*/

*/

From

[ቀይዋ ማርስ በጣም ቀልታ፣ ደምቃ የምታበራበት የመስከረም 26 አስደሳች ሌሊት]
✍️ በመ/ሐ/ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
💥 በእውነቱ ያሳለፍነው 2012 ዓ.ም. ግርዶሽን ጨምሮ የሚገርሙ ክስተቶች ያየንበት ዓመት ነበር፤ አሁን የያዝነው 2013 ዓ.ም. አስገራሚ የሥነ ፈለክ ክስተተቶች በደንብ የሚታዩበት ዓመት ነው፡፡ በተለይ በዚህ ሳምንት ከምናየው ደስ የሚል ክስተት ውስጥ ማግሰኞ መስከረም 26/ 2013 ዓ.ም. አራተኛዋ ቀይዋ ፕላኔት ማርስ በሰሜንም በደቡብም ንፍቀ ክበብ ላሉ በጣም ደምቃ ከምሽት ጀምሮ በተለይ ግን እኩለ ሌሊት ላይ ለመሬት በጣም ቀርባ የምትታይበት ነው፡፡

💥 እንደ ሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች በዚ መልኩ መቀራረብ የሚከሰተው ከ15 ዓመት በኋላ በ2035 ነው፡፡ ምናልባት ደመና ካለ፣ ዝናብ ከዘነበ የነገውን ድምቀቷን በዐይን ማየት ካልቻልን ከሁለት ዓመት በኋላ ሕዳር 29/ 2015 (ዲሴምበር 8/ 2022) ከመሬት በ38.6 ሚሊየን ማይልስ (62.07 ሚሊየን ኪሎ ሜትር) ቀርባ ትታያለችና ከሁለት ዓመት በኋላ ማየት ነው፡፡

💥 በማርስ አካል ላይ ባለው የብረት (Iron) ማዕድን ምክንያት ቀይዋ ኘላኔት በመባል የምትታወቀው ማርስ በጣም አስደናቂ ስትሆን የኤቨረስት ተራራን ሦስት እጥፍ ኦሊሞፐስ ሞንስ (Olympus Mons) የተባለው 25 ኪ.ሜ ከፍታ፤ ዲያሜትሩ 700 ኪ.ሜ የሆነ ተራራ አላት፡፡

💥 ሌላው ውጫዊ አካሏ ላይ የሚታየውና ቀልብን የሚስበው ገጽታዋ “ቫሌስ ማሪነሪስ” (Valles Marineris) የሚባለው ሸለቆዎች የሚበዙበት ተራራማ ሰንሰለት ነው፡፡ ይህ ማሪነር በተባለችውና ፎቶውን ስታነሣ በነበረችው መንኰራኲር የተሠየመው ሰንሰለታማ ቦታ 4,000 ኪ.ሜ ርዝመት፣ 100 ኪ.ሜ ስፋት እና 7 ኪ.ሜ ጥልቀት ያለው ሲሆን በማርስ መቀነት (equator) ላይ ተንጣሎ ይገኛል፡፡

💥 በተለይ ቤታችሁ ቴሌስኮፕ ያላችሁ በምሽቱ አየር ዘና እያላችሁ የማርስ ፓላር ካፕ እና እሳተ ገሞራውን እስከ ቅዳሜ እያያችሁ መደነቅ፣ መደመም ትችላላችሁ፡፡ እኔም የሥነ ፈለክ መመልከቻ መሣሪያዎቼን ወልወል ወልወል እያደረኩ ነው፡፡

💥 ቴሌስኮፕ የሌላችሁ ግን ቀይ ሆና ደምቃ ስለምትወጣ በዐይንም ስለምትታይ ድምቀቷን፣ ውበቷን እያያችሁ በተለይ ነገ ምሽት በምሥራቅ አቅጣጫ በማርስ መደነቅ ትችላላችሁ፡፡

💥 ሌላው በደቡብ አቅጣጫ ጐንና ጐን ደምቀው በዐይናችን የምናያቸው ሁለቱ ፕላኔቶች ጁፒተርና ሳተርን ታኅሣሥ 12/ 2013 ዓ.ም. (ዲሴምበር 21/ 2020) በጣም ተቀራርበው ገዝፈው በዐይን የሚታዩበት ክስተት አስገራሚው ሲሆን ያ ቀን የማያ ዘመን ቀመር ሙሉ በሙሉ የሚያበቃበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስገራሚ ጉዳይና ብዙ ጉዳዮች በውስጡ ስላለው ወደ ፊት በስፋት አቀርብላችኋለሁ፡፡

