......

......

.


ወደ ቤቷ ለመግባት ያዘቀዘቀችውን  ጠይም ውብ ጀንበር ከርቀት እያያ ሰፊ ባለ ኮብልስቶን መንገድ ተከትሎ በቀስታ ይራመዳል። ጥቁር ኮፍያ ጭንቅላቱ ላይ ደፍቷል። ከኮፍያው ስር የተኮሳተረ ጠይም ፊት ይታያል። አዋራ የጠጣ ጥቁር ቦርሳ አንግቷል። 

አይኑን ከጠይም ጀንበሯ ሲመልስ ከፊት ለፊቱ መንገዱ ጥግ ላይ የስልክ እንጨት ላይ የካልሲ ኳስ በገመድ አስረው በጠመጠመ የሚጫወቱ ልጆች ተመለከተ (ቴዘር..)። እርምጃውን የማቆም ያህል አቀዝቅዞ በአንክሮ ተመለከታቸው። አዲስ ነገር የተመለከተ ያህል ነበር እይታው። አንዳች አይነት ናፍቆትና ትዝታ በአይኖቹ ላይ ለቅፅበት አለፉ። 

አብዛኛውን ጊዜ የምትለብሰውን ካኪ ሱሪ እግር አጥፋ እግሮቿን ሽቅብ ኳሱን ለመመለስ ስትዘረጋ በመገረም ነበር የሚያያት። ብዙ ጊዜ ከመጫወት ይልቅ ከዳር ሆኖ እሷ ስትጫወት ማየት ይመርጥ ነበር። ፀጉሯ በንፋስ ሲውለበለብ... እግሮቿ በስልት ተነስተው ሲወረወሩ... በተመስጦ ሆኖ ያያታል.. የሚችላት አልነበረም። ሁሉም ነገሮች ላይ ቃጤ ነበረች። በዚያ ላይ ደፋር። ከአባቷ ጋር ነበር የምትኖረው። አባቷ ሰፈርተኛው የሚያከብራቸው የታወቁ ጠበቃ ናቸው። የሴትነት ቀንበር ሳይጭኑባት ነፃ አድርገው ነበር ያሳደጔት። የሴትም የወንድም የተባሉ ጨዋታዎች አይቀሯትም። ከሰፉሩ ወንዶች ጋር አፈር ላይ እየተንከባለለች ብይ ትጫወታለች። ከሴቶቹ ጋር ሲዞ ትዘላለች። ከወንዶቹ ጋር ለዋና ወደ ወንዝ ትወርዳለች (ሁሉም ተደብቀው ቢሆንም)። 

በጀርባው አልጋ ላይ ተኝቶ የእስር ቤቱን የቆሸሸ ኮርኒስ እየተመለከተ... የእስር ቤት ግቢ ውስጥ አንዱ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ... ውሃ ውሃ የሚል የእስር ቤቱን ምግብ እየበላ... ለብዙ ሺኛ ጊዜ ይሄን ነገር አሰላስሎታል። ልጅነታቸውን። በእያንዳንዱ የህይወት እጥፋቶቹ ውስጥ እሷ አለች። ልጅነቱ ውስጥ። ወጣትነቱ ውስጥ። ዛሬው ውስጥ።

አሁን የት ትሆን...? ምን አይነት ህይወት እየኖረች ይሆን..? ብዙ ብዙ እያሰበ እርምጃውን ቀጠለ። 

በጊዜዋ መሆን ያለባትን ሁሉ ሆና ብትጠብቀው አይከፋባትም። ድሮም ጠብቂኝ አላላትም። የፈለገው ጤናኛ ህይወት እንድትቀጥል ብቻ ነው። 

ሁሉም ነገር በአፍታ ነበር የሆነው። እነሱ ቤት አብረው ነበሩ። አዲስ አበባ ዪንቨርስቲ የመመደቧን ዜና ተከትሎ እየቦረቁ... የእናቱን የዶሮ አይን የመሰለ ቡና ሲጠጡ... ሲጎነታተሉ.... ሲቀላለዱ..... ሲያወሩ.... 

