*/

*/

From

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን ነሐሴ 27-ሲኦል ውስጥ ገብተው ይጸልዩ የነበሩት ታላቁ ጻድቅ ተአምረኛው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ልደታቸው ነው፡፡ + ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ሰማዕታቱ ቅዱስ ብንያሚንና እኅቱ ቅድስት አውዶክስያ ዕረፍታቸው ነው፡፡ + ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ቅድስት ሣራ መታሰቢያቸው ነው፡፡ + ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት 4ኛው የሆነው መልአኩ ቅዱስ ሱርያል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፡፡ + ነቢዩ ሳሙኤልም በቤተ መቅደስ ሳለ የተጠራበት የመታሰቢያው ዕለት ነው፡፡ + 12ቱ የአባታችን የያዕቆብ ልጆች መታሰቢያቸው ነው፡፡

+ + + + +

ሰማዕታቱ ቅዱስ ብንያሚንና እኅቱ ቅድስት አውዶክስያ፡- ወላጆቻቸው ደጋግ ክርስቲያኖች ስለሆኑ በቅድስና የሚኖሩና እንግዳን እንዲሁም መጻተኛን መቀበል የሚወዱ ናቸው፡፡ ቅዱስ ብንያሚንና ቅድስት አውዶክስያን በወለዷቸው ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኝተው ምግባር ሃይማኖት እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ወዲዚያች አገር ከሃዲ መኮንን መጣና የብዙ ክርስቲያኖችን ደም ሲያፈስ ቅዱስ ብንያሚንም ይህንን ሰማና በጌታችን ስም ሰማዕት ይሆን ዘንድ ወደደ፡፡ በመኮንኑም ፊት ቆሞ የክርስቶስን አምላክነት መሰከረ፡፡ መኮንኑም ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች ካሠቃየው በኋላ አሠረው፡፡ ወላጆቹና እኅቱ ይህንን በሰሙ ጊዜ እጅግ አዝነው አለቀሱ፡፡ ቅዱስ ብንያሚን ግን ‹‹የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ ጥላ ፈጥኖ ያልፋል፣ የወዲያኛው ዘላለማዊው ኑሮ ግን ፍጻሜ የለውም….›› እያለ ያጽናናቸው ነበር፡፡ እኅቱ ቅድስት አውዶክስያም ወንድሟ ይህንን ሲናገር ከሰማች በኋላ ‹‹አንተ የምትሞተውን ሞት እኔም ከአንተ ጋር እሞታለሁ›› አለችው፡፡ ይህንን ብላ ፈጥና ወደ መኮንኑ ዘንድ በመሄድ የጌታችንን ክብር መሰከረች፡፡ እርሱም ያሠቃያት ጀመር፡፡ ከወንድሟም ጋር በእሥር ቤት ውስጥ አሥረዋቸው ያለ ምግብና ያለ መጠጥ 20 ቀን አቆዩአቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ወደ አደባባይ አውጥተው ከባድ የሆኑ ትላልቅ ድንጋዮችን በአንገታቸው ላይ አሥረው ወደ ጥልቅ ባሕር ውስጥ ጣሏቸው፡፡ ወዲያውም የታዘዘ መልአክ መጥቶ ድንጋዮቹን ከአንገታቸው ፈታላቸውና ወደ አንድ ወደብ አደረሳቸው፡፡ በዚያም አንዲት ድንግል ልጅ ብታገኛቸው ሳመቻቸውና ከውኃው ውስጥ አወጣቻቸው፡፡ ቅዱሳኑ ዳግመኛም ወደ መኮንኑ ሄደው እርሱንና የረከሱ ጣዖታቱን ረገሙበት፡፡ እርሱም ጽኑ በሆኑ ሥቃዮች አሠቃያቸው፡፡ ማሠቃየቱም በሰለቸው ጊዜ በዚህች ዕለት አንገታቸውን በሰይፍ አስቆረጠውና የሰማዕትነት ፍጻሜያቸው ሆነ፡፡ የሰማዕትነት አክሊልም ተቀዳጁ፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + + +

የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል በነበረው በገዛ አባቱ እጅግ ተሠቃይቶ ምስክርነቱን የፈጸመው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር፡- ኅርማኖስ የተባለው ወላጅ አባቱ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ያፈስ የነበረው የዲዮቅልጥያኖስ ልዩ አማካሪና የሠራዊቱ አለቃ ነበር፡፡ እናቱ ማርታ ግን በክርስቶስ አምና የተጠመቀች ክርስቲያን ነበረች፡፡ እንዲያውም ልጇን ቅዱስ ፊቅጦርን ከመውለዷ በፊት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዳለበት ሄዳ ‹‹እመቤቴ ማርያም ለኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን ልጅ ስጪኝ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን ማኅፀኔን ዝጊልኝ›› ብላ በጸለየችው ጸሎት ነው ቅዱስ ፊቅጦርን ያገኘችው፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ ያሉ በክርስቶስ ያመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ ‹‹ከፍ ባለ ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድርያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ›› ቢለውም ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ሥቃይን ተቀብሎ ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ዲዮቅልጥያኖስን ‹‹ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም መጣሁ፤ ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣ ቤትህንም ጠላሁ›› ብሎታል፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ፊቅጦርን በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕረግ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን ይጾማል ይጸልያል እንጂ በንጉሡ ቤት አይበላ አይጠጣም ነበር፡፡ ዕድሜውም 27 ብቻ ነበር፡፡ አባቱንም ከጣዖት አምላኪነቱ እንዲመለስ ቢመክረው ሄዶ ለንጉሡ ከሰሰው፡፡ ፊቅጦርም ‹‹ለአንተ ለጣዖት አምላኩ አገልጋይ አልሆንም›› በማለት በንጉሡ ፊት ትጥቁን ፈቶ ጣለ፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ወላጅ አባቱ ኅርማኖስ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን ስለነበር ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል ብዙ ሲያግባባው ነበር፡፡ አባቱም ልጁ በሀሳቡ እንዳልተስማማለት ሲያውቅ ከዲዮቅልጥያኖስ ጋር ተማክሮ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያና ወደ ተለያዩ ሀገሮች በግዞት ተልኮ በዚያም ተሠቃይቶ እንዲሞት ፈደበት፡፡

ወደ ግብፅም ልከው በዚያ እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ነጥቆ ወስዶ በሰማያት የሰማዕታትን ክብር አሳይቶት ወደ ምድር መለሰው፡፡ ክፉዎቹም በብረት አልጋ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደደዱበት፡፡ በሌላም ልዩ ልዩ በሆኑ ማሠቃያዎች እጅግ አሠቃዩት፡፡ መልአክም ተገልጦ ፈወሰው፡፡ ወደ እንዴናም አጋዙትና በዚያም ብዙ አሠቃዩት፡፡ ምላሱን ቆረጡት፤ በችንካርም ጎኖቹን በሱት፤ ቁልቁል ሰቅለውም ቸነከሩት፤ በእሳትም ውስጥም ጨመሩት፤ ዐይኖቹን አወጡት፤ እሬትና መራራ ሐሞትንም አጠጡት፡፡ ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ጌታችንም ተገልጦ ካጽናናው በኋላ ፈወሰውና ፍጹም ጤነኛ አደረገው፡፡ ፊቅጦር፣ ፋሲለደስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ አውሳብዮስና መቃርዮስ እነዚህ ሰማዕታት በአንድነት በአንድ ዘመን አብረው ኖረው ተሰውተው ሰማዕት የሆኑ የሥጋም ዝምድና ያላቸው የነገሥታት ልጆች ናቸው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም የቅዱስ ፊቅጦርን ዐይኑን አስወለቀው፣ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ መጥቶ የዓይኑን ብርሃን መልሶለታል፡፡ ሰማዕቱ በመዝለል ባሕር የሚሻገር እንደ አሞራ የሚመስል ፈረስ ነበረው፡፡ ከዚህም በኋላ ማሠቃየቱ ቢሰለቻቸው ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ሰይፈው በሰማዕትነት እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ ፊቅጦር አንድ የሚነገር ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ እርሱም በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ በራእይ ተገልጦ በ8ኛው ሺህ ዘመን በሀገራችን በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም በቁስጥንጥንያና በሮም ወደፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ በግልጽ የተናገረ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ስለ ሃይማኖት ቅዱስ ፊቅጦር ያየው ራእይ›› የሚል መጠሪያ ያለው ይህ ራእይ በሀገራችን ጎጃም ደብረ ጽሞና ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + +

