...

...


የምኮራበት እንጂ የምቆጭበት ሥራ የለም›› አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ


ላለፉት ሁለት ዓመታት የአዲስ አበባ አስተዳደርን በምክትል ከንቲባነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። በአዲስ አበባ አስተዳደር በነበራቸው የሁለት ዓመት የቆይታ ጊዜ በመልካምም፣ በአሉታዊም መነጋገሪያ የነበሩ ናቸው። በቅርቡ በሚኒስትርነት ከተሾሙ በኋላ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሥልጣን ቆይታቸው ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ የመሬት ወረራና ሕገወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላን የተመለከተ ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል። በዚህም ምክንያት የሰሞኑ መነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል። ዮሐንስ አንበርብር ይህንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና በአሁኑ ወቅት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ከሆኑት ታከለ ኡማ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል።


ሪፖርተር፡- ጥያቄዬን ከአዲሱ ኃላፊነት ለመጀመር ያህል አንድ ጥያቄ አንስቼ ወደ ዋናው ጉዳይ አገባለሁ። አዲሱን የሚኒስትርነት ኃላፊነት እንዴት አገኙት?


አቶ ታከለ፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይሁን አስፈጻሚዎችን እንደገና ለማደራጀትና ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን እንዲሁም የትኩረት መስኮችን ሳያቸው፣ ለአገራችን የዕድገት ጉዞ ትልቅ ሚና የሚጫወት ተቋም ነው። ስለዚህም በጣም ጥሩ ሆኖ ነው ያገኘሁት።


ሪፖርተር፡- ላለፉት ሁለት ዓመታት በኃላፊነት ወይም በምክትል ከንቲባነት ካገለገሉበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በድንገት ነው የተነሱት? ወይም ከዚህ ኃላፊነት እንደሚነሱ አያውቁም ነበር? በተጨማሪም በመነሳታቸው ደስተኛ አይደሉም ይባላል። ስለዚህ ምን ይላሉ?


አቶ ታከለ፡- ብዙ ሊባል ይችላል። እውነታው ግን የተለየ ነው። ከአዲስ አበባ ኃላፊነቴ እንደምነሳና ወደ ሌላ ተልዕኮ እንደምሄድ ከሁለት ወራት በፊት አውቅ ነበር። ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ኃላፊነት የመጣሁበትን ወይም ኃላፊነት የተረከብኩበትን ሁለተኛ ዓመት ከሌሎች ባልደረቦች ጋር በዘከርንበት ዕለት ሥራ ለማስረከብ ዝግጁ ነበርኩ። ነገር ግን በፓርቲያችን በኩል ዝግጅቱን ስላልጨረሱ ነው እስከ ነሐሴ አጋማሽ በኃላፊነት ላይ የቆየሁት። ከኃላፊነት በመነሳቴ አልተከፋሁም፣ እንዲያውም ደስተኛ ነኝ ብል ይቀለኛል። ምክንያቱም እኔ የለውጡ የታሪክ ጉዞ አካል ነኝ። ከምክትል ከንቲባነት ኃላፊነት የተነሳሁትም በራሴ ፍላጎት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መልቀቂያ አቅርቤ ነው። እውነታው ይህ ነው። በነገራችን ላይ አንድ ኃላፊ እስከሚነሳ መጠበቅ የለበትም የሚል እምነት ያለኝ ሰው ነኝ። ይህንን እምነቴንም በተግባር ፈጽሜያለሁ።


ሪፖርተር፡- ስለዚህ የኃላፊነት ቦታ ለውጡን የጠበቁትና ቀድመው የሚያውቁት ነበር?


አቶ ታከለ፡- ምንም ጥርጥር የለውም። ስጠብቅ ስለነበር አዲስ አልሆነብኝም።


ሪፖርተር፡- እርስዎ ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነት ተነስተው በሚኒስትርነት መሾሜ ቀድሜ ያወቅኩትና የጠበቅኩት ነው ቢሉም፣ ጉዳዩ ትኩረት የሳበ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር። አንዳንዶች መነሳት አልነበረባቸውም ከተማዋን ጥሩ እየመሩ ነው ሲሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ በከተማዋ በነበረዎት ቆይታ በተለይም ከመሬት አስተዳደርና ከቤቶች ዕደላ ጋር የሚወቅስዎትም አሉ። ከተነሱ ከቀናት በኋላም ኢዜማ በከተማ አስተዳደሩ የመሬት አስተዳደርና የቤቶች ማስተላለፍ ሥነ ሥርዓት ላይ ጥናት አድርጎ ሰፊ የሆነ ሕገወጥነት ስለመኖሩ ማረጋገጡን የሚገልጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በዚህም እርስዎንና አስተዳደርዎን ወቅሷል። ለዚህ ምን ምላሽ አለዎት?


