...........................

...........................

Yohannis_Et

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ አዳራሽ ጥቂት መቀመጫወች ሲቀሩት በተማሪዎች ተሞልቷል። አሁንም በሁለቱም በሮች ያለማቋረጥ ተማሪዎች እየገቡ ነው። እንደ እውነቱ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ከደቂቃዎች በሇላ የቀሩትም የአዳራሹ መቀመጫዎች ሞልተው ለተማሪዎች መቀመጫ እንደሚጠፋ ግልፅ ነው:: እኔ በሶስተኛው የመቀመጫዎች ረድፍ በቀኝ ግድግዳ በኩል ብቀመጥም እጅግ የተዋበው የአዳራሹ መድረክ በሙሉ ይታየኛል። መድረኩ ላይ ሙሉ በሙሉ በመስታወት የተሰራ ሰፋ ያለ ጠረጵዛ አለ። ጠረጴዛው በፊቱ በኩል ለታዳሚው ትዩዩ ሆኖ የዩንቨርሲቲውን አርማ የያዘ <ስቲከር> ተለጥፎበታል:: ከጠረጴዛው ጀርባ አራት ዘመናዊ ወንበሮች የእለቱን ተረኛ መድረክ መሪ በኩራት እየተጠባበቁ ነው:: ስልኬን አንስቼ ሰዓት ለማየት ስሞክር 2:27 ብሏል። የአዳራሹ በሮች ሊዘጉ 3 ደቂቃዎች እንደቀሩ ሳስተውል ዘወር ዘወር ብዬ አዳራሹን በወፍ በረር ቃኘሁት። እንደገመትሁት ነው ሙሉ መቀመጫዎች ተይዘው የአዳራሹ የጀርባ ግድግዳ ላይ የቆሙ ተማሪዎች አሉ:: ብዙም ሳይቆዩ ሚያዚያ 21/2013 ዓ.ም ለጠዋት 2:30 የተቀጠረውን በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁኔታ ላይ የአዲሥ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን ውይይት ለመምራት የተመረጡ ሁለት ፕሮፌሰሮች ከዩንቨርሲቲው ዲን ጋር በመድረኩ መግቢያ ገብተው እጃቸውን እያነሱ ሠላምታ እየሠጡን ወደ መቀመጫቸው አመሩ። አንድ ደቂቃ ከማይሞላ ራስን የማዘጋጀት እንቅስቃሴ በሆላ ስልሳዎቹን ያገመሱ የሚመሥሉት የዩንቨርሲቲው ዲን የድምፅ ማጉያውን ከመርሀ ግብሩ አስተባባሪዎች ተቀብለው "እንደምን አደራችሁ?" አሉ የተለመደው ፈገግታቸው ሣይለያቸው። ፕሮፌሰር ዘነበ ቀደም ብለው በዩንቨርሲቲው የጤና ፋካሊቲ በማሥተማር የቆዩና ከሁለት አመት በፊት የአዲሥ አበባን ዩንቨርሲቲ እንዲመሩ የተሾሙ ናቸው። ምንም እንኳን በእድሜ የበሰሉና የፕሮፌሰርነት ማዕረጋቸውንም ከእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ የተቀበሉ ቢሆንም ከተማሪዎች ጋር ያላቸው ቅርርብ ግን እንደ አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ያሥመሥላቸዋል።

"..ቀድመን እንዳሳወቅናችሁ" አሉ ፕሮፌሰር... "ቀድመን እንዳሳወቅናችሁ ዛሬ ሀገራችን ስላለችበት አስቸጋሪ ሁኔታና ስለወገኖቻችን መቸገር እንዲሁም ስለእናተና በየትኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስላሉ ወንድም እህቶቻችሁ ሁኔታ ልናወያያችሁ ፈልገን ነው ዛሬ ይህን መድረክ ያዘጋጀነው። ..በርግጥም የምነግራችሁ በዚህ ጉዳይ በተለያየ ወቅት የሀገሪቱ ሙህራን ከየ ዩንቨርሲቲውም እየተሰባሰብን በሌላም ዘርፍ ያሉትን እያካተትን ብዙ ጊዜ ለመወያየት ሞክረናል፤ ሆኖም በውይይቱ በመፍትሔ ሀሳብነት መልካም መልካም ሀሣቦች ቢነሱምና ወደ ተግባርም ለማውረድ ሰፊ ጥረት የተደረጉ ቢሆንም አሁንም ግን የችግሩን አሳሳቢነት እንደምታዩት ነው ይባስኑ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው::" ..ብለው የድምፅ ማጉያውን ከአፋቸው ገለል አድርገው ለአፍታ ፀጥ አሉ። ቀና ብለው ቀጠሉና...

"..ለዚያ ነው ዛሬ እናተን ብንሰበስባችሁም ውይይታችን ግን እንደተለመደው እኛ ከዚ በፊት ስለተሔደባቸው መንገዶች እያነሳን እናንተን የማናነጋግረወው፤ ይልቁንም ዛሬ እኛ እናንተን ብቻ ልንሰማችሁ መጠናል። ብልህ ታናሹን ይሠማል ነውና ዛሬ እኛ በእድሜ ከፍ ብለን ማዕረግ ብንጭንም ከመካከላችሁ ግን እኛ ያልታየንን የሚያይ ያልተረዳነውን የሚረዳ የልጅ አዋቂ እንደሚኖር ርግጠኛ ነኝ ስለዚህ..." ሲሉ አዳራሹ በአንድ ጊዜ በጭብጨባ ቅልጥ አለ። "..ስለዚህ ዛሬ አንደበታችንን ሳይሆን ጆሯችንን ልንሰጣችሁ መጠናልና እናተ ልጆቻችን በልባችሁ ያለውን የሚሠማችሁን ሁሉ እያወጣችሁ እንድትነጋገሩና እኛም ንግግራችሁን እንድናደምጥ በማክበር ነው ምጋብዛችሁ።..ምናልባት ተጨማሪ ነገር ካለ ለወንድሞቼ ተራውን ልስጥ" ብለው የድምፅ ማጉያውን ከቀኛቸው ለተቀመጡት ለወጣቱ ፕሮፌሰር ለፕሮፌሰር እስክንድር ሰጧቸው። ተማሪዎችም ንግግራቸውን በጭብጨባ አሳረጉላቸው። በእድሜ ከሁለቱም የሚያንሱት ፕሮፌሰር እስክንድር በቀዩ ፊታቸው የሞላውን ጥቁር ፂማቸውን በግራ እጃቸው እየነካኩ...

 " ..እ..እሽ! እንዴት አላችሁ? ..በርግጥ ፕሮፌሰር የሚባለውን ሁሉ ብለዋል እሳቸውም እንዳሉት ዛሬ ልናዳምጥ እንጂ ልንናገርም ስላልመጣን እኔ የተለየ ምለው ነገር የለኝም.. እንዲያው ማጉያውን ከሰጣችሁኝ አይቀር አንድ መልዕክት ላሥተላልፍ.." አሉና.....

"..የመግቢያ ሰዓት ስላለፈ የአዳራሹ በሮች ቢዘጉ መልካም ነው መረባበሽ እንዳይኖር..." ብለው ፈገግ ሲሉ ነበር እኔም በሮቹ እንዳልተዘጉ ያሥተዋልሁት:: አስተባባሪዎቹም ፍጥን ብለው ከላይና ከታች በሮቹን ዘጓቸው። እሳቸውም ቀጠሉ....

"..ንግግር ይኖራቸዋል ብዬ ባላሥብም ምናልባት መከልከል እንዳይሆንብኝ ግን..." ብለው የድምፅ ማጉያውን ከግራ ጫፍ ወደ ተቀመጡት ፕሮፌሰር ብርሃን ለማድረስ ሲሞክሩ ፕሮፌሰር ብርሀን የአልፈልግም ምልክት በእጅና በጭንቅላታቸው ሰጧቸው::

"..መልካም እንግዲያውስ ወደ እናተ እንምጣ... አሁን እጃችሁን እያሣያችሁን ሀሣባችሁን በየተራ ታካፍሉናላችሁ.. ለሁላችንም መልካም ጊዜ ይሁንልን" ብለው ማጉያውን ጠረጴዛ ላይ ሲያስቀምጡት እንደተለመደው ሞቅ ያለ ጭብጨባ አዳራሹ ውስጥ ተስተጋባ።

