*/

*/

From

በህወሃት የጥፋት ቡድን ከበባ ውስጥ የነበረው ሰራዊት ከከበባ በመውጣት መልሶ እያጠቃ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደፊት በመገስገስ ላይ ነው - ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ(ኤ ኤም ኤን) ህዳር 2፤2013
በህወሃት የጥፋት ቡድን ከበባ ውስጥ ገብቶ ለአምስት ቀናት ምግብና ውሃ ተከልክሎ የነበረው የሰሜን ዕዝ ጦር ከከበባ በመውጣት ራሱን መልሶ በማደራጀት እያጠቃ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደፊት በመገስገስ ላይ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

በጥፋት ቡድኑ ከበባ ውስጥ ገብቶ የነበረው 7ኛ ሜካናይዝድ፣ 8ኛ ሜካናይዝድ፣ 23ኛ ክፍለ ጦር፣ 11ኛ ክፍለ ጦር፣ 31ኛ ክፍለ ጦር፣ 20ኛ ክፍለ ጦር፣ 4ኛ ሜካናይዝድ፣ 5ኛ ሜካናይዝድ በሙሉ የሰሜን እዝ ሰራዊት እንደነበረ ለኢዜአ ገልጸዋል።

“ይህ ሰራዊት ለአራትና አምስት ቀናት ምግብና ውሃ ተከልክሎ፣ ራሱን በውሃ ጥም ውስጥ ሆኖ በፅናት የተከላከለ ጀግናና የመከላከያ ሰራዊታችን ሞዴል ሆኖ በመገኘቱ በራሴና በኢትዮዽያ ህዝብ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ” ብለዋል።

የሰራዊቱ ጀግንነትም ሲዘከር የሚኖር ገድል መሆኑን አስገንዝበው፤ “እውነተኛ የኢትዮዽያ ህዝብ ሰራዊት መሆናችሁን በተጨባጭ ስላስመሰከራችሁም ከፍተኛ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ” ብለዋል።

ሰራዊቱን ከከበባ ለማላቀቅ ከምስራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ ፈጥነው በመድረስ የሰሜን እዝን ለመታደግ ለቻሉት የሰራዊቱ አመራርና አባላት የ“እንኳን ደስ ያላችሁ” መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ በኋላ ቀሪው የሰራዊቱ ተልዕኮ እስካሁን ከተፈጸመው ተግባር አንጻር አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት ጀኔራል ብርሃኑ፤ ሰራዊቱ ይህንን በመረዳት ቀሪውን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ እንደሚወጣ ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል።

ሰራዊቱ ከከበባ በመውጣትና ራሱን መልሶ በማደራጀት ባለፉት ሁለትና ሶስት ቀናት ከዳንሻ ጀምሮ ሁመራ በሚገኘው ትርካን አየር ማረፊያ እንዲሁም ባዕከርን በማጥቃትና በመቆጣጠር 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦርን ከከበባ ማላቀቁን ተናግረዋል።

ከከበባ ከተላቀቀው 5ኛ ሜካናይዝድ ጋር በመሆንም ሁመራን ነፃ በማውጣት ሉግዲ፣ ማይካድራንና በረከትን ነፃ እንዳወጣ አመልክተዋል።

ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከሁመራ 60 ኪሎሜትር ወደ ምስራቅ ኢድሪስ በሚባል ቦታ ላይ የጥፋት ቡድኑን እየደመሰሰ እንደሚገኝ ያመለከቱት ጀኔራል ብርሃኑ፤ “ሰራዊታችን በተፈፀመበት ኢሰብዓዊ ድርጊት በመበሳጨቱ በከፍተኛ ወኔ፣ ጀግንነትና ተነሳሽነትም ሁሉንም ነገር ወደነበረበት ለመመለስና ከሃዲውን ቡድን በህግ ፊት ቀርቦ እንዲቀጣ ለማድረግ እየሰራ ነው” ብለዋል።

ሰራዊቱ የትግራይን ህዝብና የትግራይን የፀጥታ ሃይል ጭምር ነፃ ለማውጣት ግስጋሴውን ወደ ሽሬ መቀጠሉን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጠቁመዋል።

“ህገወጡ ጁንታ ህዝቡና የፀጥታ ሀይሉን እንደ ምሽግ ስለተጠቀመ፣ ህዝቡንና የፀጥታ ሀይሉን ከዚሁ ወንጀለኛ ቡድን በመነጠልና እሱኑ ኢላማ ያደረገ እንቅስቃሴ እየተካሄደም ይገኛል” ያሉት ጀኔራል ብርሃኑ፤ ህግ የማስከበሩን ስራ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ጁንታውን ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዳይጎዳ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ለጦርነት ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ላይ እያለ በህወሃት የጥፋት ቡድን ልዩ ሃይል አማካኝነት ጥቃት የተፈጸመበት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።

Report Page