*/

*/

Source

ከ 22 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ እለት ግንቦት 6 ቀን 1991ዓ.ም. ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ከዚህች አለም በሞት የተለዩባት ቀን ነው ፤ ለማስታወሻ እንዲኾን ይሄንን ጽሑፍ እነኾ:

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከአንድ ነጭ ተማሪያቸው ጋር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሆነው ህመምተኞችን እየጎበኙ ነው። አንድ በአንድ ህመምተኞቹን እያዳረሱ፣ አንድ በእድሜያቸው ገፋ ያሉ አዛውንት ጋር ደረሱ። አዛውንቱ ነጭ–አምላኩ ነበሩና " ነጩ ዶክተር ካላከመኝ" ብለው ድርቅ አሉ። እንግዲህ ወጣቱ ነጭ ፕሮፌሰር አስራትን ፣ በትምህርት ደረጃ ፣ በስራ ልምድ ፣ በግል ተሰጥኦ ይወዳደራል ተብሎ አይታሰብም ። ከእርሳቸው ሰፊ ልምድ፣ ስር ሆኖ ሊማር በፈቃደኝነት የመጣ ነው።
አዛውንቱ ግን በሀሳባቸው ፀኑ።

ስለዚህ ፕሮፌሰር አሥራት መላ ዘየዱ።እርሳቸው ለነጩ ተማሪ እንደ ረዳት ሆነው አዛውንቱን ሊመረምሩ ( ትኅትና የአዋቂዎች ንብረት ናት) በዚህ መሰረት ነጩ ተማሪ የፕሮፌሰር አሥራትን መመሪያ እየተከተለ አዛውንቱን መረመረ። በሽታቸውም ታወቀ። ፕሮፌሰር አሥራት የፈውስ መድሃኒቱን ማዘዣው ላይ ፅፈው ለነጩ ተማሪ አስረከቡ። ተማሪው ደግሞ ለአዛውንቱ። አዛውንቱ ፣ መልአክ የመሰለ ነጭ ሰው ስላከማቸው በጣም እየተደሰቱ፣ ገና መድሃኒቱን ሳይወስዱ የመሻል ስሜት እየተሰማቸው ፣ ሆስፒታሉን ለቀው ወጡ።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ፕሮፌሰር አሥራት ያንን አዛውንት ከመንገድ ያገኟቸዋል። የተለመደ ጥያቄያቸውንም ይሰነዝራሉ ፦ " እንዴት ኖት አሁን? ጨርሶ ተሻሎት?" አዛውንቱ ሲመልሱ ፦

" አሁን ፍፁም ጤነኛ ነኝ። ጭራሽ አሞኝ አያውቅም። ያ የተባረከ ፈረንጅ በሙሉ ነው የፈወሰኝ" ፕሮፌሰር አሥራት በአዛውንቱ የጤንነት ሁኔታ ተደስተው፣ አሁን እውነቱን ብነግራቸው ችግር የለውም ብለው አሰቡና፦

" ይኸውሎት አባቴ፣ ፈረንጁ የኔ ተማሪ ነበር፣ ከኔ ሊማር ነው የመጣው። ያከምዎት፣ ህመምዎን ያገኘሎት ፣ መድሐኒት ያዘዘሎት እሱ አይደለም፣ እኔ ነኝ" ቢሉ፣ አዛውንቱ መልሰው፦
" ለዚያ ነዋ ህመሙ፣ ደጋግሞ የሚነሳብኝ!"

※※※

"ከሰባት አመት በፊት በጠና ታምሜ ነበር። እንደምሞት እርግጠኛ ነበርኩኝ። ብዙ ሐኪሞች ሕመሜ መፍትሔ እንደሌለው አረዱኝ። በመጨረሻ ልጆቼ ወደ ጥቁር አንበሳ ይዘውኝ መጡ። ታዲያ እጁን ይዤ ፊደል ያስቆጠርኩት ልጅ ቀዳጅ ሀኪሜ ሆኖ ተገኘ። እሱ ነው የፈወሰኝ ፤ ከሞት የመለሰኝ። ታዲያ እነዚህን ሰባት አመታት የቀጠለልኝ እሱ አይደለም! የቱ የበለጠ እንደሚያስደስት ግራ ይገባኛል! ከሕመሜ መዳኔ ወይስ ያዳነኝ የኔው ልጅ አስራት መሆኑ! የሰራሁት ሰው መልሶ እኔን ሰራኝ! ከድሮውኑም ሳስተምረው ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ አውቀው ነበር። ታዲያ ከሰዎች ጋር ሆኜ ሳገኘው ‘የየኔታ ልጅ ነኝ። መምህሬ ናቸው።‘ ብሎ ልቤን በኩራት ይሞላው ነበር።"

(የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የልጅነት መምህር ለ"የካቲት" መጽሔት የሰጡት ምስክርነት)

※※※

እስቲ ስለ ፕሮፌሰር አስራት የህክምና ገድል ደግሞ በመጠኑ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ―ለኢትዮጵያ አንድነት የታገሉ ―የቀዶ ጥገና ሐኪም፣ የዩኒቨርስቲ ዲን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ እና የፖለቲካ እስረኛ የነበሩ ―ኃይለሥላሴ በ1967 እስከሞቱ ድረስ የግል ሀኪማቸው የነበሩ ―አለምአቀፍ የቀዶ ጥገና ሐኪም ለመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የነበሩ ―በምእራቡ አለም፣ የረቀቀ የህክምና ቴክኖሎጂ ባለበት ቦታ፣ በትልቅ ደሞዝ እንዲሰሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ ገሸሽ አድርገው በአስቸጋሪ ሁኔታ እና በትንሽ ደሞዝ ሃገራቸውን ለማገልገል የመረጡ ―በ1977 የድርቅ ዘመን በቀዶ ጥገና ጥበባቸው የጋርዲያኑን ጋዜጠኛ የፈወሱ ―በ1986 ወያኔ ከዩኒቨርስቲ ካባረራቸው 21 አማራ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች አንዱ የነበሩ ―በዛው አመት መአህድን(መላው አማራ ህዝባዊ ድርጅትን) መስርተው በሊቀመንበርነት የመሩ ―በዚሁ ፓርቲ አማካኝነት ለአማራ ጥቅምና ለኢትዮጵያ አንድነት ሲታገሉ ከ1987 ጀምሮ ለሁለት አመት የታሰሩ ―በሐሰት ክስ ላይ የሐሰት ክስ እየተደረበባቸው ለተጨማሪ ሶስት አመታት የታሰሩ ―በእስር ወቅት ከእስረኛ እንዳይገናኙ ለብቻቸው ጨለማ ቤት የተዘጋባቸው ―አስራት ሐቀኛ ፣ ትሁት የነበሩ ቢሆንም የፖለቲካ ሰው ያልነበሩ (መጠላለፍና ሽኩቻ የሚበዛው የሃገራችን ፖለቲካ ከአስራት ድንቅ ሰብእና ጋር የሚሄድ አልነበረም) ※※※

በመጨረሻ ብዙዎችን የፈወሰው የፕሮፌሰሩ እጅ በካቴና ታስሮ በወያኔ ወህኒ ቤት ማቅቀው ሞተዋል።

~ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው

Report Page