰረት ሁሉንም ለእግዚአብሔር ላስተካክል እወዳለሁ›› ብሎት ነበር(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.92)፡፡በገጽ 147 ንጉሡ ‹‹የኢትዮጵያን ሃይማኖት ለምን ለሁለት ትከፍላላችሁ?አሁንም እኛ ዘንድ የጎደለውን እናንተ እየሞላችሁ፤እናንተ ዘንድ የጎደለውን እኛ እየሞላን ‹በመጻሕፍት ይወሰን›…›› ብሎ ነው የሰበሰባቸው፡፡ዘርዐያዕቆብን በተግባሩ እንወቅሰዋለን እንጂ እነሱ ያልተቀበሉን ሕግ ጠቅሷል ብለን አናማውም፡፡ከፋም ለማም እሱም ‹‹ኑና በሕጉ ተዳኙ›› ነው ያለው፡፡እንደሕጉ ሄዷል/አልሄደም ሌላ ጥያቄ ነው!በጥሪው መሰረት እየቀረቡ ባደረጓቸው ክርክሮች 2ቱም ወጎኖች በዋናነት 81ዱን መጽሐፍቅዱስ ነው የሚጠቀሙት፡፡ማሳያ ካስፈለገ በገጽ 88፣185፣186 እና ከ294-297 ያሉ ሞቃት ክርክሮችንና ምልልሶችን መመልከት ይቻላል፡፡በመጽሐፍ ቅዱስና በአዋልድ አጠቃቀስ ዙሪያ የተነሳ አለመግባባት በገድላቱ ውስጥ አ…ል…ተ…መ…ዘ…ገ…በ…ም፡፡ባልተመዘገበ ቃል ብይን መስጠት ደግሞ አያስኬድም፡፡ስለዚህ ፕ/ር ደቂቀ እስጢፋኖስ ከFundamentalist ወገን እንደነበሩ አድርገው ያቀረቡትን ማስታወሻ የምቀበለው አይደለም፡፡ለማንኛውም ‹‹መፍቀሬ-ደቂቀ-እስጢፋኖስ›› ብለን ረጅሙን የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ሓሳብ ለመሞገት የተንደፋደፍንበትን አማተራዊ ርእስ በዚሁ ቋጭተን ወደሌላ ዕይታ ተሻገርን!

3. እንቅስቃሴውን ፖለቲካዊ ትርጕም መስጠት!

ገና ስጀምር የደቂቀ እስጢፋኖስ ታሪክ ‹‹ለትርጉም የተመቸ ነው›› ብዬ ነበር፡፡የሆነውም እንዲያ ነው፡፡የደቂቀ እስጢፋኖስን ሰቆቃ መብዛት ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ በወቅቱ የገነገነውን ዓለማዊነት የተጫነውን ምንኵስና ለመታገል ከተደረገው ጥረት ጋር ያይዙታል፤መ/ር ካሕሳይ ከንጉሡ አምባገነንነትና መፍቀሬ-ሥልጣን መሆን ጋራ ያቆራኙታል፤ፕ/ር መስፍን ከንግግር ነጻነት ነፋጊነትና ከማሰብ ነጻነት ጋራ ያይዙታል፤Hagos G የተባሉ ጸሐፊ ‹‹The Dekike Estifanos: Towards an Ethiopian Critical theory›› በሚል ርእስ ከሐገራዊ ኂስ(በእሳቸው ቋንቋ ‹‹ሐተታ››) ጋር አገናዝበው ለእኔ የጣፈጠኝ ውብና በተለየ አንጻር የቀረበ ዳሰሳ አድርገውበታል፡፡አቡነ ጳውሎስና Krzysztof Piotr BŁAśEWICZ የተባሉ በደቂቀ እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ ዙሪያ 2ኛ ዲግሪያቸውን የሰሩ ፖሊሽ (ፖላንዳዊ) የቲዎሊጂ ሊቅም የደቂቀ እስጢፋኖስን መሳደድ ወደ ፖለቲካዊ ትርጓሜው አድልተው ዐይተውታል፡፡የሁሉንም ሐሰባ ማስፈር ባይቻልም የተወሰኑትን እናቅርባቸው፡፡

