*/

*/

Source

ኑዛዜ በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት እንዴት ይታያል/ ************

የሰው ልጅ ከተወለደበት እለት አንስቶ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ድረስ በዚች ምድር ላይ የሚኖረው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ ዘላለማዊ አይደለም፡፡

የምድር ላይ ቆይታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሀብት የማፍራት እና ያፈራውን ሀብት የማስተላለፍ ሕጋዊ መብት አለው፡፡

ውርስ ማለት የአንድ በሞት የተለየን ሰው ንብረት እና ሀብት እንዲሁም ሊተላለፍ የሚችሉ መብት እና ግዴታዎች በሕይወት ላሉ አንድ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ወራሾቹ የሚተላለፍበት ሕግ ነው፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ ይህ የውርስ ሕግ በ1952 ዓ/ም በወጣው የፍታሐብሄር ሕጋችን በሁለተኛ መጽሐፍ በአንቀጽ አምስት ውስጥ ከአንቀጽ 826 እስከ 1125 ድረስ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

በአገራችን የውርስ ሕግ ውስጥ በኑዛዜ እና ያለኑዛዜ የሚባሉ የሁለት አይነት የውርስ ማስተላለፊያ መንገዶች ሲኖሩ በዛሬው ዝግጂታችን የኑዛዜ ውርስ ማለት ምን ማለት ነው ከኢትዮጵያ ሕግ አኳያ እንዴት ይታያል በሚለው ትኩረት አድርገናል ተከታተሉን፡፡

ኑዛዜ ማለት ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በፍላጎቱ መሠረት ለተተኪዎቹ የሚያስተላልፍበት ሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ ሟች በኑዛዜው ከሞተ በኋላ ስለ ንብረት ክፍፍል፣ የልጆቹ ሞግዚት ማን እንደሚሆን፣ ንብረቱን ማን እንደሚያስተዳድርና ስለ ቀብር ስነ-ስርዓቱ ሊገልፅ ይችላል፡፡

ኑዛዜ በወኪል ወይም በእንደራሴ የማይከናወን የተናዛዡ የግል ድርጊት ነው (ፍ/ብ/ሕ/ቁ/857)፡፡ ሟቹ ኑዛዜውን የተናዘዘው በሌላ ሰው አስገዳጅነት የሆነ እንደሆነ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡ስለዚህም ለመናዘዝ፣ ለማሻሻል ወይም ቀሪ ለማድረግ በውክልና ለሌላ አካል መስጠት ኑዛዜውን ዋጋቢስ ያደርገዋል፡፡

ኑዛዜ የሚደረገው በተናዛዡ ብቻ እንደሆነ ከላይ የተገለጸ ሲሆን ማንኛውም ሰው የሚያደርገው ኑዛዜ ሁሉ የሚፀና አይደለም፡፡ አንድ ኑዛዜ በሕግ በኩል ተቀባይነት የሚኖረው ተናዛዡ በሕግ የመናዘዝ ችሎታ ያለው ሰው ሲሆን ብቻ ነው፡፡

በሕጉ ችሎታ የላቸውም የተባሉት ሰዎች እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ፣ በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች እና የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡አንድ እድሜው አሥራ ስድስት ያልሞላ ልጅ ኑዛዜ ማድረግ እንደማይችል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 295 ላይ ተገልፆል፡፡

በፍርድ የተከለከለ ሰው ከተከለከለበት እለት ጀምሮ ኑዛዜ ማድግ አይችልም፡፡ ነገር ግን ከመከልከሉ በፊት ያደረገው ኑዛዜ ተቀባይነት አለው፡፡ ይህም ሆኖ ዳኞች እንደነገሩ ሁኔታ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል እንዲፈርስ የማድረግ ሥልጣን በፍ/ብ/ሐ/ቁ 368 ላይ ተሰጥቶቸዋል፡፡

የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው ያደረገው ኑዛዜም አይፀናም፡፡ ኑዛዜው የማይፀናው ግን ኑዛዜውን ባደረገበት ጊዜ የታወቀ ዕብድ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፍታሐብሄር ሕግ አንቀጽ 880 መሰረትም ሦስት አይነት የኑዛዜ ፎርሞች አሉ፡፡ እነዚህ

 በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ

 በተናዛዡ ጽሁፍ የሚደረግ ኑዛዜ

 በቃል የሚደረግ ኑዛዜ ሲሆኑ

በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ ተናዛዡ በእራሱ ወይም በተናዛዡ ተናጋሪነት በሌላ ሰው ሊጻፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከተፃፈ በኋላ በተናዛዡ በአራት ምስክሮች ፊት ካልተነበበና ይህም ስርዓት መፈፀሙንና የተፃፈበትን ቀን የሚያመለክት ካልሆነ በቀር በተጨማሪም ተናዛዡና ምስክሮቹ በኑዛዜው ላይ ወዲያውኑ ፊርማቸውን ወይም ያውራጣት ምልክታቸውን ካላደረጉ በቀር ፊራሽ ነው፡፡