በቀን ለሰባት ሰዓት ያህል ሲኦል ውስጥ ገብተው ይጸልዩ የነበሩትና ጥንባሆ ስለሚጠጡ ሰዎች ጌታችን ታላቅ ምሥጢርን የነገራቸው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ልደታቸው ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ስንነሣ ጥናቶች እንደሚያሳዩትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንዱ ክፍል (UNODC-united nation’s office on Drug and crime) በጥናቱ ይፋ እንዳደረገው በየዓመቱ 200,00 (ሁለት መቶ ሺህ) ሰዎች አደንዛዥ ዕፅን መጠቀማቸውን ተከትሎ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ በአሜሪካን አገር ብቻ በየቀኑ ከ95 በላይ ሰዎች በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት ይሞታሉ፡፡ አደንዛዥ ዕፅን በክትባት መልክ (injection) ከሚወስዱት ውስጥ አብዛኛዎቹ በደማቸው ውስጥ የHIV ቫይረስ ይገኛል፡፡ በአሜሪካን አገር በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በመኪና አደጋ እና በድንገተኛ እሳት አደጋ ምክንያት ከሞቱት ሰዎች ቁጥር በ10% ብልጫ አለው፡፡ አደንዛዥ ዕፅንና ሱስን በተመለከተ ዓለም መፍትሄ አጥታ ትባዝናለች፡፡ ችግሩ በዓለም ላይ ይህን ያህል የገዘፈውንና ብዙ ቀውሶችን እያስከተለ ያለውን የጥንባሆን (የአደንዛዥ ዕፅን) ጉዳይ አባቶቻችን እነ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ምሥጢሩን አግኝተውታል፡፡ ሚሥጢሩንም ከፈጣሪ አግኝተው ከተረዱ በኃላ ጤናን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ ለዘለዓለም የነፍስን ቅጣት እንደሚያስከትል አደንዛዥ ዕፁም ከሰይጣን እንደተገኘ በግልጽ ነግረውናል፡፡ ጻድቁ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ጥንባሆን ስለሚጠጡ (አደንዛዥ ዕፅን ስለሚጠቀሙ) ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን ከጌታችን የተነገራቸው ናቸው፡፡ (የዚኽን የጥንባሆውን ምሥጢር ከጻድቁን ገድል ላይ ይመለከቷል።)

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደተጋድሎአቸውና እንደጽድቃቸው መጠን እንደተሰጣቸውም እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን መጠን በሁሉም አካባቢ እንደሌሎቹ አንጋፋ ቅዱሳን በደንብ ያልታወቁ እጅግ የከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ አባታቸው ደመ ክርስቶስ እናታቸው ማርያም ሞገሳ ይባላሉ፡፡ ሀገራቸው ጎጃም ግሽ ዓባይ ነው፡፡ ዋሸራ ገዳም ካቀኑት አባቶች ውስጥ አንዱ የሆኑት ተስፋ ኢየሱስ የተባሉት ጻድቅ ወንድማቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ጸጋ ኢየሱስ ይባላል፡፡ ነሐሴ 27 ቀን ተወልደው ሃይማኖትን ተምረው ካደጉ በኋላ ‹‹ዘርዐ ቡሩክ›› ብሎ ስም ያወጣላቸውና ጳጳስ አድርጎም የሾማቸው ራሱ ጌታችን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡
አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ከመወለዳቸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አባታቸው ደመ ክርስቶስ ዐይነ ሥውር የነበረ ሲሆን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በተወለዱ ጊዜ ግን የአባታቸውን ዐይን አብርተውለታል፡፡ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ገና በሰባት ዓመታቸው ነው ረቡዕና ዓርብ መጾም የጀመሩት፡፡ በዚሁ በሰባት ዓመታቸውም ‹‹ይህን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ ዐይኖቼን አሳውርልኝ›› በማለት ዐይናቸውን እንዲያጠፋላቸው አምላካቸውን ለምነው እንደፈቃዳቸው ዐይነ ሥውር ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ በ12 ዓመታቸው ጌታችን ‹‹ለዓለም የምታበራ ብርሃን አደርግሃለሁና ዐይንህም ይብራ›› በማለት ዐይነ ብርሃናቸውን መልሶላቸው እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ዕድሜያቸው (በ12 ዓመታቸው) ሰባቱንም አጽዋማት ይጾሙ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሁሉ ገለጠላቸው፡፡ መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን፣ መጻሕፍተ መነኮሳትን፣ አዋልድ መጻሕፍትን ሁሉ ገልጦላቸዋል፡፡ ከሟርት መጻሕፍት በቀር ያስቀረባቸው ነገር አልነበረም፤ የቅዱስ ያሬድንም ዜማ እንዲሁ ገለጠላቸው፡፡