💥 እንደ እኔ በምሽት ሰማይን በመመልከት በሥነ ፈለክ ሰማያዊ አካላት መደነቅ ለምትፈልጉ ወዳጆቼ ለምሳሌ ያህል በዚህ በመስረም ወር በሰማይ ላይ ወቅታቸውን ጠብቀው የሚወጡ በዐይን የሚታዩ ሕብራተ ከዋክብትን፣ ፕላኔቶችን በደንብ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ዛሬም ወጣ ብላችሁ ብታዩ በምሥራቅ ደምቃ ቀልታ ወጥታለች።

💥 ለምሳሌ በኢትዮጵያ ያለን እንኳ ያለምንም ቴሌስኮፕ በዐይናችን ብቻ ከሕብራተ ከዋክብት መካከል በሰሜን አቅጣጫ በኢትዮጵያው ንጉሥ ሴፌውስ፣ በኢትዮጵያዋ ንግሥት ካሲዮፕያና በልዕልት አንድሮሜዳ የተሠየሙት ሕብራተ ከዋክብት እና ሌሎችም ከነቅርጻቸው ይታያሉ፡፡

💥 በደቡብ አቅጣጫ ኮሮና አውስትራሊስና ሌሎችም ይታያሉ፡፡ በምዕራብ አካባቢ እነ ሊብራ፣ ስኮርፕዮ እና ሌሎችም በዐይን ይታያሉ፡፡ በምሥራቅ እነ ሴተስ፣ አኳርየስ እና ሌሎችም ይታያሉ፡፡

💥 ከፕላኔቶች ደግሞ በዐይናችን በደቡብ አቅጣጫ ወደ ሰማይ ብናይ ከፕላኔቶች ጁፒተርና ሳተርን ጐንና ጐን ሆነው ይታያሉ፡፡ በምሥራቅ አቅጣጫ ደግሞ ቀይዋ ፕላኔት ማርስ ቀልታ በምሽት ላይ በደንብ ትታየናለች፡፡ ምናልባት እነዚህን መለየት እንድትችሉ Star Tracker የሚል አፕሊኬሽን ከፕሌይ ስቶር አውርዳችሁ ከነወጡበት አቅጣጫ ስለሚያሳያችሁ ተጠቀሙበት፡፡

💥ከመሬት ጋር በተቀራረበ 23 ዲግሪ መልኩ ማርስም በ25 ዲግሪ ማጋደሏና ይህም ወቅቶች እንዲፈራረቅባት ማድረጉ፤ እንደ መሬት በሯሷ ዘንግ አንድ ጊዜ በመሽከርከር 1.03 ቀን መፍጀቷ ደረቅ ወንዝ መኖሩና ይህም ከማርስ ውስጣዊ አካል ውስጥ ውሃ ሊኖር ይችላል ተብሎ መገመቱ ወደ ፊት የሰው ልጆች ሕይወት ቢመሠርቱባት ችግር አይኖርም የሚለው የሳይንሱ ሐሳብ የሰው ልጆች የወደፊት መኖሪያ ኘላኔታቸው ለመሆን አንድ አማራጭ ዓለም አድርጓታል፡፡

💥 ለመሬት ስትቀርብ 56 ሚሊዬን ኪ.ሜ፤ ስትርቅ ደግሞ 402 ሚሊየን ኪ.ሜ የምትርቀው ማርስ አሁንም የሰው ልጆችን ቀልብ እንደገዛች ናት፡፡ በ2020ዎቹ ተጨማሪ ሰው አልባ ጉዞዎች በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በቻይናም የታቀደ ሲሆን አሜሪካ በ2030ዎቹ ውስጥ የሰውን ልጅ ማርስ ላይ አሳርፋለሁ ስትል ባዘጋጀችው ፍኖተ ካርታዋ ላይ በግልጽ አስቀምጣለች፤ መሳካቱን አለመሳካቱን በጊዜው ማየት ነው።

💥 መጪው ጊዜ የሥነ ፈለክ ጊዜ ነውና በዚህ ጉዳይ ላይና በመጪዎቹ በሰማይ ላይ ስለሚከናወኑት እጅግ አስገራሚ ነገራት Dr. Rodas Tadese በሚለው የYou Tube ቻናሌ በዝርዝር የማቀርብላችሁ ሲሆን ዐዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የዩቲዩብ ቻናሉን ሰብስክራይብ በማድረግ ሰፊ ዕውቀትን መውሰድ ትችላላችሁ፤ ሊንኩ
ነው፡፡

💥በተረፈ ስለማርስ በስፋት ለማወቅ ከፈለጋችሁ “አንድሮሜዳ” መጽሐፍ ላይ ከገጽ 63-69 ማንበብ ትችላላችሁ፡፡
[እውቀት፣ እውነት፣ እምነት፣ አመክንዮ፣ ቀና አመለካከት ሰውን በጥበብ ያሳድጋሉ]

Report Page