*/

*/

From

የመሬት ልጆች ነን

ይህች የምንኖርባት ምድር (መሬት) ከተፈጠረች ወደ 4.5 ቢሊየን አመታትን አስቆጥራለች ይላሉ የ አርኪዮሎጂ/ሳይንስ ባለሞያዎች። ስለ አፈጣጠርዋ ስናነሳ ከ ሳይንሳዊው ይልቅ መንፈሳዊው ምጡቅ የሆነ ጅማሬ ነውና ከ መሬት በአምላክ ቃል መፈጠር ጋር ተያይዞ ለአዳም የተሰጠው በፍጥረት ላይ ሁሉ ሉአላዊ የመሆን ስልጣን ይነሳል። ከዚያም ግዜ አንስቶ የሰዉ ልጅ መሬትን እያለማና ቡቃያዋን እየተመገበ ዛሬ ላይ ደርሷል። ባለንበት ዘመን ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ሀይል በመሬት ላይ እንዳላቸው ያምናሉ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን አሁን ላይ በሀገራችንም ሆነ በመላው አለም የእርስ በ እርስ ግጭቶች መንስኤ በ አንድም በሌላም ይኸው የ መሬት ይገባኛል ጥያቄ ነው። የመሬት ባለቤትነት ጊዜያዊ መሆኑ ከመረሳቱም ባሻገር ፤ ከመሬት(አፈር) መበጀታችን የተዘነጋን ይመስላል። አንድ ሰሞን መሬት የህዝብ ነው ፣ ሌላ ግዜ ደግሞ የመንግስት ነው... እያሉ የመሬት ባለአባቶች እና የመንግስት አካላት ሲታበዩ እና በኩራት ሲናገሩ ቆይተዋል ። ህዝብም ሆነ መንግስት ባለበት ሰአት ላይ የመሬቱ ጌታ ይሆናል እንጂ ግዜው ባለፈ ሰአት ከመሬት(አፈር) በታች ነው። አያቶቻችን በየአካባቢው ተዘዋውረው መኖራቸውና የየማህበረሰቡን ባህላት በማወቃቸው በፍቅርም ሆነ በጥይት ሀይል ውሉ ባይገባኝም ያው ኖረው ዛሬን ሰተውናል። አሁን ላይ ያለነው በአንፃሩ ካለንበት ልማድም ሆነ አስተሳሰብ ውጪ የመኖር ክሂሉ ስለሌለን ፤ አዳም(አደም) የፍጥረት መጀመሪያ መሆኑን እና አምላክ ለ ኢብራሂም(አብርሀም) "ዘርህን እንዳሸዋ እና ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለው" ብሎ ቃል መግባቱን ዘነጋነው መሰል። እንዲህ ከሆነ ፤ በሰውነታችን እንድንበዛ እንጂ መከፋፈላችንን አምላክ መች ወደደ? ሰው ሆኖ መብዛቱ የእርሱ ቃል እንጂ መችስ የኛ ሆነ?

አዳምን(አደምን) ከመሬት አፈር ሲሠራው... በሰውኛ፦ ፈጣሪው (አባቱ) ፤ መገኛው ደግሞ መሬት(አፈር) ነበረች። አኛ የመሬት - አፈር ልጆች ነን እንጂ መሬት የኛ አይደለችም። እንድንከባት እንጂ እንድንጋደልባት አልተፈቀደልንም!። ማንም ከ መሬት በላይ አይሎ ሁልጊዜ መግዛት አይችልም ፤ ጊዜ እንደ ነፋስ ፣ እድሜም እንደ ወንዝ ካለፈ ላይመለስ እስከ ወዲያኛው ወደዚችው ጌታሽ ነን ወደምንላት መሬት ይመልሰናል። ስለዚህ ነው ከልዩነታችን አንድነታችን ይበልጣል የምላችሁ ፤ ባቢሎን ላይ ቋንቋችን ቢለያይም አምላክ በ አመተምህረቱ ምሮናል ፤ አንድ አድርጎናል ላንለያይ። በዚህላይ የሆነች ነገር ላክል... "ይህች ሀይማኖትዋን አክባሪ ምድር ላይ ቁጭ ብሎ ጎጠኛ እና ዘረኛ የሚሆን ካለ ፤ ሀይማኖቱን አያውቀውም ወይንም ሳይገባው ነው ሚከተለው። ሁሉም ቤተ እምነት ሰላም እና ፍቅር ሰባኪ ነውና።"

Report Page