*/

*/

Source

ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ያሰባሰበው የቴክኢን ቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ተጀመረ
=================
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ያዘጋጀውና የአራት ቀናት ቆይታ የሚኖረው ቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ዛሬ በይፋ ተጀመረ፡፡ ከተለያዩ የትምህርት ደረጃ እና ሙያ ዘርፍ የተውጣጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተካሄደው ይህ ፕሮግራም ተሳታፊዎቹን በማንኛውም የኢንኩቤሽን ፕሮግራም ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ብቁ የሚያደርጋቸውና ሀሳባቸውንም ወደ ቢዝነስ እንዲለውጡ የሚያስችላቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ የፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መለወጥ የሚችሉ ሰዎች እንዳላት ይታመነናል ያሉት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም እነዚህን ሰዎች የማሰባሰቡን ድርሻ ኢንስቲትዩታቸው ወስዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ብዙዎቹ ታላላቅ ምጣኔ-ሐብትን መገንባት የቻሉት ሀገራት ለስኬት የበቁት በትምህርት እና የፈጠራ ሀሳብ ላይ በመስራታቸው መሆኑን ያወሱት ኢ/ር ተሾመ የዝግጅቱ ተሳታፊዎችም የፈጠራ ሀሳባቸውን በአግባቡ አንፀው ወደ ቢዝነስ ሀሳብ በመለወጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ ቢዝነስ መገንባት እንዳለባቸው በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸው አሳስበዋል፡፡

በዛሬው መሰናዶ ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ለተሳታፊ የፈጠራ ባለሙያዎቹ የማነቃቅያ ንግግር ያቀረበው ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ እንዲሁም የአይከን አፍሪካ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆነው አቶ ኢዘዲን ከሚል ነበር፡፡ እርሱ ባይኖር ኖሮ የራሴን ድርጅት መመስረትም ሆነ አሁን ባለውበት ደረጃ ለመድረስ አልችል ስነበር “ኮቪድ ለእኔ ትልቅ ዕድል ነው” ያለው አቶ ኢዘዲን ተሳታፊ የፈጠራ ባለሙያዎቹም የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችን ወደ እድል እንዲለውጡ ምክሩን ለግሷል፡፡ አያይዞም የኮቪድ 19 ወረርሺኝን የተመለከቱትን ጨምሮ እሳካሁን በአራት ዘርፎች 36 የተለያዩ ፈጠራና ምርቶችን መስራት መቻሉን እና ከነዚህ ውስጥም 13 ያህሉን በፓተንት ማስመዝገብ መቻሉን ለተሳታፊዎች አሳይቷል፡፡

ከነዚህ በተጨማሪም በዛሬው መርሀ ግብር የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ በሆኑት አቶ ሙሉጌታ አንበሳ፣ አቶ አባይሰው አየለ፣ አቶ በላቸው አለማየሁ እና አቶ አብዱለጢፍ ሀቢብ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ገለፃ ቀርቧል፡፡ አቶ አባይሰው የሰው ልጅ ስላለፈባቸው የፈጠራ ሂደቶች፣ የኢኖቬሽን ምንነት፣ በሀገራችን ያሉ መፍትሄ የሚያሻቸው ተግዳሮቶች እንዲም በአሁኑ ሰዓት ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ እየመሩ ባሉት እንደ ቢግ ዳታ ኮምፒውቲንግ፣ ዲኤንኤ ባዮቴክኖሎጂ፣ ብሎክቼይን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮረ ገለፃን አቅርበዋል፡፡ አቶ በላቸው በበኩሉ የኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እና በኢትዮጵያ ስላለው የኢኖቬሽን ገፅታና ተግዳሮት ያብራራ ሲሆን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ምንነት፣ ምስረታና ተግባራት እንዲሁም በቅድመ ኢንኩቤሽን ፕሮግራሙ ላይ ያተኮረውን ገለፃ ደግሞ አቶ ሙሉጌታ አማካኝነት አቅርቧል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሆነው የሀሳባቸው ጥንካሬ ላይ ምልከታን ባደረገ ውድድር አማካኝነት የተመለመሉ ናቸው፡፡ ይህ ፕሮግራምም ከላይ ከተገለፁት ዓላማዎች ባሻገር ይህ ሀሳባቸውን እንዲያንፁና ወደ አዋጭ ቢዝነስነት እንዲለውጡ የሚያስችላቸው ስለመሆኑ በአዘጋጆቹ ተነግሯል፡፡

Report Page