...ከመድረኩ ላይ የተቀመጡት ሶስቱም ፕሮፌሰሮች በአይኖቻቸው አዳራሹን መዳሰስ ጀመሩ። መልዕክቱ ለኔም ያልሆነ ይመሥል ከነሱ ባልተናነሰ ሁኔታ ነበር ተዟዙሬ ያየሁት:: ገና በመጀመሪያው ብዙ እጆች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ:: ፕሮፌሰር ዘነበ እጃቸውን ከአዳራሹ መሀል እየጠቆሙ አንገታቸውን በይሁንታ ነቀነቁ..የንግግር ፈቃድ ለመሥጠት መሆኑ ነው:: ድምፅ ለመሥማት ያለው ጉጉት የፈጠረው ይመሥላል አዳራሹ ከቀድሞ ሁኔታው በተለየ ፀጥ አለ:: እኔም እንቅስቃሴዬን ሁሉ አቁሜ ጆሮዬን ከፍቼ ሳለሁ "እሽ..አመሠግናለሁ" የሚል የሴት ድምፅ ስሰማ "በአዳራሹ ውስጥ ለምረጡኝ ከተዘረጉ እጆች መሀል ይህቺ ሴት መመረጧ መቼስ <አፈርማቲቭ አክሽን> መሆኑ ነው..በዚች እንኳን ቅድሚያ ለሴቶች ተባለ? ለነገሩ እንዲያውም እነሱን ለማሥቀደም ትክክለኛው ቦታ ይሄ ነው ለዘመናት ድምፃቸው ታፍኖ ኖረው የለ?!..ድምፃቸውን ለመሥማት ከማስቀደም የበለጠ <አፈርማቲቭ አክሽን> የሚለውን ሀረግ የሚገልፀው አይኖርም.." እያልሁኝ በውስጤ ሳጉረመርም ልጅቷ ንግግር ጀምራለች።

"...እናም እኔ በጉዳዩ ላይ የተለየ እይታ አለኝ ብዬ ባላሥብም የሚሠማኝን መናገሩ መልካም ነው ብዬ ስላሠብሁ ነው::" ብላ ቀጠለች...

"...እኔ እንደሚሠማኝ ከሆነ 'በዚህ ቦታ ለተፈጠረው ችግር እንደዚህ አይነት መፍትሔ ያሥፈልጋል..በዚያ ላለውም እንደዚያ አይነት' እየተባለ በየዘርፉ ለሚፈጠሩ ችግሮች የሠላም እጦትና ግድያዎች ወቅታዊ ውይይት ማድረገና ዘርፋዊ መፍትሔ መፈለጉ ልክ ነው ብዬ አላሥብም:: ..ለምሳሌ እንደነገርሆችሁ እኔ ከመጣሁበት የደብረ ብርሃን ከተማ ብዙ ሳይርቅ በዚያው በዞኑ ሲፈፀም የነበረውን እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የምናውቀው ነው እና..." ..ስትል እኔ ስለ <አፈርማቲቭ አክሽን> ከራሴጋ በማወራበት ጊዜ ማንነቷንና የመጣችበትን አካባቢ ገልፃ እንደነበር ገመትሁኝ።

..ቀጠለች.."በሌላም አካባቢ በየመንገዱ መኪናዎች በግዳጅ እየቆሙ ክበር የሆነው የሰው ልጅ ሂወት በአሰቃቂ ሁኔታ እየተቀጠፈ ነው፤ ቤት ተዘግቶ በዚያው በሳት ነደው የሞቱት ስንት ናቸው? የተሠደዱት የተፈናቀሉትንማ አናንሳ:: በሌላም በኩል እንደ እኛ በየ ግቢው እንማራለን ብለው በዚያው የቀሩ እህት ወንድሞቻችን ከበቂ በላይ ሆነው ሳለ ዛሬም ግቢዎቻችን ከስጋት ነፃ አልሆኑም...

...እንግዲህ ይቺ ሀገር ዛሬ ያለችወትን ሁኔታ እኔ ማብራራት ያለብኝ አይመሥለኝም አለም የሚያውቀው የአደባባይ ሚስጥር ነው.. ስለዚህ እኔ ወደ ሀሣቤ ልመለሥና ካሥተዋላችሁት ለዚ እየሆነ ላለው ሁሉ ጥፋት መንግስትም ሆነ ሌላው አካል የተናጠል መፍትሔ ነው ለመፈለግ ሚሯሯጠው:: ጥይት ሲፈነዳ ድምፁ በተሠማበት ሰፈር እንቅስቃሴ ታያላችሁ.. ማህበረሰባዊ ግጭት ሲፈጠር እንቅስቃሴው ጫጫታው ወዳለበት ሲዞር ታዩታላችሁ... እንዴ! ግን ይሄ መፍትሔ አይሆንም! በዚ ሁኔታ ምናልባት ለጊዜው ነገሩን ልናስታግስ ብንችል እንጂ ይቺን ሀገር ከገባችበት ስቃይ የሚያወጣ ዘላቂ መፍትሄ ልናገኝ በፍፁም አንችልም::" አለችና ለአፍታ ርፍ ብላ ቀጠለች...

" እስኪ አስቡት..! እኔ የገበሬ ልጅ ነኝ እና ቤተሠቦቼ በማሣቸው ላይ ጎርፍ ሲገባባቸው አንድ ወይም ሁለት ተክሎች በጎርፍ ተነቅለው ያገኛሉ ነገር ግን እነዚያ ተክሎች አካባቢ አይደለም ጎርፉን ለማቆም የሚታገሉት:: ምናልባት እዚያ አካባቢ የተወሰደውን አፈር ለመተካት ተጨማሪም እንዳይወሰድ ቆፍረው አካባቢውን በአፈር ይከትሩታል። ነገር ግን ያ ክትር ያችኑ አካባቢ ከጎርፍ ቢያድን እንጂ ጎርፉ አቅጣጫ ቀይሮ በሌላው የማሣው ክፍል እንደሚፈስ ስለሚያውቁት በቃን ብለው አይቀመጠም። ይልቁንም ገና ከማሳው ጫፍ ከውጭ ጀምረው የመሬቱን ዳር እየቋፈሩ ጎርፉን ከማሣው ውጪ እንዲፈስ ያደርገታል እንጂ። ..በዚህ መንገድ ሙሉ ማሣውን ከጎርፍ ይታደጋሉ። 

..የሀገራችንም ሁኔታ ይሄው ነው! በየ ሠፈሩ ለሚሠማ ጩኸት መልስ ሳይሆን ችግሩ እንደ ሀገር ነውና ሀገራዊ የሆነ መፍትሔ መፈለግ ላይ ቢሠራ መልካም ነው እላለሁ:...አመሠግናለሁ::" ..ብላ ስትቀመጥ ጩኸት የተቀላቀለበት ጭብጨባ ተደረገ..ያው እኔም ሀሣቧን ስለወደድሁት እጀ በፈቀደ ሞቅ አድርጌ አጨበጨብሁ::

"..በእውነት ዛሬ ከውይይታችን ትልቅ ነገር የምናገኝ ይመሥለኛል... መልካም ጅማሮ ነው እስኪ እንቀጥል..." አሉ ባለ ፈገግታው ፕሮፌሰር ከነ ሙሉ ፈገግታቸው። በዚያው እድል ሠጠው ድምፅ ማጉያቸውን ቁጭ አደረጉት።

በተመሣሣይም "አመሠግናለሁ..." ሲል ቀጠለ ጉርምስናውን የድምፁ መጎርነን የሚያሣብቅበት ተረኛ ተማሪ::

"..እህታችን የተናገረችውን ንግግር ሳላደንቅ አላልፍም..በእውነቱ እኔም በእርሷ ሀሣብ እስማማለሁ ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሔ ካልተፈለገ በአጭር ጊዜ ይቺ ሀገር ላትመለስ እንደምትወድቅ ነው ሚሠማኝ:: ልብ ካልነው በተናጠል የሚደረገው ሩጫ በጋራ ከሚደረግ ርምጃ ያነሰ ፍጥነት.. በተናጠል የሚሠነዘር ቡጢም በጋራ ከሚደረግ ግፍተራ ያነሰ ጉልበት እንዳላቸው ግልፅ ነው:: ከዚህም በላይ ደግሞ እህታችን እንዳለችው ችግሩ ሀገራዊ ነውና ይህን አካሄድ እንድንከተል ያስገድደናል።" አለና....