ኑዛዜው የተፃፈበትን ቀን ማመልከትና አራት ምስክሮች መገኘት አለባቸው፣ ጽሑፍ የሚደረግ ኑዛዜ ሙሉ በሙሉ በተናዛዡ መፃፍና ፅሑፉ ኑዛዜ መሆኑ በግልጽ “ኑዛዜ ነው” ተብሎ መፃፍ አለበት፡፡ ተናዛዡ ኑዛዜው የራሱ መሆኑን በእጅ ጽሑፍ በእያንዳንዱ ገፅ ላይ መግለፅ አለት፡፡

በኑዛዜው ቃል ላይ የሚገኘውንና መጀመሪያ የተፃፈውን ቃል የሚለውጥ ስርዝ፣ መፋቅና ድልዝ ኑዛዜውን ፈራሽ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም የተናዛዡን ፈቃድ መለወይ ስለሚሆን ነው (ፍ/ብ/ሕ/ቁ 889)፡፡ በሌላ በኩል ስርዝ ወይም ድልዝ በመኖሩና በመፋቁ ምክንያት የኑዛዜ ቃል ፈራሽ የማይሆንበት ጊዜ አለ፡፡

ይህም እንደ ኑዛዜው ፎርም አይነት ኑዛዜው በግልጽ የተደረገ ኑዛዜ ከሆነ ምስክሮቹ ስርዝ ድልዙን በፊርማ ያፀደቁት፤ ኑዛዜው በተናዛዡ ጽሑፍ የተደረገ ከሆነ ግለሰብ በራሱ ማስታወሻ ላይ ከገለፀ የኑዛዜው ቃል ፈራሽ አይሆንም፡፡ (ፍ/ብ/ሕ/ቁ 889)፡፡
የቃል ኑዛዜ ማለት አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተስምቶት የመጨረሻ ፈቃድ ቃሎቹን በሁለት ምስክሮች ፊት የሚሰጥበት የኑዛዜ አይነት ነው፡፡

የዚህ አይነቱን ኑዛዜ ለመስማት የሚጠሩት ምስክሮች ለአካለ መጠን የደረሱና በፍርድ ወይም በህግ ያልተከለከሉ መሆን አለባቸው፡፡ ስለሆነም የዚህ አይነት ኑዛዜ በሁለት ምስክሮች ፊት መስጠት አለበት፣ ተናዛዡ በዚህ የቃል ኑዛዜ ላይ እንዲናዘዝ የሚጠበቀው ስለቀብሩ ስነ-ሰርዓት ያሉትን ትዕዛዞች ከአምስት መቶ ብር በላይ ያልሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን ለተለያዩ ሰዎች መናዘዝ እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ካሉት እነሱን በሞግዚትነት የሚያስተዳድራቸውን ሰው በተመለከተ ውሣኔዎችን መስጠትና ተፈጻሚነቱ ተናዛዡ በህይወት ባለበት ሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንዱ ወይም ከአንድ በላይ ነጥቦች ከተጓደሉ ኑዛዜው ፈራሽ ይሆናል፡፡


በአጠቃላይ ኑዛዜ ማለት ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በፍላጐቱ መሠረት ለተተኪዎቹ የሚያስተላልፍበት ሕጋዊ መንገድ ሲሆን ኑዛዜ የሚደረገው ኑዛዜውን ለማድረግ በሕግ ችሎታ ባለው ሰው ብቻ በግሉ (በራሱ) የሚያደርገው ሕጋዊ ድርጊት ነው፡፡

ኑዛዜው የሚፀና እንዲሆን ኑዛዜውን በተመለተ መሙላት ያለባቸው ሁኔታዎች ኑዛዜው መፈፀም የሚችልመሆኑ፣የኑዛዜው ቃል በሕገ ወጥ ያልሆነ፣በሃይል እና በጫና ምክንያት የተደረገ መሆን የለበትም፡፡አንድ የኑዛዜ ቃል በማያሻማ መልኩ ተጠቃሚውን ወይም ጉዳዩን ካላመላከተ ፈራሽ ነው፡፡

ውድ አንባብያን ሚገባንን በመጠየቅ የማይገባንን በመተው መብትን እና ግዴታችን በማወቅና በማክበር ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ኃላፊነታችን እንወጣ በማለት መልዕክታችን እያስተላለፍን በቀጣይ ዝግጂት ያለኑዛዜ ስለሚደረግ ውርስ ይዘን እቀርባለን!! ሰላም
By FDRE Attorney General

Report Page