አቶ ታከለ፡- ይህንን ጥያቄ ካነሳህ አይቀር፣ ጥያቄና መልሱን እንደ ወረደ ቃል በቃል እንድትጽፈው እፈልጋለሁ። በሁለቱም ወገን የሚነሳው ጥያቄም ሆነ ሐሳብ ወይም ትችት የራሱ መነሻ አለው ብዬ አስባለሁ። ከምክትል ከንቲባነት መነሳት አልነበረበትም ስለሚሉ ወገኖች በምሳሌያዊ አነጋገር (Metaphorically) ላስረዳ። አንድ ትጉህ፣ ቅንና ታታሪ አርሶ አደር የእርሻ ወይም የወይን ማሳውን ያለ ዕረፍት ቀን ከሌት፣ ቁርና ሙቀት እየተፈራረቀበት ቤተሰቦቹንና የሥራ አጋሮቹን አስተባብሮ በጥንካሬና ብርታት ማሳውን አዘጋጅቶ መልካም ዘር ይዘራል። ይህንን ካደረገ በኋላ ሥራዬን ጨረስኩ ብሎ ማሳውን አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎ ተጠቃልሎ አይተኛም። ዘሩ ሳይበቅል በአዕዋፋት እንዳይለቀም፣ ቀበሮም የወይኑን ቦታ እንዳያጠፋው ይከለከላቸው ዘንድ ይተጋል። ዘሩ በቅሎ፣ ቡቃያ ሆኖ ፍሬው እስኪጐመራና የጠበቀውን ውጤት እስከሚያገኝም ድረስ እረፍት የለውም።


ባለፉት ሁለት ዓመት እንደ ቤተሰብ ከከተማችን ነዋሪዎች፣ የከተማችንን ዕድገት ከሚመኙ በአገር ውስጥም ከአገር ውጪ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጋር ያለ ዕረፍት ለከተማችን መልካም ሥራዎችን በጋራ ሠርተናል። ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይህ የተጀመረው መልካም ሥራ እንዲቀጥል፣ ፍሬ እንዲያፈራም ይፈልጋሉ። ስለዚህ ብዙ ዜጎች ቢቆይ በጋራ የጀመርናቸውን ጉዳዮች ወደ አንድ ደረጃ እንደርሳለን የሚል ተስፋ ስላላቸው በኃላፊነት እንድቆይ ይፈልጉ ነበር። የእነዚህ ሰዎች ሐሳብ ከቅንነትና የከተማውን ዕድገት ከመመኘት የተነሳ ነው እንጂ፣ የታከለ ሥራዎች ሁሉም ፍፁምና እንከን የለሽ (Flawless) ነው እያሉ ግን አይመስለኝም። ሊሆንም አይችልም። እንደዚህ ዓይነት ሐሳቦች ሁልጊዜም አገር የሚገነቡና ለሚሠሩ ሰዎች ደግሞ አቅም፣ ጉልበትና ስንቅ የሚሆኑ ናቸውና አሁንም በፍፁም ቅንነት በጋራ ሥራዎቻችን እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ደግሞም ለተፈጠሩ ችግሮች ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ።


ሌሎች ደግሞ ወቀሳ አላቸው። ይህም ተገቢና ተፈጥሯዊ ነው። እውነት ለመናገር ወቀሳውም በሥራ ሒደት የሚፈጠረውን ስንክሳር ማረም ማስተካከል ይችላሉ ከሚል የመነጨና የራሳቸው ልጆች መሆናችንን ስለተረዱት የሰነዘሩብን ነው ብዬ አምናለሁ። ይኼውልህ እኛ ኬክ ሻጮች አይደለንም። የሕዝብ አገልጋዮች ነን። የቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ በግሌ ማለት የምችለው ሪፖርቱ በአመዛኙ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የቀረበ መሆኑን ነው፣ የምረዳውም እንደዚያ ነው። ብዙም ቦታ አልሰጠውም።


ነገር ግን በቅን ልቦና ሥራዎቻችን ሲደግፉ ለነበሩት የከተማችን ነዋሪዎች ግን ትክክለኛና ተዓማኒነት ያለውን መረጃ መስጠት ስላለብኝ ነው ይህንን መልስ የምሰጠው እነሱ ወርደው በሄዱበት መንገድ መሄድ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን በእውነትና በትህትና በቅንነት ሥራዎቻችንን ሲደግፉ፣ ሲያግዙና ሲያበረታቱ ለነበሩት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ሆነ ለሌሎች መግለጽ ስለፈለግኩ ነው። የደከምንበትን የሕዝብ ሥራ ለከሰረ ፖለቲካው ማነቃቂያ እንዲጠቀምበት ስለማልፈልግም ጭምር ነው።


ሪፖርተር፡- በኢዜማ ሪፖርት የቀረበብዎትን ወቀሳና ክስ ሙሉ በሙሉ አይቀበሉትም ማለት ነው?


