*/

*/

Source
USTAZ ABU HYDER Offical Page
ፆም ግዳጅነቱ በማን ላይ ነው? አቡ ሀይደር በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡ የፆም መስፈርቶች ዛሬ ደግሞ የምንመለከተው የፆምን መስፈርት (ቅድመ ዝግጅት) ነው፡፡ አንድ ሰው የረመዷን ፆም ግዴታ የሚሆንበት ምን ምን መስፈርቶችን (ሹሩጦችን) ሲያሟላ ነው? ግዴታው የሚነሳለትስ መቼ ነው? የሚለውን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡ ከመስፈርቱ በፊት፡- ፆም በኢስላም ውስጥ ዋጂብ (ግዳጅ) የሆነ የአምልኮ ተግባር ነው፡፡ ከአምስቱ የኢስላም ማእዘናትም አንድ ማእዘን ነው፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡- "يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ " سورة البقرة 183 "እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነገገ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡" (ሱረቱል በቀራህ 183)፡፡ ዑመር ኢብኑል-ኸጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ፡- "ኢስላም በአምስት ነገራት ላይ ተመስርቷል፡፡ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩንና፡ ነቢዩ ሙሐመድም የሱ መልክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንቡንና ስርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካትና(ምጽዋት) መስጠት፣ የረመዷንን ወር መፆም እና የአላህን ቤት መጎብኘት (ሐጅ ማድረግ) ናቸው" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡ ከላይ ያለው ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጽ ሁለት ነገር ያስረዳናል፡- አንደኛ፡- ጾም በኛ ላይ የተደነገገ ሃይማኖታዊ ግዳጅ መሆኑን፡፡ ሁለተኛ፡- የጾም ስርዓት በዚህ ኡምማ የተጀመረ አዲስ አምልኮ ሳይሆን፡ ከዚህ በፊት በነበሩት የነቢያት ተከታዮችም ላይ የተደነገገ ስረ-መሰረት ያለው የአምልኮ ክፍል መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን አፈጻጸሙ ላይ እንደዘመኑ ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ኡምማ ላይ ጾም ግዳጅነቱ የተደነገገው፡- በሂጅራ አቆጣጠር በ2ኛው ዓመት፡ በስምንተኛው ወር ሻዕባን፡ በሁለተኛው ቀን ሰኞ እለት ነው (مصدر:- المختصر في شرح أركان الإسلام: بعض طلبة العلم)፡፡ እንግዲያውስ ግዳጅነቱ በነማን ላይ ነው? የሚባል ከሆነ፡ መልሱም፡- ቀጥሎ ያለውን መስፈርት ባሟሉት ላይ የሚል ይሆናል፡፡ መስፈርቶቹም፡- 1. ሙስሊም በሆነ ላይ፡- የመጀመሪያውና ዋነኛው መስፈርት ነው፡፡ ካፊር አብሮን ቢጾም ከጾሙ የሚያገኘው ትርፍ ረሀብ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራ አላህ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የግድ ሶስት መስፈርቶች መሟላት አለባቸው፡፡ ከዛ ውስጥ አንዱ ‹‹ሙስሊም›› መሆን ነው፡፡ የካፊር ሥራ ከንቱ እንደሆነና ተቀባይነት እንደሌለው ቀጣዮቹ የቁርኣን ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡- "ከእናንተ ውስጥም ከሃይማኖቱ የሚመለስና እርሱም ከሐዲ ሆኖ የሚሞት ሰው እነዚያ (በጎ) ሥራቸው በቅርቢቱም በመጨረሻይቱም አገር ተበላሸች፡፡ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡ እነርሱ በርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡" (ሱረቱል በቀራህ 2፡217)፡፡ "ወዳችሁም ሆነ ጠልታችሁ ለግሱ ከናንተ ተቀባይ የላችሁም እናንተ አመጠኞች ሕዝቦች ናችሁና በላቸዉ። ልግስናዎቻቸውን ከነሱ ተቀባይ የሚያገኙ ከመሆን እነሱ በአላህና በመልክተኛዉ የካዱ ሶላትንም እነሱ ታካቾች ሆነው በስተቀር የማይሰግዱ እነሱም ጠይዎች ሆነው በስተቀር የማይሰጡ መሆናቸዉ እንጂ ሌላ አልከለከላቸውም።" (ሱረቱ-ተውባህ 9፡53-54)፡፡ "እነዚያም የካዱት ለነሱ ጥፋት ተገባቸው፤ ሥራዎቻቸውንም አጠፋባቸው።