"..ይሄን ብዬ እኔም ልጨምር የፈለኩትን ነገር ልበል... በየ እለቱ እንደምንሰማውና እንደምንመለከተው ለተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ተብሎ ሚጠቀሰው የብሔር ጉዳይ ነው:: ..አዎ! እዚ ሀገር እከሌ ብሔር የእከሌን ብሔር ተወላጅ ገደለ አረደ አቃጠለ... ሁሉም እንደዚ ነው:: ስለዚ ምናልባት ይሄን ችግር ለመቅረፍ ከላይ ያሉ ባለስልጣናት ሳይቀር ወደታች ወርደው ሁኔታውን ለማየትና በየ ብሔሮች ላይ ለሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሚሆኑ አለመግባባቶችን ከስሩ ለማጣራት መሞከር ያለባቸው ይመሥለኛል:: እስከምናውቀው ድረስ አሁን ያለንበት ሁኔታ ባለ ስልጣናቱ በተዋረድ ነው መረጃ ሚሠበስቡት ..በመንደር ያሉ አደረጃጀቶች ለቀበሌ መረጃ ይሰጣል ቀበሌው ለወረዳ፣ ወረዳው ለዞን፣ ዞኑ ለክልል፣ ክልሉ ደግሞ ለፌደራል ባለስልጣናት ያሣውቃሉ። ታዲያ ይሄ ሲሆን ግን ገና ከመንደር ጀምሮ እስከላይ ባሉ ተዋረዶች ሁሉም ባለስልጣኖች ራሳቸውም የማህበረሰባቸው አካል ናቸውና የራሳቸውን አካባቢ ችግር እየደበቁ የሌላውን እያጎሉ ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂውን ሌላው እያደረጉ ራሳቸውን አስውበው ነው ወደላይ መረጃ የሚልኩት። ይህም ሲሆን ለፌደራል ባለስልጣናት የሚደርሰው መረጃ ባናየውም ለመገመት የሚከብድ አይደለምና ሁሉም ጣት ቀሳሪ የሆነበት መረጃ ነው ሚደርሰው። ስለዚህ ምላሽ ለመሥጠት አመች ሁኔታ በፍፁም ሊፈጠርና ችግሩን ለመቅፈረፍ አይቻልም። ለዚህም ነው ብዙ ቢሠራም ውጤት ማምጣት ማይቻለው ስለዚ ከላይ ያሉት ወደታች ወርደው ሁኔታዎችን ሊያጠኑ ይገባል። በሌላም በኩል ሙህራኑም እንደባለድርሻ በዚህ ላይ የበኩላቸውን ቢያደርጉ መልካም ነው እላለሁ። " ብሎ ቁጭ አለ። የተለመደ ጭብጨባ...

የአዳራሹ ድባብ ሞቅ ብሏል ለተሳትፎ የሚዘረጉ እጆችም ሲጀምር ከነበረው በብዙ ጨምሯል:: እነ ፕሮፌሰርም በተማሪዎቹ ንግግሮች በየመሀሉ ጎምበስ ቀና እያሉ ማሥታወሻዎቻቸው ላይ ይፅፋሉ..አንዳንዴም ራሳቸውን እየወዘወዙ በሀሳቦቹ ላይ ያላቸውን አብሮነት ያፀናሉ። ከዚያም በግራዬ በኩል ከመሀል አካባቢ አንድ ረዘም ብሎ የቀጠነ ወጣት እድል አግኝቶ ብድግ አለ። የድምፅ ማጉያውን ለመቀበል ገና ከሩቅ እጁን ሲዘረጋ ሳይ የውይይቱ ሂደት በውስጡ እንዲናገር ያስገደደውን አንዳች ሀይል እንደፈጠረበት ተረድቼ ነበርና "እስኪ ስጡት ይተንፍሰው!" አልሁ በልቤ።

..ወጣቱ ግን ማጉያውን ተቀብሎ ዝም አለ። የድምፁ መቅረት ሲያሣሥበኝ ዘወር ብዬ ለማየት ስሞክር በቀኝ እጁ ማጉያውን አፉ ጋር አድርጎ አንገተን አዘቅዝቋል። ቀና አለና...

"..እህ..እህህ" አለ እንደ ሳቅ ቢጤ... የአዳራሹን ትኩረት የኔን ጨምሮ የበለጠ ሳበው...:: ፊቱን መልሶ ኩስትር አደረገውና ወደ መድረኩ እየተመለከተ "መምህር " ሲል ንግግሩን ጀመረ። 

"መምህር..በርግጥ እንዲ ማሠባችሁ መልካም ነው። እናተም ወንድም እህቶቼ የተሠማችሁን ለመናገር የሚነገረውንም ለመሥማት አዳራሹ እስኪሞላ መሠባሠባችሁ ጡሩ ነው። ግንኮ..." አለና ያችው ሲጀምር የሠማናትን ሳቅ "እህ..." ብሎ አሰማንና ቀጠለ..

 "ግን ችግራችንኮ አዳራሽ ተሠብስቦ በማውራት የሚቀረፍ አይደለም" ሲል.. "እና እና በአደባባይ በመደባደብ ነው የሚሥተካከለው? መቼስ ሰልፍም ሰላማዊ መሆኑ ከቀረ ሰነባብቷል...ምነው ማይሆን ነገር ከመናገሩ በፊት በተቀመጠ" አልሁኝ.. በልቤ ነው። ሥሜታዊ እየሆነ እንደሆነ ስላሥተዋልሁ መጥፎ ንግግር ውስጥ እንደሚገባ ገምቻለሁ:: እሱ ግን የሚያቆም አይደለም ቀጠለ...

"..ወገኖቼ ይሄ እንዴት አይነት ቂልነት ነው?..ቆይ በየትኛው ዘመን በየትኛውስ ሀገር ነው ጥፋትን ለማረም አጥፊ ሚወያየው? ችግርን ለመፍታት ችግር ፈጣሪ ሚማከረው? ሞት ለማሥቀረት ገዳይ የሚነጋገረው? እ?!" ብሎ አሁንም ድርቅ ሲል.. ነገረኛው ልቤ "እርፍ...በላ አጥፊ ናችሁና ውጡ አትወያዩ በለን" አልሁኝ:: እሱም ቀጠለ...

"..ንገሩኝ እስኪ ይቺ ሀገር የምትታመሠው፤ ቤት የሚፈርሰው ደም የመፈሰው በማን እጅ ነው? በገዛ እጃችን አይደለም እንዴ? ወገኖቻችን ቢሞቱ ቢሠደዱ የምንገላቸው የምናሳድዳቸው እኛው አይደለንም እንዴ?! እና በየትኛው ድፍረታችን ነው ዛሬ እዚ ልንወያይ የተቀመጥነው? ምናልባት እንዲህ ስል ከናተ መካከል "የለም የሞተ እገሌ ነው የገደለ ደግሞ እገሌ.." ብላችሁ ራሳችሁን ለማውጣት ወይም ራሳችሁን ተጠቂ ለማድረግ ትሞክሩ ይሆናል.. ምን አደባበቀኝ እንደዚ ሚያሥብ ካለ እሱ ማሠብም ማሥተዋልም የተሣነው ግዑዝ ነው:: እንዴት ነው ከአንዲት ሀገር ሟችና ገዳይ ተብሎ ሊከፈል የሚችለው? ኢትዮጵያ ማለትኮ ብዙ ቅርንጫፍ ያላት አንድ ዛፍ፤ ብዙ አካላል ያላት አንድ ሰው ነች። እስኪ ማንኛችሁ ናችሁ በቀኝ እጃችሁ ግራችሁን በቆንጨራ የምትቆርጡት ወይም በእጃችሁ እግራችሁን የምትቆራርጡት? ..እኔ የማውቀው ለጭንቅላት የተወረወረን ድንጋይ በእጅ ስንጋርድ ነው። እኛ ደግሞ በእጃችን ጭንቅላታችንን እንመታለን:: እና እጄ ጭንቅላቴን ደበደበብኝ ብሎ ክስ ከሚቆም ተጠቂ በላይ ..ጭንቅላቴን ደበደብሁ ብሎ በጀግንነት ከሚገሰል አጥቂ በላይ ቂል አለ? እስኪ ንገሩኝ?! በእኛ ሀገር እየሆነ ያለው ይሄው ነው.." ሲል አዳራሹ በጩኸትና በጭብጨባ ድብልቅልቁ ወጣ:: ልጁ ግን አቁሙ በሚመሥል ሁኔታ እጁን ብድግ አደረገና ከፀጥታው አስከትሎ ንግግሩን ቀጠለ።

"..ለምን ትሉኝ ይሆናል ግን..ጭንቅላት ተጠቃሁ ብሎ ቢከስ ቢያሥፈርድም እጁን ነው ሚያጣው.. ሌላ ጉዳት፤ እጅም አጠቃሁ ብሎ ቢከራከር ጥቃቱን ቢያከብድ ጭንቅላት አልባ ሆኖ ነው ሚቀመጠው። ወገኖቼ በመጨረሻ ማናቸውም በድላቸው ይጎዳሉ እንጂ አይጠቀሙም። ..ያም አልበቃ ብሎ ችግር እንፈታለን ብለን ይሄው ለውይይትም ተቀምጠናል..ታዲያ ከእኛ በላይ ማፈሪያስ አለ?! ቆይ እኛ ማን ነን? እንዴት ነው ለዚች ገናና ሀገር ችግር ልንፈታ የተቀመጥነው? 