(3.1) <<Filsata: The Feast of the Assumption of the Virgin Mary and the Mariological tradition of the Ethiopian Orthodox Tewahido Church>> በተሰኘ የዶክትሬት ማሙያ ጥናታቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ <<…It seems that much of their opposition was politically motivated,directed at the claims of the Solomonic dynasty>>ሲሉ የደቂቀ እስጢፋኖስን እንቅስቃሴ ሰሎሞናዊ ንግሥናን ከመቀበልና ካለመቀበል ጋር አያይዘውታል(አቡነ ጳውሎስ፡ገ.262)፡፡ደቂቀ እስጢፋኖስ ሰጥ ለጥ ብለው ለንጉሡ አለመገዛታቸው ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አንድነትን መሰረት ያደረገ ግዛት ለመመስረት ቆርጦ በተነሳው አጼ ዘርዐያዕቆብ አደባባይ ቅጣታቸውን እንዳከበደባቸው ይከራከራሉ(ዝኒ ከማሁ፡ገ.263)፡፡መ/ር ካሕሳይም ይሄንኑ ሐሳብ ያጠናክራሉ(ካሕሳይ፡ገ.52)፡፡አቡነ ጳውሎስ ከመ/ር ካሕሳይ ለየት የሚሉት ደቂቀ እስጢፋኖስ የቀደምት አይሑዳውያን-ክርስቲያኖች ቅሪቶች ሳይሆኑ አይቀርም የሚለውን የቤተ-እስራኤል ታሪክ ጸሐፊዎች አስተሳሰብ ወደመቀበል በማዘንበላቸው ነው፡፡እሱን ወረድ ብዬ እመለስበታለሁ፡፡

(3.2) Krzysztof Piotr BŁAśEWICZ በተመሳሳይ የደቂቀ እስጢፋኖስ መከራ መብዛት ከሃይማኖታዊ መነሻው ይልቅ በካሕናተ-ደብተራ የብልጽግና ኑሮ ላይ ባነሱት ተቃውሞ፣ከሚከተሉት በራስ የድካም ፍሬ የማደር የጠበቀ የምንኵስና ሕይወት፣ከጥብቅ የመጽሐፍ ንባብቸውና ያነበቡትን ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት፣ከበዐታቸው እየወጡ በመስበካቸውና ለንጉሡ ባለመስገዳቸው ፖለቲካዊ ይዘት ሊኖረው እንደሚችል ሲተርኩ፤<<The persecution which they experienced were most likely caused by the fact that they refused to pay heed to the ruler reserving it exclusively for God and the unfavourable attitude of the fast becoming rich clergy for their reforming activities such as: living from the work of one’s own hands, sharing the crops with the ones in need, emphasis on study and observation of the laws of the Holy Scriptures, propagating their ideas beyond the walls of the monastery and charismatic personalities endowed upon them.>>( BŁAśEWICZ,p.42)ብለዋል፡፡

(3.3) በዚህ ጎራ ያለውን አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ መካድ ኢ-ፍትሐዊ ይሆንብኛል፡፡ከበርቴ ካሕናተ-ደብተራ በንጉሡ ዙሪያ መኖራቸው እውነት ነው፡፡ንጉሡ ለሥልጣኑ ያለው ቀናኢነት ልጆቹና ሚስቱ ላይ ሳይቀር ለማስጨከን የሚያስችለው ነበር፡፡ለንጉሥ ሰጊድ እንዲደረግ በይፋ ሕግ ያወጣውና ‹‹አንቱታ››ን ያመጣው እሱ መሆኑ ከዜናመዋዕሉ እና ከታሪክ መጻሕፍት እንረዳለን(ፍስሐ ያዜ፡ገ.252)፡፡በጊዜው ለደገኛው ክርስቲያን ንጉሣዊ አስተዳደር ተገዳዳሪ ከነበሩት ቆለኛ ሡልጣኔቶችና የቤተ-እስራኤላውያን መሳፍንት መነሳሳት አንጻር ንጉሡ ዙፋኑን ያለሃይማኖት አንድነት ማስጠበቅ እንደማይችል ስጋት አድሮበትም ሊሆን ይችላል፡፡ይህን በመሳሰሉ ምክንያቶች ደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ ክንዱን አበርትቶባቸው ሊሆን ይችላል ቢባል ተገቢ መላምት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ያም ሆኖ ግን የደቂቀ እስጢፋኖስ ‹‹ለመስቀልና ለእመቤታችን አንሰግድም›› የሚል አቋም ማስተባበያ እስካልተገኘለት ድረስ ሰቆቃቸው ‹‹ፖለቲካን ብቻ››መሰረት ያደረገ ነው ብሎ መደምደም ደግሞ ተአማኒ አይመስለኝም፡፡ጪስ ከሌለ እሳት አይኖርም!የልደት በዓል ‹‹ታሕሳስ 28 ወይስ ታሕሳስ 29?›› ነው መከበር ያለበት በሚል ክርክር ብቻ የብዙኃን ደም በፈሰሰባት ሀገር ለእመቤታችንና ለመስቀል አለመስገድ እንዲህ እንደዋዛ ይታለፋል ማለት ያውካል፡፡ስለዚህ በእኔ እምነት ለእመቤታችንና ለመስቀል ያለመስገዳቸው ጉዳይ መነሻ ሆኖ ከላይ የተጠቀሱት ፖለቲካዊና መደባዊ ጉዳዮች ስቃያቸውን በገድላቱና በተአምረ ማርያም በሰፈረው መልኩ እጅግ ኢ-ሰብአዊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

