*/

*/

From

“ህፃናትን ወደ ጦርነት መላክ” ሌላው ህገወጡ የትህነግ ቡድን ሊጠየቅበት የሚገባ ወንጀል

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 04/2013 ዓ.ም (አብመድ) ህፃናት የአንዲት ሃገር የወደፊት ተስፋ እና ሃብት ናቸው፤ በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ14 ዓመት እስከ 18 ዓመት ያሉ ልጆች ህፃን ወጣቶች ተብለው እንደሚጠሩ ከአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ተቀብላ ከፈረመቻቸው እና ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እና ስምምነቶች መካከል የህፃናት መብት ስምምነት እና የአፍሪካ ህፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ለህፃናት መብት ጥብቅና ከቆሙ እና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ድንጋጌዎች መካከልም ይገኛል፡፡ ሁሉም የህፃናት መብት እና ደኅንነት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች የሚሉትም ህፃናት የዳበረ ስነ ልቦና እና ጠንካራ አካላዊ ውቅር ስለሌላቸው የተለየ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው ነው፡፡

በትግራይ ክልል የትህነግ ጁንታ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት በሰሜን እዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ህፃናትን ወደ ጦርነት እየማገደ ነው፡፡ “ራሳቸውን የመጠበቅ አቅም ስለሌላቸው የቤተሰቦቻቸው፣ የማኅበረሰቡ እና የመንግስት ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የተባሉ ህፃናት ለትህነግ የማይረካ የጥፋት ፍላጎት ነፍጥ አንግበው እንዲዋጉ ከማድረግ በላይ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚበድል ተግባር የለም፡፡

የትህነግ ዘራፊ ቡድኖች የራሳቸውን ልጆች በዓለም አሉ የተባሉ ቅንጡ እና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ እና የተቀናጣ ኑሮ እንዲኖሩ እያደረጉ የሕዝቡን ልጆች ወደ ጦርነት መማገዳቸው ሌላው የከፋው ባሕሪያቸው ነው፡፡

ህገወጧ ህወሓት ነፍጥ አሸክማ ወደተለያዩ አውደ ውጊያዎች ካሰማራቻቸው እና በተለያየ ምክንያት እጃቸውን ሰጥተው ወደ አማራ ክልል ከገቡት ወታደሮች የበዙት ለውትድርና የበቃ እድሜ ላይ የደረሱ አይደሉም፡፡ ጉዳዩን አስመልክተን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የህፃናት መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ አሻግሬ ዘውዴን አነጋግረናቸዋል፡፡

“ህወሓት ለግጭቱ ያሰለፈቻቸው አብዛኞቹ ወታደሮች እድሜያቸው ለወታደርነት የሚበቃ እንዳልሆነ በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ከቀረቡት ምርኮኞች እና እጃቸውን ከሰጡት ወታደሮች አይተናል” ብለዋል አቶ አሻግሬ፤ ይህ ሀገሪቱ የፈረመቻቸውን እና የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶች የሚጥስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ድንጋጌ አንቀፅ 182 ህፃናትን ለባርነት፣ ለአደንዛዥ እፅ ዝውውር፣ በዝሙት ሥራዎች እና በጦርነት ላይ ማሰማራትን እንደሚከለክል በግልፅ ያመላክታል፡፡
ወታደርነት አንድ የሥራ መስክ ቢሆንም ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ድንጋጌ ዝቅተኛ የሥራ ቅጥር እድሜ መወሰን እንደሚገባ ስለሚደነግግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን እና ወጣቶችን ወደ ውትድርና ማስገባት የተከለከለ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ “ህፃናት በወላጆቻቸውም ቢሆን እንኳን ለማንኛውም ዓላማ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ በግልፅ ይደነግጋል” ሲሉ አቶ አሻግሬ አስረድተዋል፡፡

ህገወጧ ትህነግ ህፃናትን ወደ ጦርነት ያሰማራችበት መንገድ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን የጣሰ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ “ህፃናት በአንዲት ሃገር ውስጥ የተለየ መብት ባለቤቶች ናቸው” ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ወላጆች፣ ማኅበረሰቡ እና መንግስት የህፃናቱን መብት ማክበር እና ማስከበር ይኖርባቸዋል፡፡

እንደ አቶ አሻግሬ ማብራሪያ ወላጆች በተለያየ ምክንያት ልጆቻቸው ወደ ጦርነት እንዳይገቡ መከላከል አለባቸው፤ ከአቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ለህግ ጉዳዩን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ለህፃናት ጥበቃ የሚሆን ስርዓት እና ባህል መገንባት አለበት፡፡ የቀጣይዋን ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የሚወስኑ ህፃናትን ወደ ጦርነት መማገድ ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩን ይፋ በማድረግ የትህነግ ቡድን እንዲጠየቅበት ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ተመስገን ሲሳይ እንዳሉት በኢትዮጵያዊያን ልቦና ውቅር እና ልማድ መሰረት ህፃናትን እና ዐቅመ ደካሞችን ለጦርነት መመልመል ማህበረሰባዊ ቅቡልነት የለውም፡፡ የህግ ምሁሩ እንደሚሉት ሃገሪቱ ስራ ላይ የምታውላቸው ሁሉም ህጎች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ለውትድርና መመልመል እና ማሰማራት በህግ ያስጠይቃል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Report Page