..ልቦና ካለን ራሳችንን የዚች ሙሉ ሀገር አንድ አካል ክፍል እንደሆን ሀቁን ተቀብለን እጅ ፊትን ከጉዳት እንደሚከልል እየተጠባበቅን ፤ አፍንጫ ሲመታ አይን እንደሚያለቅስ በሌላችን ላይ ከውጭ ጉዳት ቢደርስ አንዳችን እያለቀስን እንኑር! አይ ካልህ ግን እያንዳንድህ ማንንም አትጎዳም እግርህን በእጅህ እየቆረጥህ ትጥላለህ እንጂ!

...ብሎ ያሥለመደንን ፈገግታውን አደረሰንና "..ይቺን ሀገርኮ አታውቋችም ወገኖቼ ሀገራችንን አናውቃትም! እስኪ ሁሉንም ተውትና ከ3000 አመት በላይ ስላሣለፈችው ታሪክ ለማወቅ ሞክሩ። ጠይቁ እውነት ተናናሪ ብታገኙ፤ እውነት ፀሀፊም ብታገኙ መፅሀፍቱን አንብቡ። ያኔ ሀገራችሁን እንደማታውቋት ታሥተውላላችሁ:: ..ናከን አትበሉኝ ግን ሀገራችሁን ብታውቋት ይሄን አስተሳሰባችሁን ይዛችሁ ችግሯን ልትፈቱ ባልተሰባሠባችሁ ነበር። አልበቃም ብሎ 'ችግሯን ካልፈታነው ሀገራችን ትጠፋለች ባላላችሁ ነበር ' ..አይይይ! እንግዲያውስ ቁርጥህን እወቅ ወገኔ!! እንደተናገርሁት ነው ልቦናህን አጥፍተህ አካልህን በአካልህ እየቆራረጥህ እጅህን በአፍህ ከሰህ እያስቆረጥህ ራስህን ይዘህ ትጠፋለህ እንጂ ኢትዮጵያስ አትጠፋም!! "

..ንግግሩ ውስጤን እየነካው ብዙ ጊዜ ለማጨብጨብ ፈልጌ ነበር ግን ከጅምሩ ያቋረጠውን ጭብጨባ እያሠብሁ ..ንግግር ሲጀምር "ዝም ባለ" በማለቴ ራሴን እየወቀስሁኝ ከልቤ ማዳመጤን ቀጠልሁ።

"..ኢትዮጵያ አጠፋም ወገኖቼ! ጎርፍ አፈር ቢወስድ እድፉን ይጠርጋል ቁጥር ይቀንሳል እንጂ አፈር አያጠፋም ..እሳት ወርቅን ቢያነድ ጉድፉን ለይቶ ምርጠን አንጥሮ ያወጣዋል እንጂ ወርቁን አያጠፋውምና ልብ ያለህ ልብ በል የምንለማመነው ራስህን ከጉድፍ ከእድፍነት እንድትለይ ነው። አይ ካልህ እሳት ይበላሀል እትዮጵያ ግን በእሳት በነጠሩ ወርቆች እጅ እግሯን አጠንክራ የተሠወረውን ክብሯን በአለም ትገልጣለች እንጂ እመነኝ ወገኔ ይቺ አገር አጠፋም! " ...ብሎ የግራ ክንዱን ቀና ሲያደርገው ከመዳፉ በታች አረንጎዴ ቢጫ ቀይ ጨርቅ በእጁ ላይ ታስሯል።..ውስጤን አንዳች ስሜት ይረብሸኝ ጀምሯል... ልጁ ግን የሚያቆም አልሆነም።

"..ለእኛ ግን ገለን ልንኖር ለምንጥረው አካላችንን ለምንቆርጠው እውነቱን ላልተረዳረው.. ለኛ ግን ወየውልን!..ወዮታ አለብን!" አለ በተሠበረ አንደበት.... 

"..ወየውልን! ራሳችንን ሳናውቅ ለኖርነው ክብራችንን ላልተረዳነው ለኛ..ከወርቅ መሀል እድፍ ሆነን ነደን ለምንጠፋው ለእኛ ግን ወዮታ አለብን..." ..ሲል የእምባ ሲቃ ተናነቀው። " ...እ..እ.ስኪ ንገ..ሩኝ ቆይ ማ..ማን......" 

..እምባው በፊቱ ሞላ አንደበቱም ተያዘ ..ፊቱን ሳይዞር የቀኝ እጁን ወደ ጎን ዘርግቶ የድምፅ ማጉያውን እንዲቀበሉት እያወዛወዘ በግራው እጀ በታሠረችው ጨርቅ ፊቱን በእልህ ያሸዋል። ፕሮፌሰር እስክንድርም ተቀበሉት በሚመሥል ሁኔታ እጁን አወናጨፈ። ከጎኑ ከተቀመጡት አንደኛው ተማሪ ማጉያውን ሲቀበለው ወንበሩ ላይ ቁጭ አለ:: አዳራሹ ፍፁም ፀጥ ከማለቱ የተነሳ ቲንሽ ኮሽታ እንኳን ከሩቅ ትሰማ ጀመር:: እነ ፕሮፌሰር አይኖቻቸውን በያቅጣቸው ወርውረው ትክዝ አሉ። እኔም ወንበሬን በጀርባዬ ወደኩበትና ጣራ ጣራ እያየሁ በሀሣብ ተወሠደሁ። በዚህ ሁኔታ ለጥቂት ጊዜ ከቆየን በሇላ የዩንቨርስቲው ዲን የድምፅ ማግያቸውን ብድግ አድርገው የተማሪውን ትኩረት ለመሠብሰብ ይመሥላል...

"..እሽ " አሉ...

"...ስለ እውነት በሀገራችን ጉዳይ ስሜታዊ ብንሆን ጥፋት አይሆንብንም ነገር ግን አንተ ተረጋጋ ወንድሜ " አሉና ውይይቱን ለማሥቀጠል...

"ወደ ሌላ ሀሣብ እንሂድ.." ብለው እድል ሊሠጡ እጅ ለማየት ሲሞክሩ ፕሮፌሰር ብርሃን "አይ " ብለው የድምፅ ማጉያውን ከፕሮፌሰር ተቀበሏቸው::

"..ይመሥለኛል ወንድማችን ሃሣቡን አቋረጠ እንጂ አልጨረሰም ስለዚህ ምናልባት ለመረጋጋት ጊዜ ከፈለገ እንስጠውና ሀሣቡን ቢቋጨው መልካም ይመሥለኛል.. አይደለም?" ብለው ወደ ሁለቱ ባልደረቦቻቸው ዘወር ሲሉ ሁለቱም በይሁንታ አንገታቸውን ነቀነቁ :: እሳቸውም መለሡና ንግግሩን በእንባ ወዳቋረጠው ተማሪ እየተመለከቱ...

"እሽ.. ስትረጋጋ መቀጠል ትችላለህ" ብለው ረዘም አድርገው ተነፈሱ። ልጁም መጠበቅ አልወደደም የድምፅ ማጉያውን ከተቀበለው ተማሪ ወስዶ ብድግ አለና ንግግሩን ድክም ባለ ድምፅ ጀመረ።

"..ብዙ የቀረ ሀሣብ የለኝም ግን ወንድሞቼ እህቶቼ አይናችን ላይ እየሆነ ያለውን የማናስተውል ከሆነ እንዴት የሀገራችን ልጆች አካሎች ልንባል እንችላለን? እንዴትስ በአንድ ሀገር ያውም በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እየኖርን ሁለት አላማ ይኖረናል? ቀኝ እግሩን ወደፊት ግራውን ወደሇላ ሊያራምድ የሚችል ማን ነው? ያለ እጁ የጎረሰ ያለ እግሩስ የተራመደ ማን ነው? እናስተውል!..አንድ ቀን የሚበላ ቀርቦ መመገቢያ እጅ አጠን የምንራብበት ቀን ይመጣል። ዛሬ እርስ በእራሳችን ልንጠፋፋ እንዝታለን እገሌ እገሌን ሊገድል ይደክማል፤ እድል ቢኖረውና ገድሎ ቢጨርስ ግን ይጎድልበታል እንጂ አይሞላለትም.. ምድር ይጠበዋል እንጂ አይሰፋውም ምክንያቱም እግር አጦ የማይራመድና መሬት ጠቦት የማይራመድ ያው የማይራመዱ ናቸው። ስለዚ መሬት ለማሥፋት እግርን መቁረጥ ትርፉ ያው ሳይራመዱ መኖር ነው..."