(3.4) ደቂቀ እስጢፋኖስ የንጉሡን ሰሎሞናዊ ዝርያ ስላልተቀበሉት ነው መከራ ያወረደባቸው የሚለው አነጋገር ከአባባል ባለፈ በገድሉ ሲንጸባርቅ አናየውም፡፡ነገሥታቱ እስራኤላዊ ዝርያ አለን የሚለውን ትምክህት ባይተውትም ወደኋላ ክርስትናቸውንም ትልቅ የሥልጣን ሕጋዊነት (Legitimacy) ማስገኛና መመኪያ አድርገውታል፡፡ሰሎሞናዊ ነገሥታት እስራኤላዊነተን ትተው በክርስትናቸው መኩራት ስለመጀመራቸው አጼ ይስሐቅ በገጽ 83 ከእስራኤል ስምና ከክርስትና ስም የቱ ይበልጣል ለሚለው ክርክር ‹‹እኛም ትምክህታችን በክርስትና ነው›› ሲል ለአባ እስጢፋኖስ ደግፎ አረጋግጡዋል፡፡ስለጉዳዩ ያለውን የቀደምት ሰሎሞናዊ ነገሥታት ስነ-ልቡና የበለጠ ማወቅ የፈለገ ደግሞ ክብረ ነገሥትን ከገጽ 106-108 ማንበብ ነው፡፡ወይም የዶናልድ ሌቪኒን ታላቋ ኢትዮጵያ ገጽ 90 መመልከት፡፡አሁን ወደ ሌላ ምልከታ…ስርዋጽ እናስገባ…

4. እንደስርዋጽ፡-ደቂቀ እስጢፋኖስ ነገሥታቱን በተለይ አጼ ዘርዐያዕቆብን እንዴት ያዩታል?

የታሪክ መዛግብትን ከደቂቀ እስጢፋኖስ ጋር አነጻጽረን ካየን ከአጼ ይስሀቅ (1406-1420) እስከ አጼ ናዖድ (1486-1500) ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታዊ ዙፋን 10 ነገሥታት ነግሠዋል፡፡ሆኖም ከነዚህ ውስጥ ከደቂቀ እስጢፋኖስ ጋር ስማቸው ተያይዞ በገድላቱ የተነሳው 4ቱ ብቻ ናቸው፡፡አጼ ይስሐቅና አጼ ናዖድን ገድላቱ በበጎ ያነሷቸዋል፡፡አጼ ዘርዐያዕቆብንና ልጁን አጼ በዕደማርያምን በመራር ቋንቋ ቅጽል የክፋት ስም አውጥተው ይጠሯቸዋል፡፡ጥቂት እንሂድበት!

