*/

*/

From

በ750 ሚሊዮን ብር የተገነባ የጋራ መኖሪያ ቤት ለፌዴራል ዳኞች ተላለፈ
************************************ (ኢፕድ)

በ750 ሚሊዮን ብር የተገነባ የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ለፌዴራል ዳኞች ተላለፈ።

በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጄክት ጽህፈት ቤት የተገነባው የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ቁልፍ ርክክብ ተደርጓል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ቁልፎች ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ አስረክበዋል።
ግንባታቸው በአራት ዓመታት ውስጥ የተጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ለ278 አባወራዎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ምቹና ዘመናዊ ቤቶች መሆናቸውም ተገልጿል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የዳኞች የተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ እንዲመሩ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል።

የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየተደረገ ባለው ስራ ላይ የዳኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ አሰራር ለመዘርጋት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
ህዝቡ ሁልጊዜ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ይፈልጋል፤ይጠይቃል፤ዳኞች ህዝቡን በቁርጠኝነት ለማገልገል ቤታቸውም መስሪያ ቤታቸው በመሆኑ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ምቹና ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ማዘጋጀቱ ለሚሰሩት ስራ ቅልጥፍናን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

የዳኝነት አገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሻሻልና ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውሰጥ የቤቶቹ ግንባታ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ የዳኞችን ደመወዝና ጥቅማጥቅም በማሻሻል ሲነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሻ እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል።
"አገሪቱ ባላት አቅም ይህን ያህል ለዳኞች ካደረገች እኛም በሙያችን በታማኝነትና በቁርጠኝነት ለማገልገል መነሳታችንን ማስመስከር ይገባናል፡፡" ብለዋል።

የህግ የበላይነትን ለማስከበር የዳኝነት ሚና ወሳኝነት እንዳለው ጠቁመው፣ የተቋም ግንባታው በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚከናወን ቢሆንም፣ በተቻለ አቅም ለህብረተሰቡ ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል የጀመርነውን ስራ አጠናክረን እንቀጥልበታለን ብለዋል።

ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው፣ የመንግስት ሠራተኞች ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት በመንግስት በኩል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ የዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎችን ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች ቢሰሩም አሁን ካለው ፍላጎት ጋር ብዙ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

መንግስት የሠራተኞቹን የመኖሪያ ቤት ችግር በማቃለል ሰራተኞች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩና ለአገሪቱ ብልጽግና የበኩላቸውን እንዲወጡ ከምንግዜውም በላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Report Page