..በድጋሜ የአዳራሹ ድባብ በተመሥጦ ተቃኘ። ልጁም በለሰለሰ አንደበት ንግግሩን ቀጥሏል።

".. ዛሬ በየ መንገዱ የሠው ልጅ እንደ በግ እየታረደ ይወድቃል እና ሁሉም በየ ደረጃው ስለዚህ ይንጫጫል ግን አርፍደናል ወገኖቼ.. አርፍደናል! ጫጫታው በዚህ አልነበረም...:: ርግጥ ነው ሠው ሲሞት ለቅሶ ጫጫታ ዋይታ የሚገባ ነው ግን እንዲህ አይደለም። ..በፊት ነበር አሉ በደርግ ዘመን የደርግ መንግስት ወጣቶችኝ በግዳጅ ሰብስቦ ለውጊያ ያሠልፍ ነበርና ከየ ክፍለ ሀገሩ ለዚሁ አላማ በመኪና እየዞረ ወጣት ወንዶችን ከቤተሰቦቻቸው በሀይል እየነጠለ ለንግድ እንደሚጫን ከብት ይጭናቸዋል። ያኔ ልጆቻቸው የተወሠዱባቸው እናቶች ከእየቤታቸው እየጮኹ ይከተላሉ። ልጆቻቸው በወታደር ተከብበው በመኪና እየተጫኑ ሲሰባሠቡ እነሱም መኩናውን ከብበው ደረት ይደቃሉ ሙሾ ያወርዳሉ መኪናውም ሲሄድ አቅማቸው እስከፈቀደ እየተከተሉ አልቅሰው ጩኸው ደክመው በየወገኖቻቸው ተደግፈው ወደቤት ይመለሣሉ። ..እንደምታሥተውሉት እነዚህ እናቶች ልጆቻቸው ሲሞቱ አይደለም ያለቀሱት በቁማቸው እያሉ ነው ግን ተጭነው እየሄዱ ያሉት ወደ ሞታቸው እንደሆነ ስላወቁ ነው። ..አያችሁ እነዚህ እናቶች በእውነት ታላቅ ናቸው..." ብሎ አንደበቱን የቁጭት አደረገው። እኔም በልቤ በእናቶች ጀምሮ እኛጋር ሊደርስ እንደሆነ ስለተረዳሁ ንግግሩን በይበልጥ ጓጓሁለት።

"..እኛ ግን አወቅን ስንባል በዘመን የቀደሙንን እናቶቻችንን አልመሠልናቸውም። አረፈድን ያልሇችሁ ለዚ ነው... ገና በፊት ራሳችን ለራሳችን ፊት እንድንዟዟር ውስጣችን ሲመረዝ፤ በአካላችን ላይ በጠላትነት ልንነሳ ሲሆን ወደሞት እንደተጫንን ተረድተን ማንባት ማልቀሳችን ያኔ በሆነ ነበር። ..ዛሬማ ጦርሜዳ ላይ ሊጫወት እንደሚወድድ ቂል ሆነናልና ሠይፉም በደጃችን ነው።

...እንግዲህ ልቦና ካለን ተሠይፎ ከሚሞተው በላይ በቁም ለሞትነው ለራሳችን እናልቅስ ነው የምለው። እነዚያማ የሞቱት አንዴ ነው እኛ ግን በልባችን ክፋት በእየለቱ እየሞትን ነውና እንዲያውም የእነሱን እድል ቢሠጠን ምንኛ ጡሩ በሆነ! ..ነገር ግን አይሆንም...."ብሎ ረፍት ቢጤ ወሰደና..

" ..በስሜት ሠዓታችሁን ተሻማሁ መሠለኝ ይቅርታ አድርጉልኝ" ብሎ ነገሩን ሲቋጭ በስርዓት የተሞላ ጭብጨባ ረዘም ላለ ጊዜ ተሠማ።

"መልካም.." አሉ የዩንቨርሲቲው ዲን ከጭብጨባው መገባደድ በሇላ:: "..እጅግ ልቤን የነካው ንግግር ነው ግን ዛሬ የኔ አድናቆት አያሥፈልግም" ብለው አስተያየት ከመሥጠት ተቆጠብው ፈርጠም አሉና "እንቀጥላ.." አሉ እንደተለመደውም አይናቸውን በአዳራሹ ዙሪያ ሲያማትሩ እኔም አይኔን መልሼ ቀጣዩን ንግግር ለመሥማት አቀረቀርሁና መጠበቄን ቀጠልሁ።

ለቆይታ ያክል ምንም ድምፅ የለም..ምን እንደተፈጠረ ለማየት ቀና ስል የሶስቱም ፕሮፌሰሮች አይን በመገረም አይነት ቅልጭው ቅልጭው ይላሉ። በፍጥነት ዘወር ብዬ በየ አቅጣጫው አዳራሱን ለመመልከት ስሞክር አንድም እጁን ያወጣ ተማሪ የለም። "እንዴ..!" ብዬ በደንብ ሳስተውል በርግጥም ምንም እጅ የለም። "..ምን ሆኑ..?" ብዬ ማሠብ ልቀጥል ስል...

"ያ ሁሉ እጅ የት ገባ?" አሉ ፕሮፌሰር ግራ እየተጋቡ..የኔም ጥያቄ ስለነበር መልሱን ባገኝ ተመኝቼ ነበር ግን ከአዳሪሹ ምንም ምላሽ የለም። በዚ ሁኔታ ደቂቃዎች አለፉ። እነ ፕሮፌሰርም በሁኔታው ግራ ተጋብተው እርስ በእርሳቸው እየተዟዟሩ የማንሰማውን ንግግር ጀመሩ። መቼም ምንም ቢወራ ከፕሮፌሰር ዘነበ ፊት ፈገግታ አይለይም እኔም የሚያወሩትን ሳላውቅ የእርሳቸውን ፊት እያየሁ አብሬ ፈገግ ብያለሁ። ብዙም አልቆዩም ወደ አዳራሹ ተመልሰው 

"ምነው ልጆች ሀሣብ አለቀባችሁ እንዴ?" አሉ ምፀት በሚመሥል ንግግር። ከዚያም ከጀርባ አካባቢ ምልክት አዩ መሠለኝ ወደዚያው እየተመለከቱ..

"መልካም መልካም..እሽ ወንድሜ" አሉ። እኔም "በዚህ ፀጥታ መሀል ለመናገር የደፈረው ማን ነው?" ብዬ ለማየት ስዞር የአዳራሹ ወንበር ሞልቶባቸው የጀርባ ግድግዳ ተደግፈው ከቆሙት ተማሪዎች መካከል ነጭ ቲሸርት ያደረገ ጠይም ልጅ የድምፅ ማጉያውን ተቀበለ። ልጁ መካከለኛ ቁመት ያለው ሲሆን ከራሱ ላይ ከውሃ የተጣሉ ይመሥል ድርቅ ክርድድ ያሉ ረጃጅም ፀጉሮቹ በፈርጅ በፈርጅ ተፈትለው ከግንባሩ ላይ ተበታትነዋል። ከቀኝ ጎኑ ከእሱ አንሶ የማያንስ ልጅ (ጓደኛው መሠለኝ) ቆሟልና እጁን በተከሻው አሳልፎ አቅፎት በግማሽ አካሉን ጭኖበታል። በዚያችው እጁ የተጠቀለለች ማሥታወሻ ቢጤ ይዞ በግራ እጁ ደግሞ ማጉያውን ተቀብሎ ንግግሩን ጀመረ።

"አ..መሠግናለሁ" ..ረፍት ነገር

..ቀጠለ.. "ኧ..ያው እንደምናየው የአዳራሹ ሙድ ብዙ አይነፋም እና ቲቸር.. ለዛሬ ሙዳችንን ያበላሸውን ወንድማችንን እያመሠገንን እኛ ላሽ ብንልና አስፈለጊ ከሆነ እናተ ብትቀጥሉ..." ሲል በፀጥታ የቆየው አዳራሽ በሳቅ ተሞላ። መድረክ መሪዎቹም ከኛ ባልተናነሰ ነው የሣቁት።

"እውነት ነው" አሉ በፕሮፌሰር ዘነበ ሳቅ በተቀላቀለው ንግግር.. "ይህን ነገር እኔም አስተውያለሁ..እና እነ ፕሮፌሰር የተለየ ሀሣብ ከሌላቸው ለዛሬ ውይይታችንን ብናጠቃልለውና እንዳስፈላጊነቱ ወደፊትም እየተገናኘን ብንነጋገር መልካም ይመሥለኛል።" ብለው ማጉያውን ለፕሮፌሰር እስክንድር ሠጧቸው። እሳቸውም...