(4.1) አባ እስጢፋኖስ ለመጀመሪያ ጊዜ አጼ ይስሐቅ ፊት ተከሶ በቀረበ ጊዜ ንጉሡን ሲመክረው ‹‹…መጽሐፍ ‹እንግዲህ ንጉሦች አስተውሉ፤መሬትን የምትገዟት ሁሉ ተገሰጹ፤ለእግዚአብሄር በፍርሃት ተገዙ› (መዝ 2 ቁ 10) ይላል፡፡…ለእግዚአብሄር መገዛት ማለት ሕጉን በመፈጸም ራስክን እየጠበቅህ ሕዝቡንም በእውነትና በትክክል ማስተዳደርና በቅዱስ ሲኖዶስ እንደተሠራው ሥርዓት ካሕናት መንጋውን በትክክል እንዲጠብቁ፣ሕዝቡም እንደተደነገገው ለእረኞቻቸው እንዲታዘዙ፣መነኵሴዎች ፍጹም ለመሆን ለሚፈልጉ ወንጌል እንዳዘዘው ራሳቸውም በሰጡት ቃል እንዲቆሙ ሁሉንም በየሥርዓቱ ማደራጀት ነው›› በማለት ስለተቋማዊ አደረጃጀት ንጉሡን ያሳስበዋል(ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.87)፡፡ንጉሡ በሃይማኖት ጉዳይ ጠልቆ እንዳይገባና ስለራሱ ክብርም መጨበቅ እንዳያበዛ ‹‹ንጉሥ ሆይ መንግሥትህን ለእግዚአብሔር አምላክ አገልግሎት አድርገው እንጂ ለራስህ ክብር አይሁን፤…እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ለመንፈሳውያን በመንፈስ፣ለሥጋውያን በሥጋ የሚኖሩበት ሕግ ለሁሉም አወጣ፡፡ከየወሰናቸው እንዳያልፉም ትእዛዝ ሰጠ›› እያለ በለዘብታ ይመክረዋል(ዝኒ ከማሁ፡ገ.93)፡፡

(4.2) አባ እስጢፋኖስ የንጉሥ ቃል ገደብ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ገደቡም የእግዚአብሔር ቃል ነው(ገ.81)፡፡ለመነኰሳት በሥጋዊ ፍርድ መደመር እርም ነው ብሎ ይከራከራል፡፡ለሥጋ ገዢዎች ግን መፍረድ እንደተፈቀደላቸው ያምናል፤ያም ቢሆን ታዲያ ‹‹በሕጉ መሰረት በእውነት ፍርድ ነው እንጂ [ከሕግ ውጭ] አይደለም(ማቴ 19 ቁ 25)››(ዝኒ ከማሁ፡ገ.93)፡፡እነዚህንና ከላይ ያነበብናትን ‹‹ለመንፈሳውያን በመንፈስ፣ለሥጋውያን በሥጋ የሚኖሩበት ሕግ ለሁሉም አወጣ፡፡ከየወሰናቸው እንዳያልፉም ትእዛዝ ሰጠ›› የምትል አነጋገር ስናይ ደቂቀ እስጢፋኖስ የሴኩላሪዝም ጽንሰ-ሐሳብ ሳይኖራቸው አይቀርም ብለን እንገምታለን፡፡በሌላ በኩል የአጼ ይስሐቅንና የአጼ ናዖድን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ፍርዶች በእነሱ ላይ መገፋትን ስላስቀሩ በአዎንታ ሲመለከታቿው እንታዘባለን፡፡ለንጉሡ ሥልጣን መደንገጊያና መገደቢያ ብለው የሚጠቅሱት መዝሙረ ዳዊትን፣ወንጌለ-ማቴዎስንና መጽሐፈ-ሲኖዶስን መሆኑም ጨርሰን የሴኩላሪዝም አራማጆች የሚል ቅጽል እንዳንሰጣቸው ይይዙናል፡፡ከካሕናተ-ደብተራ ጋራ ሲነጻጸሩ ግን የንጉሡ ሥልጣን በእግዚአብሔር ቃልም ቢሆን ሊገደብ እንደሚገባው፣መነኰሳት በዓለማዊ ፍርድ መደብለቅ እንደሌለባቸው፣ማኅበራዊ ግንኙነቱ ሁሉ በተደነገገለት የሥነ-ሥርዓት ሕግ መሰረት እንዲሆን ያላቸው አቋም ከዘመናቸው የተራመደ አስተሳሰብ እንደነበራቸው ሊያስቆጥርላቸው ይገባል፡፡የሰጊዷን ጉዳይ ሳንረሳ ንጉሡ በዚህ አስተሳሰብ ካልሄደ እንደንጉሥ ላያዩት እንደሚችሉ መገንዘብ እንችላለን፡፡

