*/

*/

From

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህግን የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ኮሚሽኑ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሦስት ቀናት ብቻ ባደረገው ፍተሻና ብርበራ 163 ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችና 1194 ጥይቶችን እንዲሁም ሌሎች ንብረቶችን መያዙን እና የህውሃት ጁንታ ቡድንን ተልዕኮ ተቀብለው ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 242 ተላላኪዎች ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል የስግብግብነት መንፈስ እና ሃገሪቱን እኔ ካልመራሁ ትፈራርሳለች በሚል ኋላቀር እሳቤ እንዳሰበው ሳይሳካለት የህልውናው ጀንበር የጠለቀችበት ከሃዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን የከተማችንን ፀጥታ ለማደፍረስ ልዩ ልዩ ሴራዎችን ሸርቦ ተላላኪዎቹን በማሰማራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ቡድኑ ህጋዊ የሆኑ ተቋማትን እና የንግድ ድርጅቶችን እንዲሁም ግለሰቦችን በተለይ ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያት ከፀጥታ አካላት የተቀነሱ እንዲሁም ያገኙት የነበረው ጥቅም በለውጡ ምክንያት የተቋረጠባቸው በኮንትሮባንድ ንግድ እና በሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በመጠቀም አዲስ አበባ ሁከት እና ስጋት ያንዣበበባት ከተማ እንድትሆን ለማድረግ የአቅሙን እየተፍጨረጨረ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ህዳር 3 ቀን 2013 ዓ/ም በሰጡት መግለጫ የፀጥታ አካላት የዚህን ቡድን እንቅስቃሴ እግር በእግር በመከታተል ጥቅምት 30 ፣ ህዳር 1 እና 2/2013 ዓ.ም ለሦስት ቀናት ባደረጉት ጥብቅ ፍተሻና ብርበራ፡-

18 የእጅ ቦንብ 485 ክላሽንኮብ ጠመንጃ 3 ሳይለንሰር 227 ልዩ ልዩ ሽጉጦች 4628 ልዩ ልዩ ጥይቶች ፣ 4 የጦር ሜዳ መነፅር 1 ጂፒስ(GPS) 2 ፀረ ተሸከርካሪ ፈንጂ ብዛቱ 74 ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት እንደተያዘ አስታውቀዋል፡፡

በድምሩ 744 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና 4628 የተለያዩ ጥይቶች ተይዞል፡፡

ኮሚሽነሩ አያይዘውም በተለይ ከሀገር መከላከለያ ጋር በተደረገው ኦፕሬሽን ስራ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ለህገወጥ ተልዕኮ ማስፈፀሚያ ሊውል የነበረ 115 ልዩ ልዩ የመገናኛ ሬዲዮኖች መያዙን ከተያዙት የእጅ ሬዲዮኖች መካከል 23 ለረጅም እርቀት ወይም በትከሻ የሚታዘሉ እንደሆኑና የተቀሩት 92 ደግሞ የእጅ መገናኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ 67 የስልክ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ የሚያችል መሳሪያ ፣ ከአንድ ግለሰብ ላይ 350 ሲም ካርዶች፣ በተለያዩ ተቋማት ስም የተቀረጹ 6 ማህተሞች ፣ አንድ ግለሰብ በተለያየ ስም ያወጣው 7 ፓስፖርቶቸ መገኘቱን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ከተማችንን ለመረበሽ ተልዕኮ ወስደው ሲንቀሣቀሱ የተገኙ 242 የህውሃት ተላላኪ ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተጣራበቸው መሆኑን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ ጠንካራ እንቅስቃሴና ክትትል በተለይ ደግሞ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን እያደረገ ያለው ድጋፍ ያስጨነቃቸው የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች በህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ በአዲስ አበባ የተለያዩ ስፍራዎች በቀላሉ የሚፈነዱና የሚቀጣጠሉ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን በመጣል ላይ መሆናቸውን ከኮሚሽነሩ ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዮ ቦታው አድዋ ድልድይ ተጥሎ የተገኘው ቦንብ ፈንድቶ በአንድ ሰው ላይ ያከተለውን ጉዳት በምሳሌነት ያነሱት ኮሚሽነሩ በሦስት ቀናት ብቻ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የተፈታቱና የተቆራረጡ ሁለት ክላሻን ኮፕ ጠመንጃዎች ፣ 90 የክላሽን ኮፕ ጥይት፣ አንድ የጦር ሜዳ መነፅር ፣ 5 ገጀራ ተጥለው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የፀጥታ አካሉ ባደረገው አሰሳ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን መያዙንና በሦስት ቀናት ብቻ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች ፣ የተለያዩ የቴሌኮም መገልገያ ቁሳቁሶች ፣ የመገናኛ ሬዲዮኖች መያዙ እንዲሁም ፀረ-ሰላም ሀይሉ ህጋዊ ድርጅቶችን ሽፋን በማድረግ መንቀሳቀሱ የጁንታው የተንኮል መረብ ምን ያክል የተወሳሰበ መሆኑን እና የስልጣን ጥመኛው የህውሃት ጁንታ ቡድን ከተማችንን ለማተራመስ ፤ ሰላሟን ለማድፍረስ ምን ያክል አቅዶ እየሰራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡

ከተማችን አዲስ አበባ ከህወሃት ተላላኪዎች እና የጥፋት ተልዕኮአቸውን ከሚደግፉ ርዝራዦቻቸው ሙሉ ለሙሉ ነፃ ሆናለች ማለት ባያስደፍርም የፀጥታ አካላት እና የህዝቡ ተደጋግፎ የመስራቱ ህብረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ እና ህብረተሰቡም ሆነ የፀጥታ አካላት ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት እንደሌለባቸው ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ የህወሃት ጀንበር መጥለቋ የሚያንገበግባቸው ጀሌዎች በከተማችን ወከባ ፣ ችግር እና ግርግር እንደተፈጠረ እንዲሁም ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት እንዳለ አድርገው ማስወራታቸውን ህብረተሰቡ ተግንዝቦ ለጥፋት ቡድኑ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ጆሮውን ሳይሰጥ ከፀጥታ አካሉ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ይገባዋል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም ተስፋ የቆረጡት እና መውጫ መግቢያ ያጡት የህወሃት የጥፋት መልዕክተኞች በየሜዳው የሚጥሏቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በነዋሪዎች ላይ ድንገተኛ ጉዳት እንዳያደርሱ በግልፅም ሆነ በስውር የጦር መሳሪያ ተጥሎ የተመለከተ ወይም የጦር መሳሪያ ሊሆን ይችላል ብሎ የጠረጠረ ማንኛውም ግለሰብ ከማንሳት እና ከመንካት ተቆጥቦ በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ አካል ማሳወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በከተማችን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን መረጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገልፀዋል፡፡

Report Page