አቶ ታከለ፡- ስለቀረቡት ወቀሳዎች የጀርባ ፍላጎት የተሰማኝን እየተናገርኩ ነው። ወደ ወቀሳዎቹ ልምጣልህ። የመሬት ወረራ የመላው የኢትዮጵያ ከተሞች ችግር ነው። በተለይ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ችግሩ የከፋ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ የመሬት ይዞታዎች (ሕገወጥና አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድላቸው) የተያዙ መሬቶች አሉ። ይህ ጥናት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ አጥንተው ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ሌሎችም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ገብቷል። ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ካቀረብናቸው የከተማው ችግር ውስጥ አንዱ የመሬት ወረራ ጉዳይ ነው። ችግሩን ለመቅረፍም የሕግና የመዋቅር፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅም ይፈልጋል። ምን ለማለት ነው? በአዲስ አበባ ያለው የመሬት ወረራው ፓርቲው ካቀረበው ሪፖርት ባላይ ነው።


ነገር ግን ወደ አንድ ወገን ወይም ወደ አንድ ብሔር ማላከክ አደገኛ የፖለቲካ አዝማሚያ ነው። ‹‹ፍትሕን አሰፍናለሁ፣ ለሁሉም ዜጎች እኩል እታገላለሁ›› ከሚል ቡድን እንደዚህ ዓይነቱን ጥልቅ ጥላቻ ስታይ የአገራችን ፖለቲካ ከጥላቻና ከእግር ጉተታ አለመውጣቱን፣ እንዲሁም አሁንም ገና ረዥም ርቀትና ትጋት ከሁላችንም እንደሚጠበቅ ነው ያስተዋልኩት።


በቤቶች ላይ ላቀረቡት ሪፖርት በእርግጠኝነት መረጃ የሰጣቸው ሰው በግልጽ እንዲሳሳቱ ለማድረግ የፈለገ ይመስላል። በመጋቢት 2011 ዓ.ም. ወር ዕጣ የወጣላቸው የቤቶች ቁጥር 51 ሺሕ አካባቢ ነው። የእነሱ ‹‹የጥናት ሪፖርት›› ግን የሚለው ሌላ ነው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ የምትተዳደረው ከተማው በሚያወጣቸው ሕጎች ብቻ አይደለም። የፌዴራል መንግሥት በሚያወጣቸው ሕጎችም ጭምር እንጂ። ሕጎችና አሠራሮች ደግሞ ከጊዜና ከሕዝብ ጥቅም ጋር የሚሄዱ ካልሆኑ፣ በማንኛውም ጊዜ ሊሻሻሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሻሩ ይችላሉ። የቤቶች ግንባታ የተጀመረው ከ15 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ እስካሁ ተገንብተው ከተላለፉት፣ እየተገነቡ ካሉትና ዕጣ ሊወጣባቸው ከታቀዱት ከ300 ሺሕ በላይ ቤቶች ውስጥ በከተማው ካቢኔ የተወሰነው ለ20 ሺሕ አርሶ አደሮች ነው።


እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች አሁን የተጀመሩ አይደሉም። ከዚህ በፊትም (በቀድሞዎቹ አስተዳደሮች) ለመምህራንና ለጤና ባለሙያዎች፣ ለፓርላማ አባላት፣ እንዲሁም ለአገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ጉዳተኞች በተመሳሳይ ውሳኔ ሲሰጥ ነበር። የአርሶ አደር ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። አርሶ አደር በመሆናቸው በደሉን ተሽክመው ይኑሩ የሚል ጭፍን ፍርድ ከሌለ በስተቀር። አርሶ አደሩ እኮ ለብዙ ዓመታት ከራሱ መሬት፣ ከራሱ የእርሻ ማሳ ‹‹በልማት›› ምክንያት (በሪል ስቴት፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ) ምክንያት ከመሬቱ ተነቅሏል። እኛ ያደረግነው ምንድን ነው? በአጠቃላይ ከስድስት ክፍላተ ከተሞች ከኑሮአቸው ስለተፈናቀሉ እንዲቋቋሙ ስለተፈለገ በካቢኔ አስወሰንን።