(4.3) ደቂቀ እስጢፋኖስ እስከመጨረሻው ድረስ ለንጉሥ ዘርዐያዕቆብ መስገድን እምቢ እንዳሉ ነው ያለፉት፡፡እጅ መንሳትና አምልኮ ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው አይመስለኝም፡፡እርስ በርስ እጅ ሲነሳሱ አይተናላ!የእሱ አባባልም ቢሆን ‹‹እኔን ለሰጣችሁ አምላክ ስገዱ›› አለ እንጅ ቃል በቃል ‹‹አምልኩኝ›› አላለም፡፡ይሄ የጠፋቸው አይመስለኝም፡፡እነሱ የማይሰግዱለት ‹‹በሕግ የማሠራ አምባገነን ነው››ብለው ስለሚያምኑ ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ማሳያ ላምጣ!በገጽ 185 ስለንጉሡ በነገረ-ፈጅነት የሚከራከሩት ካሕናተ-ደብተራ እና ደቂቀ እስጢፋኖስ ትንፋሽ የሚያቆምና የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች የተዥጎደጎዱበት አስደማሚ ክርክር ያደርጋሉ፡፡በክርክሩ ማኅል ከካሕናተ ደብተራ ወገን የሆነው ነገረ-ፈጅ ‹‹ለንጉሡ ልምን አትሰግዱም፤ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው አክብረውት የለምን?›› ሲል ላቀረበለት ጥያቄ ደቂቀ እስጢፋኖሳዊው ወንድም ሲመልስ ‹‹ንጉሡ በሕግ የሚሠራ ቢሆን እንደምትሉት እናከብረዋለን፤ከሕግ ውጭ የሚሠራ ከሆነ ግን መምዕላይ[Dictator] ነው›› ሲል የማይሰግዱለት ሕግ ተከትሎ ስለማይሠራ እንጅ የአክብሮት ስግደት(እጅ መንሳት) ስለተከለከለ እንዳልሆነ ልባቸው እንደሚያውቅ ይጠቁመናል፡፡በሌላ አጋጣሚ እንዲሁ አንድ የንጉሥ ዘርዐያዕቆብ ሰላይ ስለንጉሡ ክርስትና ያላቸውን አመለካከት ሲጠይቃቸው ‹‹ሕግ ከፈጸመ ክርስቲያን እንለዋለን፤እኛ እንደምናየው ከሆነ ግን አንተም ታየዋለህ›› ይሉታል፡፡እነሱ እንዴት እንደሚያዩት ለማወቅ ይህ ጥቅስ ከሰፈረበት መስመር ዝቅ ብለን ስናነብ ‹‹ከሕግ ውጭ መሆኑ እውነት ነው፤ንጉሥ አይደለም›› ሲሉት እናገኛለን(ገ.156)፡፡በእነሱ ዘመን-የቀደመ ግንዛቤ ከሕግ ውጭ የሆነ ንጉሥ ‹በስም› እንጂ ‹በገቢር› ንጉሥ አይደለም!What an early outstanding conceptualization of rule of law!ሕጓን እንዴት አድርገው በልተዋታል አያ!እጹብ!

(4.4) እንዲህም ሆኖ ደቂቀ እስጢፋኖስ ንጉሡንም ሆነ ስለንጉሡና በእሱ ዘመን ስለተላለፉባቸው ፍርዶችና ውግዘቶች አፈጻጸም የሚያሳድዷቸውን ኃይላት በጭካኔ፣በስግደትና ከንቱ ውዳሴ ፈላጊነት እንጂ በሃይማኖት ህጸጽ ሲከስሷቸው አናይም፡፡ሲወቅሷቸውም ‹‹አሁን ዐውቀዋል፤ተረድተዋል፤ተረድተውም መጽሐፍ እንዳለው ዕውሮች ሆኑ›› በማለት በአውቆ አጥፊነት ነው የሚወቅሷቸው (ገ.155)፡፡ቤተክርስቲያናቸውን ሲያቃጥሉባቸው እንኳ ‹‹የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን አጠፉብን፤ክርስቲያን ሆነው ሳለ በእሳት አቃጠሉት›› የሚል የትካዜና የብሶት ቋንቋ ይጠቀማሉ እንጂ የአሳዳጆቻቸውን ክርስትና አይክዱም፣አያነውሩም(ገ.256)፡፡በተረፈ አጼ ዘርዐያዕቆብንና ልጁን (አድማስ በፀር) እንኳንስ በእነሱ ላይ ስላደረሱት የጭካኔ ተግባር በ‹ደስክ› አማኞች ላይ ስለወሰዱት እርምጃ ሳይቀር እያነሱ ስለምግባራቸው ይዘልፏቸዋል(ገ.221)፡፡ያው እሱም በድርሰቶቹ በይሑዲነት እና በፀረ-ማርያምነት ያብጠለጥላቸዋል፡፡አንዳንድ ጎበዞችም የእሱን ክስ እንደወረደ ተቀብለው ደቂቀ እስጢፋኖስ ጋራ ለመዛመድ መከራቸውን ያያሉ፡፡ይቺን ጉዳይ ለብቻዋ በአዲስ ርእስ እንያት!

