*/

*/

From

የሕወሓት "የድርድር" ታሪኮች!
--------------------------------------
(ጀሚል ይርጋ)

ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል "የሰሜን ዕዝን ከባባድ መሣሪያዎች ማርከን የክልላችን ኃይል እንዲታጠቅ አድርገናል፣ በጠላታችን ላይም እናዘንበዋለን።” የሚለው ግልፅ የሆነ፣ በገዛ ምላሳቸው የታመነና የሀገር ክህደት ተግባራቸውን ያወጀ ንግግራቸው ለዓለም ጆሮ ደርሶም እያለ፣ “ሠላም ይሆን ዘንድ ወደ ድርድር ይገባ !" የሚለው ለሀገር ከመጨነቅና በቀና ልቦና የሚሰነዘር ሀሳብ መሆኑ እርግጥ ነው። የጦርነትን አስቀያሚነት የሚገነዘብ ማንም "ሠላም፣ ሠላም” ማለቱም ተጠባቂ ነው። ግና ይህ የተለያዩ ወገኖቻችን የተቀደሰ ሐሳብ እውን ይሆን ዘንድ "የሕወሓት ችኮ ተፈጥሮና አቋሙ" የሚፈቅድ አይመስልም። ከድርጅቱ ልደት አንስቶ እያጣጣረ እስካለበት የአሁኑ ጊዜ ድረስ ያሳለፋቸውን “የድርድር ታሪኮቹ "ን ብናጤነው ይህን እውነታ የምንረዳው ይሆናል። እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብለን በጥቂቱ እናስታውሰው።

1) ሕወሓትና ድርድር በትግል ዘመን
------------------------------------------------

ከሕወሓት ቀድሞ በ1966 ዓም መገባደጃ ላይ የተመሠረተው “ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ” (ግገሓት) በትግራይ ውስጥ የትጥቅ ትግል ከሚያካሂዱ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነበር። ሆኖም ከዚህ ድርጅት በኋላ የተመሠረተው "ተሓሕት (ሕወሓት)" በክልሉ ውስጥ ለብቻው መስፈንን በመፈለግ "ግገሓት"ን የተለያዩ ውንጀላዎችን በመሰንዘር ይተነኩሰው ጀመር። በዚህ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ለመዋጋት በቅተዋል። ሆኖም "ይህ ሁኔታ እርስ በራሳችን ከመዳከም ውጪ አይፈይደንም" ብሎ ራሱ ሕወሓት ለድርድር ጠርቷቸው ከመግባባትም አልፎ ተዋሕዶ ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱ ከተነገረ በኋላ ሕወሓቶች የደስደስ ትልቅ የምግብና መጠጥ ግብዣ አድርገውላቸው እስከ ምሽት ሲዝናኑ ቆይተው የመኝታ ሰዓታቸው ደርሶ በተኙበት ባመኗቸውና ከአንድ አፈር በበቀሉት ሕወሓታውያን “ወንድሞቻቸው” በጥይት መገደላቸውን ራሳቸው የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ያመኑት ታሪክ ነው። ለዚህ ጭካኔን የተመላ ድርጊታቸው እንደ ምክንያት የሚያቀርቡትም “የትግራይ መሬት ከአንድ ድርጅት በላይ የመሸከም አቅም የለውም" የሚል መሰሪ አቋምን ነበር።

በተጨማሪም በአመለካከት የተለየን የውጪ አካል ብቻ ሳይሆን በራሷ በሕወሓት ውስጥ ይገኙ የነበሩትን ታጋዮች "የመሳፍንትና የፊውዳል ቤተሰቦች” ብለው በቤተሰባቸው ማንነት በመለየት በጅምላ ፈጅተዋቸዋል።

ከዚህም ውጪ በአመለካከት የተለዩአቸውን አረጋዊ በርሄንና ግደይ ዘርአፅዮንን "የድርጅቱ ጋንግሪኖች" ብለው ሲያስወግዷቸው፣ ተኽሉ ሐዋዝን ጨምሮ ሌሎች ታጋዮችን መረሸናቸውን በሕይወት ያሉ ነባር ታጋዮችና የድርጅቱን ታሪክ ያጠኑ ጸሐፊያን ሕወሓት ከራሱ ውጪ "የሌሎችን ዓይን አልይ" ለማለቱ እነዚህን መገለጫ ታሪኮቹን በምሳሌነት ይጠቅሷቸዋል።