ወደ ቤቷ ለመሄድ ስትወጣ ግማሽ መንገድ ሸኝቷት ሳታስበው መንገድ ላይ ከንፈሯን ስሞ አሳፍሯት እየሳቀባት ተመለሰ። እቤት ሲገባ ስልኳን እረስታለች። ይዞላት እየሮጠ ወጣ። እርቃለች። ሮጦ ወደ ቤቷ የሚወስደውን እጥፋት እንደጀመረ አንድ ወጠምሻ ልጅ እጇን ግጥም አድርጎ ይዟት ተመለከተ። እንዲለቃት እየታገለችው ነው። በደም ፍላት ተጠጋቸውና ከእጁ መንጭቆብ አስለቀቃት። ልጁ ለድብድብ ተጋበዘ። እንኳን በእሷ መጥተውበት እንኳን ነካክተውት ሴትን ልጅ አላግባብ የሚላከፍ ወንድ ጋር ተጣላ ተጣላ ይለዋል። ከፊቱ በአይኑ የታየውን ድንጋይ አንስቶ ጭንቅላቱ ላይብ አሳረፈው።  አካባቢው በደም ተጨማለቀ። ጩኸት በረከተ። አንፑላንስ መጣ። በሁለት ፖሊሶች ይዘውት ሄዱ። ልጁ ለረጅም ጊዜ ኮማ ውስጥ ቆየ። አስር አመት ተፈረደበት። ቁጭ ብሎ ተረጋግቶ እስኪያስበው ድረስ የሆነው ሁሉ ህልም  ነበር የሚመስለው። የእናቱ እጅ ዳብሶ እስኪቀሰቅሰው ይጠብቅ ነበር። እሷ አንገቱ ስር ገብታ እየነከሰች ተነሳ እስክትለው ይጠብቅ ነበር።

መጀመሪያ ሰሞን እየተመላለሰችብ ትጠይቀው ነበር። ፊቷን በውሸት ፈገግታ አድምቃ። ሰውነቷ ዕለት ዕለት ሲመነምን ይታየው ነበር። አይኖቿም በእንባ ሲሞጨምጩ። ገጿም ላይ ፀፀትና ቁጭት ቤታቸውን ሰርተው ነበር። ቆይቶ እሷን ማየት እንቢ አለ። በዚህ ሁኔታ መተያየቱ ህመም ከመፍጠር በላይ ፋይዳ እንደሌለው ነበር ያሰበው። አስር አመታት ጠብቂኝ ማለት ጭካኔ መሰለው። ቤተሰቦቹንም ጔደኞቹንም ማግኘት አልፈለገም። ከትናንት ህይወቱ ጋር ሙሉ ለሙሉ ተቆራረጠ። የማይገፉ ቀናትን በአራት ግድግዳ ተከልሎ በመፅሀፍት ውስጥ ተሸሽጎ ይገፋ ጀመር። 

 ጣሳውን ከተሰቀለ ጠላ ቤት ጋር ደረሰ። በሩ ጋር እግሮቹን አፍረክርኮ ድንጋይ ላይ ተቀመጠ። አንዲት ልጅ መጥታ ታዘዘችው። በመርቲ ጣሳ ጠላውን እየጠጣ የጠላው ጣዕምብ ይዞበት የመጣውን የትዝታ ጎርፍ በመልክ በመልኩ ለማስተናገድብ እየሞከረ  ወጪና ወራጁን ይመለከት ጀመር። ጥቂት የሚያውቃቸውን ፊቶች ተመልክቷል። ማንም አላስተዋለውም። ይህን ያህል ተለውጫለሁ ማለት ነው..? ሲል አሰበ። አው ለመለወጥ ስምንት አመት ብዙ ነው። ሰፈሩም ብዙ ለውጦችን አስተናግዷል። 

ከዚህ ጠላ ቤት ውጪ በቦታው ያለ ምን አለ...? ከዚያች ከአድማስ ጥግ ብርቱካንማ ብርሃኗን ከምትፈነጥቅ ተሽኮርማሚ ፀሃይ ውጪ ምን በቦታው ያለ ነገር አለ...? የመካ ሱቅ ከቦታውብ የለም በምትኩ ትልቅ ዳቦ ቤት ተከፍቶበታል... በሰንሰል አጥር የታጠረው የእናቱ ጔደኛብ የእማማ ደስታ ግቢብ እንኳን ትልቅ ዘመናዊ መኖርያ ቤት ተሰርቶበታል። ትናንት የሄደባቸው ድንጋዮች  በቅርፅ በቅርፅ በተጠረበ ድንጋይ ተተክተዋል። እሱም ትናንት የነበረውን እሱ አይደለም። ከትናንቱ ብዙ እርቋል። ትናንት እንደሚያስበው ዛሬ አያስብም። ትናንት ህይወትን በሚያይበት መነፅር ዛሬ አይመለከትም። ጊዜና ሁኔታ ከስምንት አመት በፊት የነበረውን እሱነቱን ቀይረውታል። ዛሬ ከትናንት ፍፁም ይለያል። ትናንት የማይደገም ትውስታ ውስጥ ብቻ የሚኖር አላፊ ጊዜ ነው። ሰፈሩ ህያው ነው። የሚኖሩ ሰዎች የሚኖሩበት። ለውጡም ህያው የመሆን መገለጫው ነው። 