5. ስለደቂቀ እስጢፋኖስ አይሑዳውያንና ፕሮቴስታንት ጸሐፍት ያላቸው ዕይታ!

በእግዜር ስለማያምን ስሙን በዚህ ጽሑፍ የማንጠራለት ፈላስፋ እንዲህ አለ “The worst readers are those who behave like plundering troops: they take away a few things they can use, dirty and confound the remainder, and revile thewhole.” ምሬቱን እጋራዋለሁ!በገድል ጽንሰ-ሓሳብ የማያምኑ ሰዎች ከማያምኑበት ቅጽር ገብተው ጥቂት አርጩሜዎችን ቀጣጥፈው ከቀሰጡ በኋላ አርጩሜውን ተጠቅመው አርጩሜዎቹ ለምልመው የበቀሉባቸውን የግንድ ቅርንጫፎች እየጨፈጨፉ ስለዛፍ ቅርንጫፎ አላስፈላጊነት ሲሰብኩን እንገረማለን፡፡ይሕን ካልኩ በኋላ ወደ ይሑዲና ፕሮቴስታንት ጸሐፍቶቻችን ልመለስ--ስለደቂቀ እስጢፋኖስ ስለጻፉት!በገድል መጻፍ አስፈላጊነት ሳያምኑ ገድል ጠቅሰው ስለሚከራከሩት!

5.1 ደቂቀ እስጢፋኖስን እንደ ይሑዲ-ክርስቲያን?!

(5.1.1) የንጉሥ ዘርዐያዕቆብ ድርሰት ነው ተብሎ በሚታመነውና ንጉሡ ደቂቀ እስጢፋኖስን በ‹‹ይሑዲነት›› እና ‹‹ፀረ-ማርያም››ነት ፈርጆ ጽፎበታል በሚባለው ‹‹መጽሐፈ ብርሃን›› ዙሪያ ሒሳዊ ጽሑፍ እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም የጻፉት ታዋቂው አትዮጵያዊ-ይሑዲ(ቤተእስራኤላዊ) ፕ/ር ኤፍሬም ይስሐቅ በ15ኛ ክ/ዘ በሥላሴ የሦስትነት ጉዳይ ጥያቄ ያነሱ ዘሚካኤላውያንን በማየት፣በቀዳሚት ሰንበት አከባበር ዙሪያ ጥያቄ አንስተው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኘላቸውን እነ አባ ኤዎስጣቴዎስን በማጥናት፣መጀመሪያ አካባቢ በነበራቸው አቋም ለመስቀልና ለእመቤታችን መስገድን እምቢኝ ያሉትን እነ አባ እስጢፋኖስ በመጥቀስ ያለጥርጥር ሁሉም አይሑዳውያን-ክርስቲያኖች ነበሩ እያሉ ይጽፋሉ፡፡ኧረግ!ብንል ‹እንዲያው እመኑኝ አትጠራጠሩ› <<there is no doubt that the anti-trinitarian stand,the reverence of Saturday Sabbath,and the refusal to worship Mary and prostrate before the Cross were beliefs held in common by the Jewish Chiristian community>>ብለውን እርፍ (Ephraim Issac:p,69)

(5.1.2) በእርጋታቸው፣በአረጋዊነታቸውና በትሑት አቀራረባቸው የምወዳቸው ፕ/ር ኤፍሬም ይስሐቅ አልተችለውም!የዘርዐያዕቆብ ዜና-መዋዕል እና የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድላትም ይደግፉኛል፤ስለደቂቀ እስጢፋኖስ ይሑዲነት እርግጠኛ ነኝ፤ስሙኝ ልንገራችሁ፤<<…we now can confirm our original conjecture that the Stephanites formed part of the Ethiopian Jewish Chiristian community that strictly kept the Saturday Sabbath and the law,refusing to worship anyone except God…›› ይሉና የእመቤታችንና የቅዱስ መስቀል ክብር በንጉሥ ዳዊት በኮፕቲክ ቤ/ክ አማካይነት ተዋውቆ በአጼ ዘርዐያዕቆብ ዘመን ተቋማዊ ቅርጽና ይፋዊ ሥርዓት እንዲኖረው መደረጉን ይገልጻሉ (Ephraim Issac:p,69-71)፡፡እንደእሳቸው አዝማሚያ ከሆነ ‹ተሐድሶ› ያመጣው ዘርዐያዕቆብ ሲሆን ደቂቀ እስጢፋኖስ ግን ነባሩን አይሑዳዊ-ክርስትና ለማስጠበቅ የቆሙ ‹ወግ አጥባቂዎች› ናቸው፡፡

