*/
Fromየደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ለሀገራዊ ጥሪ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ---
ጥቂት የሕወሓት ቡድኖች ባደራጁት የፀረ-ሰላም ኃይል በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለመደገፍ በክልሉ በቂ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ነብዩ በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ዝግጅቱን አጠናቅቆ ሀገራዊ ጥሪ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ 103 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከዚህ ቀደም በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ ላይ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የ32 ንፁሃን ዜጎች ሕይወት ሲያልፍ በ13 ሰዎች ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ 14 የዞን እና የወረዳ አመራሮች 4 የፖሊስ አባላት 6 የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም 5 ሰዎች ደግሞ ከክልሉ ውጭ የሆኑና የእርስ በርስ ግጭት እንዲከሰት ተልዕኮ የወሰዱ ሰዎች መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ባለፉት 2 ሳምንታት ብቻ በክልሉ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የነበሩ 31 ክላሽንኮቭ፣ 4 ኋላቀር መሳሪያዎች እንዲሁም 7 ቱርክ ሠራሽ ሽጉጦች ከበርካታ ጥይቶች ጋር ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።
የእርስ በርስ እልቂት ለመፈጸም የተዘጋጁ 289 ገጀራዎችን ከአርባ ምንጭ ወደ ጂንካ ከተማ በማስገባት ላይ የነበሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኮሚሽነር ነብዩ ጠቁመዋል።
የክልሉ ኅብረተሰብ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ነቅቶ በመጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ኮሚሽነሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከደቡብ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።