"መቼም እናንተ ብዙ መቀመጥ አትችሉም አይደል?..ምክንያት እየፈለጋችሁ ማምለጥ ነው" ብለው ሳቅ አሉና "..ስቀልዳችሁ ነው፤ እኔም የተለየ ሀሣብ የለኝም..በቃ ለዛሬ በአጭርም ቢሆን እዚህ ጋር እንጨርስ። በርግጥ ብዙ ማለት ይቻል ነበር ግን ስንገባም እንደነገርሇችሁ መናገር አላማችን አይደለምና በውይይቱ ሀሣብ ያካፈላችሁን ልጆቻችን ፤ እናተም አዳራሹ እስኪሞላ ድረስ የሀገራችሁን ጉዳይ የኔ ብላችሁ ለመወያየት ወደ አዳራሽ የመጣችሁ ተማሪዎቻችን ሁላችሁንም እጅግ እጅግ ነው የምናመሠግነው። ውይይታችንን ቋጭተናልና መገፋፋት እንዳይኖር ቀስ ብላችሁ ተጠባብቃችሁ ውጡ። በቃ መልካም ቀን ይሁንላችሁ።" ሲሉ ተማሪው ሙሉ በሚባል ሁኔታ አንዴ ብድግ አለና ወደ በሮቹ መንቀሳቀስ ጀመረ። እነ ፕሮፌሰርም የግል ወሬያቸውን እያነጎዱ ማሥታወሻቸውን ሰባሥበው በመጡበት የመድረኩ በር በኩል ወጠው ሄዱ።

እኔ ግን እንዲሁ አዳራሹን ለቅቄ መውጣት አልፈለኩም..አንድ በልቤ የቀረ ጉዳይ ነበረኝ። የውይይቱን ማሣረጊያ ንግግር ያደረገውን ባለ ባንዲራውን ልጅ መገናኘት። እውነት ለመናገር አግኝቼ የምለውን አላሠብሁትም፤ ማግኘት መፈለጌም ምክንያቱ ምን እንደሆነ በዉል አልተረዳሁትም ግን በደቂቃዎች የአዳራሽ ውስጥ ንግግር ሙሉ የዳራሹን ድባባብ የኔንም እሳቤ ሙሉ በሙሉ መቀየር ችሏልና ምናልባትም ፈቃደኛ ቢሆንና ከሱ ጋር የማሣልፈው ጊዜ ቢኖረኝ በአስተሳሰቤ ላይ ብዙ ነገር ሊቀይርልኝ እንደሚችል አሰብሁ መሠለኝ። ብቻ ስሜት ገፍቶኝም ሊሆን ይችላል ማግኘት ግን ፈልጌያለሁ። እኔ በግድግዳ በኩል ስለተቀመጥሁኝ ለበሩ ቅርብ ነበርሁና እሱን እስኪደርስ ጠበኩት። አስቀድሜው ከተማሪዎች መሀል ሆኖ በሩን ወጣና ለብቻው ንጥል ብሎ ከአዳራሹ ወደ <ዲጅታል ላይብረሪ> በሚወስደው መንገድ መራመድ ጀመረ። እኔም ከሇላው ተከተልሁትና...

"ምን ብዬ ልጀምር.. ልጥራው እንዴ?

..አይ የሆነ ቦታ እስኪቀመጥ ልከተለው" ብዬ እያሠብሁ ብዙም ሳልቆይ... "እንዴ!..ላይብረሪስ ቢገባ አስወጥቼ ላወራው ነው? አይ!..እድሌ አሁን ነው" አልሁኝና ሮጥ ሮጥ ብዬ ርቀታችንን አጥብቤ "ወንድሜ..ሠላም ቆየህ" አልሁት። ከጎኑ ተቃርቤ ነበርና ዘወር ብሎ "እግዚአብሔር ይመሥገን!..ሠላም ቆየህ?" አለኝ..

"አለሁ..እ.. ይቅርታ ዮናታን እባላለሁ ፤ ካረበሽሁህ ቲንሽ ጊዜ ትሰጠኛለህ? ላናግርህ ፈልጌ ነበር" ስለው...

"እሽ..ህሩይ እባላለሁ፤ ምንም ችግር የለም አትረብሸኝም.. ግን በደና ነው?" ሲለኝ ፊቱ ላይ ግራ መጋባት ይታይ ነበር። እኔም ከዚ በፊት አለመተዋወቃችንና ድንገት ላውራህ ማለቴ ድንጋጤ እንደፈጠረበት አስቤ..

"ኧረ ሰላም ነው! እንዲሁ ጊዜ ካለህ እነ ፕሮፌሰር ያቋረጡትን ውይይት ብንቀጥል ብዬ ነው፤ ..ደግሞ የተቋረጠው ባንተ ምክንያት ነው ብሎሀል ልጁ እና ቅጣት ይሆንሀል" ብዬ ነገሩን በጫወታ ለመቀጠል ስሞክር እሱም ብዙ አላካበደም ሣቅ እያለ "እሱስ ልክ ነህ.. እና ቁጭ እንበል?" አለኝና "እህ..!" ብዬ መሥማማቴን ገልጬለት ከመንገዱ ቲንሽ ተጉዘን ከፊት ባለችው ወደ ላውንጅ በምትወስደው ቀጭን መንገድ ታጥፈን ሄድን።

ላውንጅ እስከምንደርስ ድረስ ምን እንደምለው እንዴት እንደምንጀምር እያሠብሁ እሱን ፀጥ ማለቴ አልታወቀኝም ነበር። ..ደረስንና ከአንድ ቀለል ያለች ዛፍ ስር ባለችው ክብ የፕላስቲክ ጠረጴዛ ዙሪያ ካሉት ወንበሮች የየራሳችንን ስበን ተቀመጥን። የምሳ ሰዓት እየደረሰ ስለነበር "የሆነ ነገር እንዘዝ ምሳ ደርሷል መሠለኝ?" አልሁት.. በዚያው ወሬ ማስጀመሪያ ቢሆነኝ ብዬ ነው።

..በርግጥም ዛሬ ገና መገናኘታችን ስለሆነ የተለየ መልስ አልጠበኩምና እሱም "አይ አያሥፈልግም ባይሆን የሚጠጣ ነገር..." ሲለኝ እሽ በቃ ይዤ ልምጣ "ምን ይሁንልህ?" ብዬ ብድግ አልሁኝ።

"ለስላሳ ነገር ካለ በቂ ነው" አለኝና እሽ ብዬው ላመጣ ወደ ላውንጁ ሄጄ ገባሁኝ። እውነት ለመናገር ለወትሮ የምፈልገውን ነገር ካለሁበት ሆኜ ነበር አስተናጋጆቹን ጠርቼ ማሥመጣው። ዛሬ ግን አጉል ጨዋ ለመሆን ይመሥል ራሴ ላመጣ ሄጄ "ሁለት ስፕራይት ልውሰድ ሰላምዬ.. ግን ደና ነሽ ኣ?" ..ንግግሬንም አላሥጨረሰችኝ

"ኦኦኦ! ዮኒ ዛሬ ማ ሊሞት ነው መጠህ ጠየከኝ.. ደና ነህልኝ" አለችኝ። ሠላም የላውንጁ ባለቤት የወ/ሮ እመቤት እህት ነች፤ እዛው ከመሥራቷ በላይ ፀባዯ ተጫዋችና ተግባቢ ስለሆነች ከኔ ብቻም አይደለም ከብዘ ልጆች ጋር ትቀራረባለች። እኔም... "ኧረ ማንም አይሞትም ስለፈለኩ ነው" ብዬ የበፊት ተቀምጦ የማዘዝ ፀባዬ አጋጣሚ እንጂ ልምድ እንዳልሆነ ለማሥመሠል ሞከርሁኝ። እሷ ግን "እንዴ!!" አለች ድርቅ ብላ። በመጠኑም ቢሆን አስደነገጠችኝና...

"ምንድን ነው? ምን ሆንሽ?" ስላት፤ "አንተ ዮናታን ቆይ ሁለት ስፕራይት ነው ያዘዝኸኝኮ" አለችኝና ፍሪጁን ከፍታ ስፕራይቶቹን አወጣቻቸው።

"አዎ ነው..እና ምን?" 

"ደሞ ያለ ፀባይህ ለመውሰድ ውስጥ ድረስ መጣህ" ..ምን እያሠበች እንደሆነ መገመት አልቻልሁምና "እና ምን ይሁን" ስላት...

"ጓደኛ ይዘሀል..ማለቴ ሴት" ብላ ሳቋን ለቀቀችው:: "ኧረ ሴትዮ አታናጅኝ ያዘዝሁሽን ስጪኝና ልሂድ" ..ምትሰማ አልሆነችም::

"እንዳላይብህ ነው አይደል ልትወስድ የመጣኸው..እንዲያውም አብረን ነው ምንሄደው ሰጥቻችሁ እመለሣለሁ" ብላኝ ከፊቴ ቀድማኝ ወጣች። እኔም ሁኔታዋ እያሣቀኝ ከህሩይ ጋር ወደ ተቀመጥንበት ወንበር ወሰድሇት። ልንደርስ ጥቂት ርምጃዎች ሲቀረን "አንተ ከትልቅ ሰው ጋ ሆነህ ነው እንዴ?" አለችኝ

 "ምን? ማለት?" አልሇት.. ግን ጉዞ ስላላቆምን ከወንበሩ ደረስንና መልስ ሳትሰጠኝ ያች እብድ ልጅ ቀዝቀዝ ብላ "ህሩይ..ሠላም ነው?" አለችው። "እንዴት ነሽ ሰላም..." ሢላት ያው ልጅቷ ከብዙዎች ጋር ስለምትተዋወቅ እሱንም እንደምታውቀው በልቤ እያሠብሁኝ...

