____________________

____________________

✍ lita

.. ገና አመጣጥህን አይቼ የአካሄድህ ኪነት ምን ሊመስል እንደሚችል አውቄያለሁ። ወደቤቴ የፈጠኑ እግሮችህን እያየሁ ጀርባ አሰጣጥህን ምን እንደሚመስል አውቄያለሁ። ዛሬ ከአይኖቼ ላይ መነሳት የተሳናቸው አይኖችህ ነገ በመሰልቸት ማዶ እንደሚቃብዙ አውቃለሁ። በፍቅር የጋለው ሰውነትህ የቱ ጋር በርዶ መቼ ሌላ ሙቀት ፍለጋ ገበያ እንደሚወጣ አውቃለሁ። በውብ ቃላት የሸለመኝ አንደበትህ መቼ እወድሻለሁ ዳገት እንደሚሆንበት አውቃለሁ...

አየህ ህይወት ትምህርት ቤት ነች። ትኖርና ታውቃለህ። ብዙ ትናንት ይኖርህና ከ እስከ የቷ ይገባሃል። ትናንት በሬን ያለፉ ሁሉ የቻሉትን እየዘገኑ ሄደዋል። በመጣ በሄደው ጎድያለሁ። የገባው በወጣ ቁጥር እየተውተረተርኩ ልቤን የምጠግን ነኝ።

የገነባሁትን አፍርሰህ ፣ ያበጀሁትን ዘባርቀህ እንደምትሄድ ባውቅም ክረምትን ፍራቻ በጋን መሸሽ አልሻምና በሬን ገርበብ አድርጌ ተቀበልኩህ።

ደግሞስ መጨረሻውን የምታውቀውን ድራማ እያየህ ተዝናንተህ አታውቅም? አንድ የምትወደውን ፊልም ለምናምንነኛ ጊዜ እያየህ አልሳክም? አላለቀስክም? እንደዚህ ነው። በህይወት ውስጥ ዋጋ ያለው መጨረሻው አይደለም። መንገዱ ነው።

በል አሁን ና እቀፈኝ...እቅፍህ ውስጥ ሁሉን እረሳለሁ። አፍህ ውስጥ በተቆላመጠው ስሜ እንደ ልጃገረድ በሽኩርምሚት እስቃለሁ። በጎዳና ስንሄድ እጄን አጥብቀህ ያዘኝ በአለም ላይ እንደእኔ ደስተኛ የሌለ እስኪመስል አየር ላይ እንሳፈፋለሁ። መውደድህን ሳትሰስት ንገረኝ ከእንባዬ ቀላቅዬ ፍቅሬን እነግርሃለሁ።

ገብተው ለሄዱት ሁሉ መጠኑ ቢለያይም አይኔ እንባ አልነሳቸውም። አንተም ስትሄድ የማፈስልህ እንባ አላጣም። እስከዚያው ለትውስታ የሚቀርልን መንገድ እንሂድ። ማለዳችንን እያስዋብን የምሽት የእንባዬን ጉድጔድ አርቀን እንቆፍር።

_________________________________

Report Page