ይህም ማለት ከአጠቃላይ የቤቶች ግንባታ ስድስት በመቶ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች እንዲሰጥ ነው የወሰንነው። ከ20 ሺሕ ውስጥ አርሶ አደር ያልሆኑ ሰዎች አሉ፣ በጥናታችን ለይተናል ካሉ ደግሞ ይህ ሥራቸው ያስመሠግናቸዋል። ነገር ግን ይህንን ጥናት ያሉትን ነገር ይፋ ለማድረግ ለምን የአመራር ሽግሽግ ወቅት ጠበቁ? ለምን አሁን? እኔ ወደ ሌላ ኃላፊነት እየሄድኩ ባለበት ወቅትና የቀረበውን ትችት መልስ ለመስጠት በማልችልበት ወቅት ለምን ለማቅረብ መረጡ የሚለውን ጥያቄ አንስቼ መልሱን ለራሳቸው መተው እፈልጋለሁ።


ድራማውን የሚረዳ ሰው ትወናውን በደንብ ይገነዘባል። ዳሩ ግን ድራማው በከሸፈ ዳይሬክተር የተዘጋጀ፣ በከሸፈ ድርሰት ላይ የተመሠረተ፣ በከሸፈ ትወና የቀረበ ነው። እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል የከሸፉ ‹‹ባለቅኔዎች›› ስብስብ መሆናቸውን፣ በሌላ በኩል በግርግር ወይም በመመሳጠር በሚሠራው የአማተር ፖለቲካ ጊዜያዊ የፖለቲካ ግለት ከመፍጠር ባለፈ፣ ለአገር ግንባታ ፋይዳ እንደሌለው ያየሁበት ነው።


ሪፖርተር፡- እሳቸው ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ብቻ ሲጠቅሙ ነው የከረሙት በሚል ይወቀሳሉ። ምላሽዎት ምንድነው?


አቶ ታከለ፡- ታከለ ኦሮሞ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም ለማለት መድፈር ያቃታቸው አስመስለው የሚያቀርቡት ጥያቄ ይመስለኛል። ለማንኛውም እኔ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ታከለ ኦሮሞ ነው ኢትዮጵያዊነቱ የማይቃረንበት። ታከለ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው። አባቶቹ በዓድዋ ላይ ያለ ማንም አስገዳጅነት በአጥንታቸውና በደማቸው ሉዓላዊ የሆነችውን ድንቅና ውብ አገር ያወረሱት የአምቦ ልጅ ነው። ታከለ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ኦሮሞን ብቻ ሲጠቅም ነው ያሳለፈው? ይህ ሐሳብ በጣም አስገራሚ ነው። ይህ ማለት እኮ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኦሮሞ ናቸው ማለት ነው። ይህ ማለት ከ6,000 በላይ በላይ ተማሪዎች ኦሮሞ ናቸው ማለት ነው። ይህ ማለት ከ1,000 በላይ የሸክላ ማዕከል የገነባንላቸው ሁሉ ኦሮሞ ናቸው። ሁለት ሚሊዮን የሸገር ዳቦ ምርት ቀጥታ ተጠቃሚዎች ሁሉ ኦሮሞ ናቸው ማለት ነው።


ይህ ሐሳብ መጀመርያ የአዲስ አበባ ከተማን ኃላፊነት ስንረከብ የነበረው ንግርትና ባዶ ትርክት አካል ነው። በየትኛውም መመዘኛ የማይገልጸኝ የወንድሞች መሠረተ ቢስ ክስ ነው። ታከለ እኮ ምክትል ከንቲባ ነው እንጂ ንጉሥ አይደለም የነበረው። በአጋጣሚ እኔ ምክትል ከንቲባ ሆንኩ እንጂ በከተማ ደረጃ ያለነው ከተለያዩ ብሔሮች የተወከልን አመራሮች ነን። እኔ እንደ አንድ ሰው ብቻ ነበርኩ እንዴ በውሳኔዎች ላይ ድምፅ የነበረኝ? ከዚህ በተረፈ ከ67 በላይ የከተማ መዋቅር መሥሪያ ቤቶች፣ አሥር ክፍላተ ከተሞችና ከ120 በላይ የወረዳ መዋቅር አለው ከተማው፡፡ በሁሉም ቦታዎች ኦሮሞ ነው የሚመራው ካላልከኝ በስተቀር።


ሪፖርተር፡- ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት በቦታው ላይ ብቆይ ይህን ማድረግ እችል ነበር፣ እነዚህን ፕሮጀክቶችንም ከግብ ባደረስኳቸው ብለው የሚቆጩበት ሥራ አለ?