"እየውልህ ውዷ ጓደኛችን እኔ ካላቀረብሁላችሁ ብላ መጣች" አልሁትና የመጣችበትን ምክንያት አስቤ እየሳኩኝ ከወንበሬ ላይ ቁጭ አልሁኝ። ሠላም የእሱን ሥፕራይት ከፍታ ፊቱ ካስቀመጠችለት በሇላ "በል አርፈህ ጠጣ" ብላኝ የኔን ገፍተር አድርጋለኝ "በሉ አይዟችሁ.." ብላን ሔደች::

እኔም ልጅቷ ህሩይ ፊት ቀዝቀዝ ማለቷ እየገረመኝ እስፕራይቴን በብርጭቆ ቀንሼ አንዴ ተጎነጨሁና "እና ህሩይ.. እንዴት ነህ ታዲያ?" አልሁት። ፈገግ ብሎ"እህ.. እንደ ሁሉም፣ ማለቴ እንደ ብዙው፤ አንተ እንዴት ነህ?" አለኝ።

"እ? ማለት?" ስለው አሁንም ፈገግ ብሎ ዝም አለኝ እኔም ወሬውን ለማሥቀጠል ...

" ..እኔ ሰላም ነኝ ያው ትምሮ አጨናነቀን እንጂ" አልሁትና ልቀጥል ስል "ምን እየተማርህ ነው? ስንተኛ አመት?" አለኝ አስከታትሎ:: 

"የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ነኝ፤ፈጣሪ ከፈቀደ በዚህ ዓመት መጨረሻ እመረቃለሁ...አንተስ ምን እያጠናህ ነው?" ብዬ ሳየው ፈገግ ያለ ፊቱ ጥቁር አለና "ህግ በሌለበት ህግ መማር አይከውድም?" አለኝ። እኔም ንግግሩ ቢከብደኝም አባባሉ ስላሣቀኝ "ተው.. ተው.. ከፖለቲካ አታነካካኝ" አልሁት፤ እንደውነቱ ከጥያቄው ማምለጫ ብዬው ነው።

"..ሣትነካው ነክቶህ የለ የት ታመልጠዋለህ" ብሎ ፍርጥም አለና "ከየት አካባቢ ነህ?" ሲለኝ ወደፊት ከሱጋ እንድንቀራረብ እያሠብሁ ነበርና የመጣሁበትን አካባቢ ብነግረው ምናልባት እሱ የኦሮምያ ወይም የትግሬ ልጅ ቢሆን ከሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ግንኙነታችን በአጭር ይቀር እንዴ? ብዬ ለአፍታ አሰብሁ። በቅፅበትም አዳራሽ ውስጥ ሲናገር የነበረው ንግግር ትዝ ብሎኝ ራሴን ታዘብሁትና...

"የጎንደር ልጅ ነኝ..ማለቴ ነበርሁ" አልሁትና ሳቅ አልሁኝ። ነኝና ነበርሁ በማለቴ ግራ ተጋብቶ ይመሥላል "ማለት?" አለኝ። 

"ማለትማ... እ..ቤተሠቦቼ ያሉት እኔም ተወልጄ ያደኩት ደቡብ ጎንደር ነው ግን..." ብዬ ገና ከመገናኘታችን በውስጤ ያለውን መናገሬ ልክ ስለመሆኑ ግራ እየገባኝ ቲንሽ ቆየሁ። እሱም ላለመጫን መሠለኝ ዝም አለኝ...ወሠንሁ።

"..ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ከዚሁ አንድ ልጅ ተዋውቄ ነበርና እሷ የአዲሥ አበባ ልጅ ነች። ፈጣሪ ከፈቀደ <ከግራጁዬሽን> በሇላ ልንጋባ አስበናል። ከዚያ በሇላ ደሞ እዚሁ ለመኖር ነው ያሠብነውና የአዲሥ አበባ ሠው ሆንሁ ማለት አይደል?..ለዛ ነው ጎንደር ነበርሁ ያልሁህ።" አልሁትና ቀለል ያለ የሀፍረት ሳቅ ሳኩኝ። 

"ኦ..ደስ ይላል! ደስተኛ ያድርጋችሁ" አለኝ...

"አሜን አሜን!..አንተስ ግን አንድ ቆንጅዬ አብራህ የለችም? አልሁት። እንደተለመደው ፈርጠም ብሎ...

"ኧረ አለች.." ሲለኝ "እንዴ ደስ ይላል.. ግን የት እዚሁ ነች? ደሞ በምን ሁኔታ ላይ ናችሁ?" አልሁት። ያው መጠየቄ እንዳይቀር ነው እንጂ ተማሪ ሆኖ ያገባል ብዬ እንኳን አልነበረም።

"..ያለች?" አለና አይኑን ውርውር አድርጎ በሀሣብ ምስጥ አለ። "አዎ የት ነው ያለችው?" አልሁት...

"ከእኔ ጋ ነች! ..ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ያው መሆን እንዳለብን..." ብሎ ቀና ብሎ አየኝ..

..እጅግ ሚስጥራዊነቱን እያየሁ ነው እና ከዚ በላይ መጠየቅ የበለጠ ግራ መጋባት እንደሆነ ሲገባኝ "መልካም..ፈጣሪ አይለያችሁ" አልሁትና ወሬ ለማሥቀየር "እና ይችን ሀገር እንዴት ታያታለህ?" አልሁት። በዚያው ወዳገናኘን ጉዳይ ብንሔድ ብዬ ነው። ፊቱ በቅፅበት ሀዘን ሲውጠው ይታይ ነበር። "..ስለ ሀገራችን አይቶ ለመናገር ሚቻልበት ሁኔታ አለ ብለህ ነው?" ..ሢለኝ "እሱስ አዎ ሁኔታችን ቲንሽ ይከብዳል.. ፈጣሪ ምህረቱን ቢልክልን እንጂ" አልሁና እስፕራይቴን ለመጠጣት ዝቅ ስል እሱ ከእስፕራይቱ ምንም እንዳልጠጣለት አየሁ። እስካሁን አለማሥተዋሌ ገርሞኝ "እንዴ ጠጣ እንጂ.. አልተመቸህም? አትወድም ነበር እንዴ? ስለው.."አረ በፍፁም!..እወዳለሁ" ብሎ አንስቶ በጥቂቱ ጠጣለትና "ፈጣሪማ...." አለ።

"..እ?" ..ሊናገር የፈለገው ነገር እንዳለ ያወኩ መሠለኝ።

"ፈጣሪማ...ይሄው ስንት ሺህ ዘመን በምህረት ኖሯል የሚቆጥርለት ጠፋጂ" ብሎ ትክዝ አለ። ሙዱን ያበላሸሁት መሠለኝና በራሴ አዘንሁ

 "እሱስ ልክ ነህ.." አልሁት።

..ከተቀመጥን ጀምሮ ንግግራችን በዝምታዎች ጣልቃ ገብነት የተሞላ ስለነበር ጊዜው እንደሄደ ተሠማኝና "ጊዜህን አላባክንብህ ህሩይ ወንድሜ ምናልባት ነፃ ከሆንህ ነገ 8 ሠዓት አካባቢ እዚሁ እንገናኝ" አልሁትና እንገናኝ ማለቴ ሌላ ነገር ያለው እንዳይመሥል ብዬ "..ያው እንዲሁ እንጨዋወታለን ብዬ ነው:: እውነት ለመናገር ህሩይ ከአዳራሽ ስንወጣ መጥቼ ስጠራህ ምንም አላማ ኖሮኝ አይደለም ግን ውስጥ የተናገርኸው ንግግር ልቤን ስለነካኝ በቃ በምንም ጉዳይ ካንተጋ ባወራ ልክ ምሆን ስለመሠለኝ ነው ፤ ለዛም ነው ዛሬ ከመተዋወቃችን ስላለሁበት ሁኔታም ሣትጠይቀኝ የነገርሁህ።" አልሁት። እሱም በእውነትም ጡሩ ልጅ ነው ከዚ በላይ ደሞ የሠውን ስሜት ከሁኔታወች መረዳት የሚችል ይመሥላልና "ምንም ችግር የለም ዮናታን ሚሥጥርም ከነገርኸኝ ልታምነኝ ትችላለህ.. ግን ነገ ይመቸኝ ብለህ ነው?!" ሲለኝ "አይ! ሌላ ቀን መሆን ይችላል" አልሁት ፍጥን ብዬ።

"ኧረ..ችግር የለም በቃ" አለኝ:: ከሆነ እሽ በቃ ለዛሬ ጥናትም ይኖርብሀል አላሥቆይህ ብዬ ዘወር ስል ሰላም ለሌሎች ተማሪዎች ትዕዛዝ አድርሳ እየተመለሠች ነው። አንድ ሁለቴ አጨብጭቤ "ሰላም.." ስላት ዘወር አለች። እጄን አንስቼ እንድትመጣ ምልክት ሠጠሇትና ሂሣብ ለመክፈል በኪሴ ስገባ ህሩይም ድፍን 50 ብር አውጥቶ ጠረጵዛው ላይ ጣል አደረገው። 

"እንዴ... ኧረ እኔ ከፍላለሁ! ጊዜህን ያጠፋሁት ሳያንስ ገንዘብማ አላሥወጣህም" ብዬ እኔም 50 ብር አውጥቼ ሳለ ሠላም ደረሰችና ጠርሙሶችንና የህሩይን ብር ከጠረጴዛው ልታነሳው ስትል...

