*/

*/

From

ግለሰቧ በአማራ ክልል ሁለተኛ ጤና ጣቢያ አስገንበተው አስረክበዋል፤ ሦስተኛውን ለማስገንባትም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡

ባሕር ዳር፡ ህዳር 01/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአሜሪካ በጤና ባለሙያነት (ነርስነት) የሚሰሩት ሲስተር ሙሉሰው ያየህይራድ ከተሰማሩበት ሥራ በተጓዳኝ ትርፍ ጊዜያቸውን ለመልካም ተግባር የሚያውሉ ኢትዮጵያዊት ናቸው፡፡

ክሊኒክ አት ኤ ታይም( Clinic at a time) የሚባል የተራድኦ ፕሮጀክት አቋቁመዉ ለጤና ጣቢያዎች ድጋፍ በማድረግና የጤና ተቋም በማስገንባት አማራ ክልልን እየረዱ ይገኛሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ የጤና ክሊኒክ በማስገንባት በሕክምናው ዘርፍ ያለውን ችግር በሂደት መቅረፍ ነው፡፡

ሲስተር ሙሉሰው ፕሮጀክቱን የሚመሩት የኢትዮጵያን ባሕል በማስተዋወቅ እና በተጓዳኝ በሚያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ ዓመታዊ ኮንሰርት ያዘጋጃሉ፤ የኢትዮጵያን ባሕላዊ ምግብ አዘጋጅተው ይሸጣሉ፤ የኢትዮጵያን ባሕላዊ ቁሳቁሶች በጨረታ ለውጪ ሀገራት ዜጎች ይሸጣሉ፤ ልዩ ልዩ ሁነቶችን ያዘጋጃሉ፤ ለአሜሪካውያንም የእንጀራ አዘገጃጀት ሙያዊ ስልጠና ይሰጣሉ፡፡

ስለ ኢትዮጵያ እንጀራ አዘገጃጀት መጽሐፍ አዘጋጅተውም ለገበያ አቅርበዋል፡፡

በነዚህ ተግባራት በሚያገኙት ገንዘብ ደግሞ ጤና ተቋማትን በመገንባት ሀገራቸውን ይረዳሉ፡፡

ሲስተር ሙሉሰው ለዚህ በጎ ተግባር ያነሳሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ የተመለከቱት የሕክምና አሰጣጥ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩ እናቶች በወሊድ ጊዜ የሚደርስባቸውን እንግልት ሲስተር ሙሉሰው ያየህይራድ ጠቅሰዋል፡፡ አሁን የተሰማሩበት ሰናይ ተግባር በክልሉ የሚስተዋለውን የሕክምና አሰጣጥ ክፍተት በመሙላት ችግሩን እንደሚቀንስም ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ቢቸና ላይ ለእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት የሚውል ባለ 11 ክፍል ማዋለጃና ማረፊያ ክፍል አስገንብተው አስረክበዋል፡፡ ይህንም “በገጠራማው የክልሉ አካባቢዎች ያሉ እናቶች የወሊድ ጊዜያቸው ሲደርስ ወደ ጤና ጣቢያ ሄደው እንዲገለገሉ ያደርጋል፤ ከወሊድ በኋላም በቂ እረፍት እንዲያገኙ ያስችላል” ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለቢቸና ጤና ጣቢያ የሕሙማን ማረፊያና ካርድ ክፍል አስገንብተዋል፤ ጀኔሬተር፣ አልጋና የላብራቶሪ መሣሪያዎችንም አሟልተዋል፡፡

አሁን ደግሞ በዲማ ከተማ በ2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን ጤና ጣቢያ አጠናቅቀው አስረክበዋል፡፡ ባለ ስምንት ክፍል ብሎኮቹ በአንድ ዓመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብተው የተጠናቀቁት፡፡ ጤና ጣቢያው የእናቶች ማቆያ፣ የቅድመ ወሊድ ምርመራ፣ ማዋለጃ፣ ምርመራ ክፍል፣ የአስተዳደር ቢሮና የመድሃኒት ማከማቻን ያካትታል፡፡

የጤና ጣቢያው አሠሪ ኮሚቴ እንዳስታወቀው ጤና ጣቢያው የተሟላ ላቦራቶሪና አልጋ ተሟልቶለታል፡፡ ይህም በአካባቢው የሚኖሩ እናቶች ጤንነታቸው ሳይጓደል እንዲወልዱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል የኮሚቴው ጸሐፊ ሀብታም ታዬ፡፡

የዲማ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ባለሙያ አብደላ ሰዒድ ጤና ጣቢያው ወደ 26 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከሩቅ ቦታ ድረስ በመጓዝ ለሞት ይጋለጡ የነበሩ እናቶችን እንደሚታደግም ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡

ሲስተር ሙሉሰው የኮሮናቫይረስን በመከላከል፣ የተቸገሩና ተፈናቃዮችን በመርዳት እና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ዘርፎች ድጋፍ የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊት ናቸው፡፡ በተለይ ለጤና ተቋም ግንባታ ቁርጠኝነት አላቸው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ዘጌ ላይ አንድ ጤና ጣቢያ የማስገንባት እቅድ አላቸው፡፡ ይህም የወረቀት ሥራው መጠናቀቁንና ቦታ የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ሲስተር ሙሉሰው አመላክተዋል፡፡

የሕዝቡን ችግር ለመቅረፍ አቅም ያላቸው ሰዎች በግላቸውም ሆነ በቡድን በበጎ ተግባሩ በመሳተፍ ጤናማ ትውልድ የመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ
በዌብሳይት
በቴሌግራም
ትዊተር

Report Page