☆☆

☆☆


ሰበር ዜና

የኦሮሚያ መጅሊስ አዳዲስ ሹመቶች በመስጠትና በአንዳንድ ት/ቤ እየተካሄደ ያለውን የሒጃብ ገፈፋ መቃወሙን ጨምሮ ባለ 10 ነጥብ መግለጫ አወጣ።


▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰
መስከረም 20/2013 ረቡዕ

የመጅሊስ ምርጫ በአስቸኳይ እንዲደረግ በአቋም መግለጫው ላይ ተጠይቋል!

የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ጉባዔውን በትላንትነው እለት በኦሮሚያ ባህል አዳራሽ ማድረጉ ይታወሳል። በዛሬው እለትም በዑማ ሆቴል ጉባዔውን አካሂዷል።

የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለ2 ቀን በፊንፊኔ ሲያካሄድ የቆየውን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በስኬት ካጠናቀቀ በኃላ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል፡፡ መጅሊሱ ለገጻችን የላከው ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል።

1. በጠቅላይ ምክር ቤቱ የቀረበዉን የ2012 ሪፖርት እንዲሁም የ2013 እቅድና በጀት በመገምገም በሙሉ ድምጽ አፅድቀናል። ህዝባችንና የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ሁሉ ለስኬታማነቱ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

2. ዛሬ የተሾሙትን የኡለማዎች፣ የምሁራን፣ የኢማሞችና ዳዒዊች፣ የወጣቶች፣ የኦዲትና እንስፔክሺን ሹመት ያፀደቅን ሲሆን ስራቸው ግብ አንዲደርስ ከጎናቸው እንቆማለን።

3. እኛ መጠሪያችን "ሙስሊሞች" የሚለው ሲሆን ከዚህ ሌላ ሊከፋፍለን ብሎ ጠላት የሚያወጣልን ማንኛውንም የክፍፍል ስም የማንቀበል መሆናችንን በድጋሚ እንገልፃለን። ሁሉንም ሙስሊም በአመለካከት ሳንለያያቸው በእኩልነት ለማገልገል ቃል እንገባለን።

4. የሙስሊሞችን የጋራ አንድነት ለማጠናከር እንደተስማማን ሁሉ ከሌሎች እምነት ተከታይ እንዲሁም ከብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋርም በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር አብረን ለመኖር ጠንክረን እንሰራለን።

5. የኦሮሚያ ከልል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኢትዮያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዉስጥ ባለው የአመራርነት ኮታ ውስጥ በሚመጥነዉ መልኩ በትክክል እንዲወከል እንጠይቃለን።

6. ከምክክር ውጪ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል ገደብ የለሽ የፌዴራል መጅሊስ ጣልቃ ገብነትን እንቃወማለን። ከእንዲህ ዓይነት ድርጊት እንዲቆጠብም እንጠይቃለን። የክልሉም ይሁን የዞን ተሿሚዎች በተዋረድ በምክር ቤቱ ጉባኤ ይሁንታ ያገኙትን እንጂ ለረዥም አመታት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ በደል ሲያደርሱ የነበሩትን የማንቀበል መሆኑን በሙሉ ድምፅ አረጋግጠናል።

7. ጠቅላላ የመጅሊስ ምርጫ እንዲደረግና እንዲሁም የኡለማዎች ስምምነት ሰነድና የመተዳደሪያ ደንብ ፀድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ እንሰራለን።

8. ከምንም በላይ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት እንሰራለን። መንግስትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶችና መላው ህብረተሰብ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የክልላችንን ሠላም ለማስጠበቅ ከሚመለከተው ሁሉ ጋር በመሆን የማዕከላዊ ሚናችንን በአግባቡ እንወጣለን፡፡

9. በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙትን የኢማሞችን ግድያ አጥብቀን እናወግዛለን። መንግስትም ይህንን ግድያ የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ለህግ እንዲያቀርብ አሁንም በድጋሚ እንጠይቃለን።

10. ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረውን የመጅሊስ ህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ አዋጅና እስላማዊ ባንክ ስለተፈቀደልን መንግስትን እጅግ እያመሰገንን አንድ አንድ ትምህርት ቤቶች ዉስጥ የሚደረገውን ሂጃብ የማስወለቅ ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን።

▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰▰

Report Page