2) ሕወሓትና "ድርድር"፣ ድሕረ-ትግል
--------------------------------------------------

ሀ) “ብሶት የወለደኝ ነኝ” ባዩ ሕወሓት ኢትዮዽያውያንን ብሶት በብሶት ለማድረግ ግንቦት 20/1983 ዓም አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ከተለያዩ ፓርቲዎች ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ተግዳሮቶች ገጥመውት ነበር። በዋነኝነት ከባድ ፈተና ተጋርጦበት የነበረውም ከፍተኛ ሠራዊት ከነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እንደነበርም የሚያስታውስ ያስታውሰዋል። በጊዜው ከኦነግ ጋር የነበረው ፖለቲካዊ ትግትግ በጉልበት እስከ መፈታተሽ የዘለቀ ነበር። በመሆኑም በበደኖ፣ አርባ ጉጉ፣ ኩርፋጨሌ፣ ወተር ወዘተ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ማኖ ያስነካችውንና በከረፋ ምግባሩ በራሱ እጅ ስሙን ያጠየመውን ኦነግ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ቀዳሚ መፍትሔ አድርጋ የወሰደችው የ"ድርድር" ማደንዘዣ መውጋት መሆኑን በማመን በኦቦ ሌንጮ ለታ ይመራ የነበረውን ይህን ድርጅት "ቅድመ-ሁኔታ" በማስቀመጥ ለ"ድርድር" ጋበዘችው። የተቀመጠለት ቅድመ-ሁኔታም "ሠራዊቱ ትጥቁን ሳይፈታ በተዘጋጀለት ካምፖች ማስገባት" ነበር ። ከላይ በተጠቀሱት ውንጀላዎችና በሕወሓት "ውጋት" መሆን ግራ ተጋብቶ የነበረው ኦነግም ይህን ቅድመ-ሁኔታ በመቀበል በቁጥር 20000 የሚጠጋ ሠራዊቱን ወደ ካምፕ አስገብቶ ለድርድር ተቀመጠ። ሆኖም "ድርድሩ" በተጀመረበት ምሽት በየካምፖቹ የሰፈረውን የኦነግ ሠራዊት የሕወሓት ታጋዮች ባልታሰበ ሁኔታ በመክበብ "ትጥቁን እንዲፈታ" አደረጉት። እምቢ ያሉት ውጊያ ገጥመው ሲገደሉ የተረፉት ደግሞ በዝዋይ ወኅኒ ቤት ውስጥ ያለፍርድ ለ20 ዓመታት ያህል ታስረዋል። ብዙዎቹም እዚያው የዝዋይ ወባ ሰለባ ሆነው አልቀዋል። ይህ አሳዛኝና ግፍ የተመላ እውነታ በ1980ዎቹና 90ዎቹ ለንባብ በቅተው በነበሩት "ኡርጂ" እና "ሰይፈ-ነበልባል" ጋዜጦች ላይ ተነቧል።

ለ) በሽግግር መንግሥቱ ዘመን ኢህአዴግን በመገዳደራቸው ምክንያት ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተደረጉትን ኢዴኃቅን ጨምሮ፣ ከሀገር የተባረሩት የኦነግ እና የሌሎች ድርጅቶች አመራሮች፣ በ1986 ዓም በተደረገላቸው "የጊዮን ሆቴል ብሔራዊ የእርቅ ጉባኤ" ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የውጪ ሀገራት አዲስ አበባ እንደደረሱ ከአውሮፕላን ማረፊያ በካቴና ተጠፍንገው ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት መወርወራቸው ሌላው አይረሴ የሕወሓት የ"ድርድር" ታሪክ ነው። በጊዜው ለእስር ከተዳረጉት መካከል የኢዴኃቁ አበራ የማነአብ፣ የኦነጎቹ ሌንጮ ለታና ኢብሳ ጉተማ ይገኙበታል። ሌንጮና ኢብሳ ብዙም ሳይቆዩ የተፈቱ ሲሆን አበራ የማነአብ ግን "የቀይ ሽብር ተዋናይ" ተብሎ ለረጅም ዓመታት ከታሰረ በሁዋላ ቢፈታም አስራ አምስት ቀናትን እንኳ ሳይቆይ ባደረበት ሕመም ምክንያት ሞቷል።

ሐ) የ1997 ዓም ምርጫ መጭበርበርን ተከትሎ ተቃዋሚዎቹ ቅንጅትና ኅብረት የጠሩት መሬትን ያንቀጠቅጣል ተብሎ የነበረው የመስከረም 15/1998 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ በቅሬታዎቹ ላይ "ውይይትና ድርድር" እስኪካሄድ ድረስ ለአንድ ወር ያህል እንዲራዘም ከኢህአዴግ የቀረበውን የጭንቀት ጥያቄ በአውሮፓ ኅብረት ተወካዩ ቲም ክላርክ አሸማጋይነት መለስ ዜናዊ በተገኘበት በተደረገው ማደንዘዣ "ድርድር" ተቃዋሚዎቹ ስምምነታቸውን በመግለፃቸውና በዚህም ምክንያት ኢሕአዴግ እፎይታ በማግኘቱ የሚጎነጉነውን ሴራ ጎንጉኖ ከጨረሰ በኋላ በጥቅምት 22/1998 ዓም የተፈጠረውን ረብሻ ሰበብ በማድረግ እንዴት "አዛ" ሲያደርጉት የነበሩትን የቅንጅት አመራሮች እንዴት ጉድ እንደሰራቸው መቼም የሚረሳ አይደለም። ለእስር ከተዳረጉ በኋላ በሽመልስ ከማል አቃቤ-ሕግነት በቀረበባችው "የሽብር፣ የሀገር ክህደት ወንጀልና ሕገ-መንግስትን የመናድ" ክስ አብዛኛዎቹ እድሜ ልክ እንዲከናነቡ አድርጓቸው ነበር፤ ከሁለት ዓመታት በኋላ በይቅርታ ተፈቱ እንጂ።

መ) ኢህአዴግ ከቀረጻቸው ፖሊሲዎች እና ከሚያራምዳቸው አቋሞቹ ላይ አንዲት ሳንቲ ሜትር ንቅንቅ የማይል መሆኑን ብዙ ማሳያዎች አሉ። የመሬትን ጉዳይ፣ የፌዴራሊዝምንና ወዘተ ጉዳዮችን "በኢህአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ … " እያለ የሀገሪቱን ጉዳዮች ሌላውን በማግለል በፓርቲው ርዕዮት ላይ ብቻ ሲቀነብብ የኖረ ሲፈጥረው የድርድር መንፈስ ያልፈጠረበት ችኮ ነው። ዛሬም የኢሕአዴግ ፈጣሪ የሆነው ሕወሓት እንደ ትናንቱና እንደ ትናንት ወዲያው ባለበት እንደተቸከለ አለ። ከችኮነቱ መላቀቂያውም ሞቱ ብቻ ይመስለኛል !!!

Report Page