ፀሃይዋን በአይኑ ሸኝቶ ሲደነጋግዝ ቦርሳውን አንስቶ ወደ ቤቱ መገስገስ ጀመረ። ትንሽ እንደተራመደ ከፊት ለፊቱ ጥቁር ቦርሳ ያነገተች ቀጭን ሴት ወደ ኋላ የተለቀቀው ስስ ፀጉሯ በንፋስ እየተገፋ ስትመጣ አያት። እርምጃውን ገታ። ነጭ ነጠብጣብ ያረፈበት ከወገቡ በተች የተበተነ ጥቁር አጭር ቀሚስ ለብሳለች። ቀያይ ባቶቿ ከሩቅ ይታያሉ። ልቡ ደረቱን ፈንቅላ ለመውጣት መታተር ጀመረች። እርምጃዋ የተጎተተም የፈጠነም አልነበረም። ሁለት እርምጃ ያህል መሃከላቸው እስኪቀርብ አላስተዋለችውም ነበር። ወይም አላየችውም። ስታየው ቆመች። ትንንሽ አይኖቿ ባለማመን አይነት በሩ።

ዘላ እስክትጠመጠምበት ድረስ የሆነ አይነት ስሜት ውስጥ አየዋለለ ነበር። የሆነ አይነት መደንዘዝ ውስጥ ነበር። ለብዙ ደቂቃዎች እንዳቀፈችው ቆየች። የሰውነቷን መንቀጥቀጥ በሰውነቱ እያደመጠ በፈረጠመ እጁ ጭምቅ አድርጎ አቀፋት። 

እጁን ይዛ ወደ እቤቷ ወሰደችው። የቤታቸው በረንዳ ላይ አጠገብ ለአጠገብ ተቀመጡ። እጁን አንቃ እንደያዘች ነበር። ረጅም ደቂቃ ያለምንም ቃል አሳለፉ። ከፊት ለፊታቸው የብር ጔል የመሰለች ጨረቃ ሰማይ ላይ ተንጠልጥላ ትታያለች። ሁለቱም አይናቸውን ችረዋታል። ቆይቶ እየፈራ "አባባ ደህና ናቸው..?" ብሎ ጠየቃት። ዝም አለችው። ከዝምታዋ መልሱን ተረዳ። እጁን ከእጇ አላቆ በትከሻዋ አሳልፎ አቀፋት። ጭንቅላቷን ትከሻው ላይ ጣል አድርጋ ከሁለት አመት በፊት ታመው እንደሞቱ ነገረችው። ቀጥላም ከሶስት አመት በፊት ተመርቃ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ እየሰራች እንደሆነ አወራችው። ስለቤተሰቦቹ ማወቅ አለበት ብላ ያሰበችውን ሁሉ ነገረችው። ስለእናቱ ስለእህቱና ስለሁለት ወንድሞቹ። በዝምታ አደመጣት ስለዚህች ግራጫማ አለም በተመስጦ እያሰላሰለ። ዳግመኛ በዝምታ ተዋጡ።

"ግን ለምን ናሆሜ... ግን ለምን ከፀፀቴ ጋር ለብቻዬ እንድማቅቅ ተውከኝ.. .? ለምን አይንህን እያየሁ ጥቂት እንኳን ህመሜን እንዳልረሳ ፈረድክብኝ? ..." አለችው አይኗን አይኖቹ ውስጥ ተክላ። የዚህን ጊዜ አይኖቿ ውስጥ ለመውረድ የተዘጋጀ ቅኔው ከውቅያኖስ የጠለቀ ውሃ ተንሰራፋ። ቀስ ብሎ አቀፋት። እቅፉ ውስጥ ሆና ልቡን እስኪያመው ድረስ ተንሰቀሰቀች። 

.

.

.





Report Page