...

...


ግብፅ በሶማሌላንድ ምን ለማድረግ እንደፈለገች ኢትዮጵያ በአንክሮ የምትከታተለው እንደሆነ፣ የተጨበጠ መረጃ ላይ በመመሥረትም ኢትዮጵያ አቋሟን እንደምታሳውቅ ገልጸዋል።


ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት፣ ግብፅ ወደ ሶማሌላንድ ፖለቲካዊ መስፋፋት ለማድረግ የጀመረችው ጥረት አንድምታው ፈርጀ ብዙ እንደሆነ ገልጸዋል።


አንደኛው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ፖለቲካን መረበሽ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተለይም በሶማሊያ ያላትን የቆየ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መገዳደር እንደሆነ አስረድተዋል። 


ይህ የግብፅ ፖለቲካዊ አካሄድ በሊቢያ የፖለቲካ ጉዳይ የበላይነት እንዳትይዝ ከቱርክና ከሩሲያ የገጠማትን ተግዳሮት፣ ወደ አፍሪካ ቀንድ እንዲስፋፋ የሚያደርግ አቅም እንዳለውና ውጤቱም ከወዲሁ መታየት መጀመሩን ጠቁመዋል። 


በዚህ ሥልት በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማድረስ ግብፅ መፈለጓ ግልጽ ነው ብለው፣ በሊቢያ ፖለቲካ ጉዳይ ፍላጎት ያላቸውን እንደ ሩሲያ፣ ቱርክና ከዚህ በተቃራኒ የቆሙትን አሜሪካና የአውሮፓ ኃያላን ወደ ሶማሌላንድ ሜዳ ለመውሰድ የሸረበችው ሴራ መሆኑን ያብራሩት ዲፕሎማቱ፣ ይህ ጥረቷ ከተሳካም እየተሸነፈችበት ያለውን የህዳሴ ግድብ ወይም የዓባይ ወንዝ የውኃ ፖለቲካ ከሊቢያ ሁኔታ ጋር ተጣምሮ፣ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ስበት ማዕከል የማድረግ አሻጥር በውስጡ እንደሚታይም ገልጸዋል። 


ግብፅ ይህንን ሴራ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው የኢጋድ አባል አገሮች፣ አሜሪካና ሌሎች ኃያላን አገሮች በጂቡቲ የሶማሊያና የሶማሌላንድን ፖለቲካዊ አለመግባባት ለመፍታት በተወያዩ ማግሥት መሆኑ ደግሞ፣ ግብፅ ይህ የሰላም ጥረት እንዳይሰምር፣ አካባቢው እንዳይረጋጋና ለፍላጎቷ ምቹ እንዲሆን በሥጋት ላይ እንደሆነች በግልጽ ማሳየቱን አስረድተዋል። 


ግብፅ ከሶማሌላንድ በተጨማሪ በፑንትላንድም ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎቿ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መጨመራቸውን የገለጹት ዲፕሎማቱ፣ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎችን በፑንትላንድ እየገነባች ወዳጅነቷን ለማጠናከር እየጣረች እንደሆነ አስታውቀዋል። 


በሌላ በኩል ሞቃዲሾ ለሚገኘው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት የጦር መሣሪያና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ሞክራ እንዳልተሳካላት የተናገሩት እኚሁ ዲፕሎማት፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ፎርማጆ የዓረብ ሊግ አባል አገሮች የህዳሴ ግድቡን በመቃወም አቋም ሲይዙ እሳቸው ግን ከዚህ ተቃራኒ መቆማቸው፣ ግብፅ አሁን በአፍሪካ ቀንድ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሶማሌላንድ የጦር ሠፈር ለማቋቋም ጥረት አድርጋ እንደነበር፣ እንዲሁም የበርበራ ወደብን አልምቶ ለማስተዳደር የ30 ዓመት ኮንትራት ተፈራርማ እይደነበር ይታወሳል። 


የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንቅስቃሴውን በመቃወም፣ ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር በጥምረት የበርበራ ወደብን ለማልማት ከገባቸው ውል ውስጥ ተከልሶ፣ እንዲሁም የሶማሌላንድ መንግሥት ድርሻ ተቀንሶ ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ 19 በመቶ ድርሻ እንዲሰጣት ተደርጓል። 


የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሶማሌላንድ ልትመሠርት የነበረውን የጦር ሠፈር በዚህ ምክንያት የተወች ሲሆን፣ ተለዋጭ ወደብ በኤርትራ ማግኘቷ ሐሳቧን እንድትቀይር ሳያደርጋት እንዳልቀረ መረጃዎች ያመለክታሉ። 


ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ የልማት ፕሮጀክት ላይ የያዘችው 19 በመቶ ድርሻ አሁንም እንዳለ ሲሆን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ 51 በመቶ ድርሻም ሆነ የሶማሌላንድ መንግሥት ቀሪ ድርሻ አሁንም እንዳለ ቢሆንም፣ አሁንም ፕሮጀክቱ ፈቀቅ እንዳላለ መረጃዎች ያመለክታሉ። 


የግብፅ ባለሥልጣናት ሶማሌላንድ መመላለሳቸውን በቀጠሉባቸው ያለፉት ሳምንታት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ልዩ መልዕክተኛቸው የሆኑትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ወደ ቱርክ ሲልኩ፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴን ወደ ሶማሌላንድ እንደ ላኩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

#Reporter

@YeneTube @FikerAssefa1

Report Page