(5.1.3) የፕ/ር ኤፍሬም ይስሐቅን ጽሑፎች በምንጭነት የተጠቀሙት አባታችን ነፍሰኄር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም በጥናታቸው <<…they are denounced as ‘Jews’…they may indeed have been followers of older Jewish Chiristian beleifs in Ethiopia which the king wanted to abolish.>>ይላሉ--ዋናው የደቂቀ እስጢፋኖስ ግጭት መንስኤ ‹‹የሥልጣን ነው›› የሚለውን አቋማቸውን ሳይለቁ ‹‹ይሑዲ›› መሆናቸው ግጭቱን አባብሶት ይሆናል የሚል መላምት በማከል(አቡነ ጳውሎስ፡ገ.262)፡፡የአቡነ ጳውሎስ ጥናት የተሠራው በደርግ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1988 ዓ.ም በስደት አሜሪካ ሳሉ በመሆኑ በደቂቀ እስጢፋኖስ በኩል የነበረውን አቋም ገድሎቻቸውን አመሳክሮ ለማገናዘብ እክል ሳይገጥማቸው አልቀረም ብለን በመገመት በርኅራኄ ካላለፍናቸው በቀር ‹‹ደቂቀ እስጢፋኖስ አይሑዳውያን ነበሩ›› የሚለውን አቋም ሳይሞግቱ በማለፋቸው መውቀሳችን አይቀርም፡፡

(5.1.4) ዘርዐያዕቆብ ደቂቀ እስጢፋኖስን ‹‹አይሑዳውያን›› ማለቱ በነገረ-ሃይማኖት ደረጃ የአይሑዳውያንን የእምነት መርሆዎች ተቀብለዋል ለማለት ሳይሆን የክሕደታቸውን መጠን አጕልቶ ቅጣቱን ለማክበድ፣በሕዝብና አሕዛብ መካከል የተጠሉ ለማድረግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ይሑዲነት ከሐዲስኪዳን በኋላ ያለው ታሪኩ ከጌታ ስቅለት ጋር እየተያያዘ ስለሚተረክ በኦርቶዶክሳውያን ደራስያን ለበጎ ስያሜ እንደማይውል ይታወቃል፡፡ምናልባት በአጼ ዘርዐያዕቆብ ዘመን ሞሶሎኒ እና ሂትለር ቢኖሩ ኖሮ ንጉሡ ደቂቀ እስጢፋኖስን ‹‹ፋሺት›› እና ‹‹ናዚ›› ሊላቸው እንደሚችል መገመት ነው፡፡ለነገሩ እነሱም ስም ለማውጣት አልሰነፉም ከሰብእና አውርደው ‹‹ድብፀር›› እና ‹‹ዝራጐን›› ብለውታል፡፡እነሱ እንዲያ ስላሉት ግን ዘርዐያዕቆብ ጅብ ወይም ደራጎን ነው ብለን ራሳችንን አናቄልም፡፡ለዚህ ነው የእስራኤላውያኑ ጸሐፍት እና ኋላ የምመጣባቸው የፕሮቴስታንት ጸሐፍት መደምደሚያ የሚያስገርመኝ፡፡እንዴት ተከሳሽን በከሳሽ ቃል ብቻ እንበይናለን!ዘርዐያዕቆብ ‹‹አይሑዳውያን ብሎ ስለከሰሳቸው ‹‹አይሑዳውያን ሳይሆኑ አይቀሩም››፤በፀረ-ማርያምነት ስለተከሰሱ ‹‹ፕሮቴስታንት ሳይሆኑ አይቀሩም›› እየተባለ ሲጻፍ ስናይ እንግዲያማ ‹‹እነሱም እሱን አያ ጅቦ፤ዝራጎኑ ስላሉት ጅብና ደራጎን ሳይሆን አይቀርም›› እንደማለት፤ወይም በሉቃስ 3 ቁ 23 አይሑድ የጌታችን አባት እ/ሔር ወልድ መሆኑ ስላልተገለጸላቸው ‹‹የዮሴፍ ልጅ›› እንዳስመሰሉት ይመስልብናል፡፡