ጻድቁ ከሁሉ ቅዱሳን በበለጠ ሁኔታ ዐሥራ ሁለት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆን በ12 ክንፎቻቸውም የሰማይን ደጆች ሁሉ ገሃነመ እሳትንም አልፈው በመሄድ ቀጥታ በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ይቆሙ እንደነበር ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ እጅግ በሚደንቅና ከአእምሮ በላይ በሆነ ሁኔታ አባታችን ለሰባት ቀናት በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቅዱሳን በምልጃቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ ነው የምናውቀው እንጂ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በሲኦል ውስጥ ገብቶ ጸሎት የጸለየ ጻድቅ እስካሁን እኔ አላጋጠመኝም፡፡
አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደ አባታችን ተክለሃይማኖት ለጸሎት በመቆም ብዛት አንድ እግራቸው እስኪሰበር ድረስ በብዙ መከራ ተጋድለዋል፡፡ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር መንበሩን ያጥኑ ዘንድ ከፈጣሪአቸው ታዘው አጥነዋል፡፡ ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ፍጥረታትን ከመፍጠር በቀር ያልሰጣቸው ሥልጣን የለም፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ብፁዕና ቅዱስ ለሚሆን አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ‹እኔ ከሥልጣኔ ሥልጣንን፣ ከክብሬም ክብርን፣ ከጥበቤም ጥበብን፣ ከተአምራቴም ተአምራትን፣ ከስጦታዬም ስጦታን፣ ከትዕግስቴም ትዕግስትን፣ ከፍቅሬም ፍቅርን፣ ከትሕትናዬም ትሕትናን፣ ከባለሟልነቴም ባለሟልነትን ሰጥቼሃለሁና ሁሉ ከሥልጣንህ በታች ሆኖ ይታዘዝልህ› የሚል እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ነው የሰጣቸው፡፡ ልዩ ልዩ ሀብታትን ሁሉ ሰጣቸው፡፡ ‹‹ለሥላሴ ከሚገባ ከስግደትና በቃልና በሥልጣን ፍጥረታትን ለመፍጠር በቀር ምንም ያልሰጠሁህ የለም›› ብሎ ጌታችን በማይታበል ቃሉ እንደነገራቸውና ቃል እንደገባላቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡

አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በወቅቱ በነበረው ገዥ ፊት በሐሰት ተከሰው ለ5 ዓመታት ያህል በእስርና በእንግልት ሲኖሩ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምግብ የሚባል አይቀምሱም ነበርና ከእስር ሲፈቱ አምስት ዓመት ሙሉ ሲሰጣቸው ያጠራቅሙት የነበረው ምግብ ትኩስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያሳሰራቸውንም ንጉሥ ገና ሕፃን ሳለ እናቱ ልታስባርከው ወደ አባታችን ዘንድ ወስዳው ነበር፡፡ አቡነ ዘርዐ ቡሩክም ሕፃኑን ከባረኩት በኋላ ለእናቱ ‹‹ይህ ልጅሽ ወደፊት ይነግሣል በንግሥናው ዘመንም እኔን ያስርና ያንገላታኛል›› ብለው ይህ እንደሚሆን አስቀድመው ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ እንዳሉትም ልጁ አድጎ ሲነግሥ ጭፍሮቹ ‹‹ንጉሥ ሆይ አንተን የማይወድ ለቃልህም የማይታዘዝ አንድ መነኩሴ አለ›› በማለት ምንም እንኳን ንጉሡ ባያውቃቸውም በሐሰት ነገር ስለከሰሱለት በግዞት እንዲኖሩና እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ጻድቁ በግዞት ሲወሰዱ ‹‹እነዚህን መጻሕፍቶቼን ለሰዎች አደራ ብሰጣቸው ይክዱኛል፣ ቤተ ክርስቲያን ባስቀምጣቸው ይጠፉብኛል›› በማለት ሰባት መጽሐፎቻቸውን ለግዮን (ለዓባይ) ወንዝ አደራ የሰጡ ሲሆን ከ5 ዓመት በኋላ ከእስር ተፈተው ሲመለሱ በወንዙ አጠገብ እንደደረሱ ጸሎት ካደረጉ በኋላ ‹‹ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)›› ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ አውጥተዋቸል፡፡ እንዲያውም አቧራውን ከመጻሕፍቶቻቸው ላይ እፍ ብለው አራግፈውታል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው የጠለቀው ምሳር እየተንሳፈፈ ወደ ኤልሳዕ እንደመጣ ሁሉ አሁንም እንዲሁ የቅዱስ አባታችን መጽሐፎች አብሯቸው ከነበረውና ዘሩባቤል ከሚባለው ደቀ መዝሙራቸው ጋር ወዳሉበት ተንሳፈው ሊመጡ ችለዋል፡፡ መጽሐፎቻቸውንም አብሯቸው ለነበረው ደቀ መዝሙራቸው ካሳዩት በኋላ እንዲይዛቸው ሰጥተውታል፡፡
የግዮን ወንዝ ‹‹ግሺ ዓባይ›› ወይም ‹‹ዓባይ›› እየተባለ መጠራት የጀመረው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ‹‹ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)›› ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ አባታችን በቦታው ላይ 30 ዓመት ሙሉ ቆመው ጸልየው ቦታውን የባረኩት ሲሆን ጌታችንም በቦታው ላይ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ብፁዕ አባታችን ለግዮን ወንዝ መጽሐፎቹን በአደራ ሰጥተው በኋላም ከደቀ መዝሙራቸው ከዘሩባቤል ጋር መጽሐፎቹን ከግዮን ምንጭ ውስጥ ከተቀበለ በኋላ ‹በግዮን ውኃ ውስጥ ሳይረጥቡ በደረቅ መጽሐፎቼን የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን› ብሎ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ ‹ያንጊዜም በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ፣ ሕመምተኞች ሁሉ ይዳኑብሽ፣ መካኖች ይውለዱብሽ› ብሎ ግዮንን በቃሉ መረቃት፣ በእጁም ባረካት፡፡ ብፁዕ አባታችንም በዚህች ቦታ ላይ ፈውስ፣ ረድኤት፣ በረከት ይደረግብሽ ብሎ ብዙ ዘመን ቆሞ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ‹ይህ በረከት፣ ረድኤት፣ ሀብት፣ ፈውስ እንደወደድህ እስከዘለዓለሙ በዚህ ቦታ ይሁንልህ› አለው›› ተብሎ ነው በቅዱስ ገድላቸው ላይ የተጻፈው፡፡

ጻድቁ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሌላው የሚታወቁበት ‹‹ብሄሞትና ሌዋታን›› የተባሉ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት ዘንዶዎችን ጥርሳቸውን ቆጥረው ምላሳቸው ሲጣበቅ የዓለም ፍጻሜ እንደሚሆን አስቀድመው ያወቁ ድንቅ ነቢይ የሆኑ አባት በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህም እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት እንስሳት ሴትና ወንድ ሆነው ምድርን እንደመቀነት ከበው የያዙ ናቸው፡፡ ዝርዝር ታሪካቸው በመጽሐፈ አክሲማሮስ (ሥነ ፍጥረትን በሚያስረዳው መጽሐፍ) ላይ በስፋት ተጠቅሰዋል፡፡

የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን።

Report Page