"..ኧረ ረ ..ተይ እንቺ ብሩን እና መልሴን ስጪኝ" ስላት "..ነው እንዴ? እሽ" ብላ ማንሳቱን ተወችውና የኔን ብር ተቀብላ በወገቧ ላይ ባሠረችው ሽርጧ ኪስ ከተተችውና በምትኩ ለመልስ ሚሆን ገንዘብ ከኪሷ አወጣች..ጥቂት አስር ብሮችና ሳንቲሞች ጨምራ ሰጠችኝ፤ ጥቅልል አድርጌ በኪሴ ከተትሁት። ይሄ ሁሉ ሲሆን ህሩይ ምንም አላለም..የኔን ውሰጅ ብሎም አልተከራከረም እንዲሁ ፈገግ ብሎ ሲመለከተን ነበር።

እንደተነጋገርን አንድ ላይ ብድግ አልን፤ ሰላምንም "እየሄድን ነው ደና አምሺ" አልሇትና መንቀሳቀስ ስንጀምር "እሽ ደና አምሹ" አለችን። ህሩይም ተቀብሎ "አሜን!" አላት።

ቲንሽ እንደተራመድን ወደዶርም የሚወስደውን መንገድ እየተቃረብን እንደሆነ ሳስተውል "ወዴት ነህ ወንድሜ?..እኔ ዶርም ልግባና ሻወር ልውሰድ መሠለኝ ቲንሽ ሞቆኛል" አልሁት። 

"እሽ ዮናታን ግባ በቃ እኔ ማገኘው ሰው አለ.." አለኝና ወደኔ ዘወር ብሎ ቀኙን በግራው ደግፎ ለሠላምታ እጁን ሲዘረጋልኝ ያችው በግራ እጁ ላይ ያሠራትን ጨርቅ አየሇት። ሠላም እያልሁት እያለ እንዴት ላውንጅ ተቀምጠን እንዳላየሇትና እንዳልጠየኩት ሀሣብ ያዘኝ..ያኔም ለመጠየቅ ጊዜ እንደሌለኝ ሳስብ ደግሞ የበለጠ ቆጨኝ ግን ምንም ማድረግ አልቻልሁም። "ለነገሩ ብጠይቀውም ግልፅ አድርጎ አይነግረኝም ነበር" ብዬ ራሴን ማፅናናት ተያያዝሁት።

.. ተሠነባብተን ተለያየንና ወደዶርም እየሄድሁኝ ሰዓቴን ሳየው 10 ሠዓት እየተጠጋ ነው። ዶርም ደርሼ ስገባ ማናቸውም የዶርም ልጆች ውስጥ የሉም። ጫጫታቸው ስለሚረብሸኝ ዶርሙን ባዶ ሳገኘው "ተመሥገን.." ብዬ ቲንሽ ለመተኛት አልጋዬ ላይ ወደኩኝ። ተነስቼ ሻወር ለመውሰድ አስቤ ነበር ግን ከቋይታ በሇላ እንደተለመደው ሲጯጯሁ ነቃሁኝና ቀና ብዬ ሳያቸው...

"ዮኒ.. ሞተሽ ነው እንዴ አልነቃ አልሽንኮ" ምናምን እያሉ ሲንጫጩ መልስም አልመለሥሁኝ አምፑል መብራቱን ብቻ ሳይ ስልኬን ፈላልጌ ሠዓት ሳይ 2:33 ይላል መሽቶ ማለት ነው። ድክም ብሎኝ ስለነበር ጫማዬን ብቻ አውልቄ እግሬን እንኳን ሳልታጠብ ልብስም ሳልቀይር ተመልሼ ተኛሁ።

..የነቃሁት ግን ገና 9:30 አካባቢ ነበር..ግን አልተነሳሁም እንዲሁ ሀሣብ ሣወጣ ሣወርድ ነው የነጋለኝ። ሌሊቱን ብቻ አይደለም ነግቶ ተነስቼም ሀሣቡ አላለቀልኝ፤ በእንቅልፍ ምክንያት የቀረውን ሻወር በጠዋት ወስጄ ፆምም ስለሆ ቁርስ አልገባሁምና ክላስ እስክገባ ድረስ እንዲሁ ሣሥብ ነበር። ..ስለ 8 ሰዓቱ የህሩይ ቀጠሮ ነበር ማሥበው። ዛሬ ብዙ ለማውራትና በተለይም በሀገራችን ሁኔታ ከኔ ብቻ ሣይሆን ከብዙዎቻችን በተለየ የሚያውቀው ወይም የሚያሥበው ነገር እንዳለ ስለተረዳሁት እንዴት ብዬ የውሰጡን እንደማሥወራው ነበር ሣወጣ ሣወርድ የነበረው። ክላስ 5:30 ጨርሰን ወጣንና 6 ሠዓት አካባቢ ከዶርም ጓደኛዬ ከዳኒ ጋር ካፌ ሔድሁኝ። እሱ እያወራ ማሠብ አልቻልሁም ግን ቀጠሮየን ሙሉ በሙሉ ሣረሳው ቀስ ብለን ምሳ በልተን ስንወጣ 7:20 ነው። ዳኒን እንደምንም ምክንያት ፈጣጥሬ ተለየሁትና ወደ ቀጠሮዬ ሄድሁኝ። እዛ ስደርስ ህሩይ ገና አልመጣም። በርግጥም አላሥችል ብሎኝ እንጂ 7:30 ያለው እንኳን እዛው ተቀምጬ ነበር። ከደቂቃዎች በሇላ ሠላም ከላውንጁ ስትወጣ አየችኝና ጮህ ብላ "ዮኒ.." ብላኝ መለስ ብላ ወደ ላውንጁ ገባች። "ይቺ ደሞ ምን ነክቷታል ጠርታኝ የምትገባው" እያልሁ ሳስብ ተመልሳ ወጣችና እየሮጠች ወደኔ መጣች.. ስትቀርብና ሳያት አንድ ስፕራይተና የታጠፈ ወረቀት ይዛለች።

"..ሠላም ነው?" አለችኝ አጠገቤ ስትደርስ። "አለሁ.. ቆይ እኔ መች አዘዝሁኝ? ደሞ ምን ወረቀት ነው የያዝሽው?" ስላት...

"..እ ..ህሩይኮ ጠዋት አካባቢ መጣና ስትመጣ ይሄን ወረቀትና ስፕራይት እንድሰጥህ ነግሮኝ የስፕራይቱን ከፍሎኝ ሄደ" አለችኝ።

..እንደማይመጣ አሰብሁና በጣም ደነገጥሁኝ ወረቀቱን ተቀብያት "የምርሽን ነው?..ቀጠሮኮ ነበረን፣ ቆይ ሌላ ምንም አላለሽም?" አልሇት..እውነት ለመናገር ለአንድ ቀን ተገናኝተን በማግስቱ የቀረብኝ ሳይሆን የልጅነት አብሮ አደጌ የጠፋብኝ ያክል ነው የተሰማኝ። 

"..እ..መገኘት ስላልቻልሁ ይቅርታ በይው ብሎኛል..በል በቃ ስራ አታሥፈታኝ" ብላኝ ስፕራይቱን ከፍታልኝ ሄደች። እኔ ግን መጠጡ ትዝም አላለኝም ሌት ከቀን የማወራውን ያሠብሁትና ለማግኘት የጓጓሁትን እያሠብሁና ቅር እያለኝ ወረቀቱን ተጣድፌ ዘረጋጋሁትና በፍጥነት ማንበብ ጀመርሁ። ..የባሰ ደነገጥሁኝ..ሀዘንም ጭንቀትም ድብልቅልቅ አለብኝ። አንድ ቀን በማውቀው ሰው እንደዚ ሊሠማኝ ይችላል ብዬ በፍፁም ያሠብሁበት ቀን አልነበረም ግን አንብቤ ስጨርስ እምባዬ በአይኔ ሞልቶ ነበር። ህሩይ የፃፈልኝ መልዕክት እንዲህ ነበር ሚለው.....


(ቀጣይ...click here)

Report Page