(5.1.5) ደግነቱ ይሑዲው የቤተ-እስራኤል ታሪክ ጸሐፊ STEVEN KAPLAN <<… the most common usage of the term ayhud in medieval Ethiopia was as a description of Christian groups viewed … as heretical. This usage was especially popular in the time of the Emperor Zar’a Ya’eqob, who sought to purge the Church of many of its dissident elements as part of his program of religious nationalism.>>ብሎ ካብራራ በኋላ ምሳሌ ሲያቀርብም አጼ ዘርዐያዕቆብ ደቂቀ እስጢፋኖስን ‹‹አይሑዳውያን›› ያላቸው ልክ የገዛ ልጁ ዙፋኑን ሊገለብጥ በሞከረበት ወቅት እምነት አጉዳይነቱን ለመግለጽ በ‹‹አይሑዳዊ››ነት በከሰሰበት መልኩ መሆኑን ይነግረናል፤እንዲህ ሲል <<His son Galawdeyos, for example, participated in a failed coup against Zar'a Ya'eqob. He and his fellow plotters, we are told, 'betrayed the king, breaking their oath which they swore to [him] that they would never revolt... Galawdeyos became a Jew, abandoning his Christianity and deny-ing Christ.’ Since Galawdeyos was a close ally of the Christian saint and holy man, Takla Hawaryat, there appears to be little question that his alleged 'Jewishness' was political in character.He certainly was not a 'Falasha'; nor were the Stephanite monks whom the same Emperor also condemned as Ayhud.>>( STEVEN KAPLAN:p,215)::

(5.1.6) STEVEN KAPLAN ያሰፈረው ፕ/ር ይሥሐቅ ላነሱትና አቡነ ጳውሎስ በቸልታ ላለፉት የደቂቀ እስጢፋኖስን እንቅስቃሴ ከ‹‹ከይሑዲ››ነት ጋር የሚያያዝ አተያይ በቂ ማስተባበያ ይመስለኛል፡፡በተረፈ ከሐዲስኪዳን ጋራ ያልተጣረሱ፣በግልጽ ያልተከለከሉና ከሐዲሱ ጋር ተጣጥመው የቀጠሉ የኦሪት ትውፊቶችን፣ሥርዓታትን፣የቤተመቅደስ መገልገያ ንዋየ-ቅድሳትን፣የአኗኗር ዘይቤዎችን፣የካሕናትና የደባትር የሲመት እና የአለባበስ ይትበሐሎችን የምንጠቃቅስ ከሆነ ደቂቀ እስጢፋኖስን ብቻ ሳይሆን መላዋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ወደ ‹‹አይሑዳዊ››ነት እንዳናወርዳት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡በደቂቀ እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ የገነኑት እነ አባ ዕዝራ የዘር ሐረጋቸውን ‹‹ከጽዮን ጋራ ከወጡ ከሌዊ ነገድ›› ተያይዞ ስለተተረከና (ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.283)፣አባ አበከረዙን የጳውሎስን 2ኛ ቆሮ 2 ቁ 11 ጠቅሶ ስለንጉሥ ዘርዐያዕቆብ ሲናገር‹‹እኔም እንደነሱ እብራዊ ነኝ›› ስላለ(ዝኒ ከማሁ፡ገ.276)፣ቀዳሚት ሰንበትን ስለሚያከብሩና ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ስለሚጓዙ(ዝኒ ከማሁ፡ገ.288 እና 289) ይሑዲ ነበሩ ለማለት መፋጠን፤በግልጽ በቅድስት ሥላሴ እንደሚያምኑ (ገ.289) እየተናገሩ፣ሰጊድንም ቢሆን መጀመሪያ ለመስቀልና ለእመቤታችን ለመስገድ ቢያወላውሉም ኋላ ከመስገዳቸውም በላይ ለሥሉስ ቅዱስ ስዕል ስላለመስገዳቸው ማስረጃ ባልቀረበበት እንዲሁም ከአይሑዳውያን በተለየ ቅዱሳት ስዕላትን በገድሎቻቸው በስፋት ማኖራቸው እየታወቀ አይሑዳውያን ነበሩ ማለት ተአማኒ አይመስለኝም፡፡

Report Page