አቶ ታከለ፡- በሁለት ዓመት ማድረግና መሥራት ያለብንን በአቅማችን በትጋትና በአስተዋይነት ሠርተናል። ለምሳሌ የእናቶችን እንባ ያበሰውና የተማሪዎችን ተስፋ ያለመለመው የተማሪዎች ምገባ፣ የሸክላና የዕደ ጥብብ ማዕከል ግንባታ፣ የኑሮ ውድነት ለማቃለል እያገዘ ያለው የሸገር ዳቦ፣ የሸገር ዘይት ፋብሪካ ግንባታ፣ የእናቶችን ቤት ማደስ፣ የማስ ስፖርት፣ ወጣቶችን ከጎዳና ማንሳት መጀመር፣ የተረሱ አርሶ አደሮችን ማገዝ፣ የዓድዋ፣ የመስቀል አደባባይ፣ የግዙፍ ቤተ መጻሕፍት ግንባታ፣ የፑሽኪን ጎተራ መንገድ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ጀምረናል፣ ግማሽና ከዚያ በላይ አድርስናል። ስለዚህ የምኮራበት እንጂ የምቆጭበት ሥራ የለም።


ሪፖርተር፡- በከንቲባነት የኃላፊነት ቆይታዎ አሳክአቼዋለው ብለው የሚያስቡት ነገር አለ?


አቶ ታከለ፡- እንዴታ!! ለምሳሌ የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር፣ የተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር፣ የሸክላና የዕደ ጥብ ሥራ ላይ የተሰማሩ እናቶች ላይ የሠራነው ሥራ፣ ከተማዋን የለወጡ ወደ የነዋሪዎቿ ጓዳ የዘለቁ መልካምና ፍሬያማ ሥራዎችን አከናውነናል።


ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ የኃላፊነት ቆይታዎ ወቅት ተምሬያለሁ የሚሉት ጠቃሚ ትምህርትና የማይረሳዎት ነገር ካለ?


አቶ ታከለ፡- አዎ፣ በዝቅታ ውስጥ ከፍታ እንዳለ በግልጽ የተረዳሁበትና ለቀሪ ዘመኔም የሕይወቴና የሥራዬ መሪ እንደሚሆን ተምሬያለሁ፣ ደግሞም ተገንዝቤያለሁ።

ሪፖርተር፡- አሁን የተሾሙበት ቦታ በበርካታ ቀውሶችና የጥቅም ግጭት የተሞላ፣ በዚያው ልክ አገር ሊለውጥ የሚችል ዕምቅ አቅም ያለው፣ ነገር ግን በብዙ ችግሮች የተተበተበ ዘርፍ ነው። ሕገወጥ የማዕድናት በተለይም የወርቅ ንግድ ያለበት፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው። እርስዎ ደግም የሥራ ልምድዎ ከከተማ አስተዳደር ጋር የተቆራኘ ስለሆነ አዲሱ ኃላፊነት የሚፈተኑበት አይመስልዎትም?


አቶ ታከለ፡- የዕውቀት ምንጮች ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ አይደሉም። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዕውቀት ምንጭ ብቻ ሳይሆን የፈተናም፣ የውጣ ውረድም ትምህርት ቤት ነው። ውስብስብ ሒደት የሚታለፍበትም ነው። አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የራሱ የሆነ ውስብስብ የዕውቀት ትምህርት ቤት ነው። ከላይ ያነሳሁልህን ፈተናዎችንም የምትጋፈጠውና እንደ ብረትና ወርቅ ነጥረህ ለሌላ የተልዕኮ ፈተና የምትዘጋጅበት፣ በይዘቱም በቅርፁም የተለየ የታሪክ ጉዞ ነው። ስለዚህ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርም ሌላ ትምህርት ቤት፣ ሌላ የስኬት፣ እንዲሁም የፈተና ጉዞ ነው። ተስፋ አለኝ በሁሉም ረገድ የተሳካና በአገራችን የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ አሻራችን በዚህ ዘርፍ ጎልቶ ይታያል።

ሪፖርተር-፡ በመጨረሻ ላገለገሉዋቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?

አቶ ታከለ ፡- ሁልጊዜም እንደምለው ...... እወዳችኋለሁ

Report Page