ይህ እነሱ አላህ ያወረደውን ስለጠሉ ነው፤ ስለዚህ ሥራዎቻቸውን አበላሸባቸው።" (ሱረቱ ሙሐመድ 47፡8-9)፡፡ ዓኢሻ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- "አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ኢብኑ ጁድዓን በዘመነ ጃሂሊያ ዝምድና የሚቀጥልና ምስኪን የሚመግብ ነበር፡፡ እናም ይህ ይጠቅመዋልን? እሳቸውም፡- ምንም አይጠቅመውም፡፡እሱ አንድም ቀን ቢሆን፡- ጌታዬ ኃጢአቴን በፍርዱ ቀን ማረኝ ብሎ አያውቅምና" ብለው መለሱላት፡፡ (ሙስሊም የዘገበው)፡፡ እንግዲያውስ ሙስሊም ያልሆነ ሰው (ካፊር) በመልካም ሥራው ምን ይጠቀማል? ከተባለ ደግሞ ምላሽ የሚሆነው ተከታዩ የነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሐዲሥ ነው፡- አነስ ኢብኑ ማሊክ(ረዲየላሁ ዐንሁ) ከአላህ መልክተኛ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የሰማውን እንደነገረን እንዲህ ብለዋል፡- "ካፊር መልካም ሥራ ከሰራ ከዱንያ ሲሳይ (በምትኩ) ይሰጠዋል፡፡ ሙስሊም ከሆነ ግን አላህ ይህን መልካም ሥራውን በአኼራ ያነባብርለታል፡፡ በዱንያም በታዛዥነቱ ልክ ሲሳይን ይተካለታል" (ሙስሊም)፡፡ በዚህ መሰረት ካፊር በሸሀደተይን ወደ ኢስላም ካልገባ በስተቀር መልካም ሥራው ለሱ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ 2. አእምሮው ያልተዛባ መሆኑ፡- ግለሰቡ ሙስሊም ሁኖ የአእምሮ ችግር ካለበት (በትክክል ማሰብ ካልቻለ) የፆም ግዳጅነት ይነሳለታል፡፡ አእምሮው በተመለሰለት ወቅትም ቀዷውን እንዲያወጣ አይጠየቅም፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ በንዴት ወይም በሃሳብ ብዛት ወሰድ አርጎ የሚመልሳቸውን ሰዎች ሑክሙ አይመለከታቸውም፡፡ እነሱ በታመሙበት ወቅት ግዳጅነቱ ቢነሳላቸውም፡ በዳኑበት ጊዜ ፆሙን መቀጠል፡ ያመለጣቸውንም ቀዷ ማውጣት አለባቸው፡፡ ዙሁር ሶላት ላይ ወሰድ አርጎት አፍጥር አካባቢ መለስ እንደሚያረገው ሰው አይነት ማለት ነው፡፡ በትክክል ከሚናገረው ይልቅ የሚቀባዥረው የበዛ፡ ህመሙ ደግሞ የሚዘወትር አይነት ከሆነ ግን ግዳጅነቱ ተነስቶለታል፡፡ ምናልባትም ወደፊት በአላህ ቸርነት በወንድሞች እርዳታ ቁርኣን ተቀርቶበት ቢድን እንኳ ላለፈው ነገር ቀዷ አውጣ አይባልም፡፡ ለዚህም ቀጣዩ ሐዲሥ መረጃ ይሆናል፡- ከዓኢሻህ እና ከዐሊይ ኢብኑ አቢ-ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አሉ፡- "ቀለም (ኸይርና ሸር የሚመዘገብበት) ከሶስት ሰዎች ላይ ተነስቷል፡፡ የተኛ ሰው እስቂነቃ ድረስ (በተኛበት ቢለፈልፍ)፣ ህጻን ልጅ ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ፣ አእምሮው የተደበቀ (እብድ) እስኪድን ድረስ" (አቡ ዳዉድ 4400፣ ኢብኑ ማጀህ 2041፣ ቲርሚዚይ 1423፣ ነሳኢይ 3445፣ አሕመድ 952)፡፡ 3. ለአካለ መጠን መድረስ፡- በሶስተኛ ደረጃ መሟላት የሚገባው ደግሞ የዕድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው (ዕድሜው 15 የሞላ፣ ወይም ከዛ በፊት ሐይድ ካየች/ኢሕቲላም ከሆኑ፣ ወይም በብልት ዙሪያ ጸጉር መብቀል ከጀመረ) ፆም መጾም ግዳጅ ይሆንባቸዋል ማለት ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ምልክቶች (ዕድሜ፣ የዘር ፈሳሽ እና ጸጉር) አንዱም ካልታየ በነሱ ላይ ፆም ግዳጅ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እነሱን በፆም ማዘዝና ማለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የሐዲሥ ማስረጃ ለዚህም ማገልገል ይችላል፡፡ 4. ጤናማ መሆን፡- ህመምተኛ የሆነ ሰው የረመዷንን ፆም መፆሙ ህመሙን የሚያገረሽበት ከሆነ፡ እሱንም ከጎዳው መፆሙ አይፈቀድለትም፡፡ ለሱ መብላት ነው የተፈቀደለት፡፡ ህመሙ የሚሽር ሁኖ ወደፊት ከዳነ የበላበትን ቀን ቆጥሮ ቀዷውን በመፆም ያወጣል ማለት ነው፡፡ ህመሙ ለመጾም የሚከለክለው ካልሆነ ግን ግዴታ መፆም አለበት፡፡ ጉንፋን ያዘኝ፣ ራሴን አመመኝ ብሎ ማፍጠር የለምና! ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡- "…ከእናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፡፡ በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት፡፡ አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል፡፡ በእናንተም ችግሩን አይሻም…" (ሱረቱል በቀራህ 2፡185)፡፡ 5. የአካባቢው ነዋሪ መሆን፡- በመኖሪያ አድራሻው ያለ ሰው መሆን አለበት፡፡ ከመኖሪያ ክልል ወጥቶ በጉዞ ላይ ሁኖ ሙሳፊር ሊሰኝ የሚችልበት (ከ 80 ኪሎ ሜትር በላይ ወደሆነ) ሌላ ከተማ ከገባ ፆም ለሱ ዋጂብ አይደለም፡፡ ከፈለገ መፆም ካልፈለገ ማፍጠር ይችላል፡፡ ለሱ መፆሙ ግን የበለጠ ተወዳጅ ነው፡፡ ከሰፈር ተመልሶ ወደ መኖሪያ ክልሉ ሲገባ ደግሞ ወደ ፆሙ ይመለሳል፡፡ በሰፈር እያለ ያልፆመባቸው ቀናት ካሉ ደግሞ በሌላ ጊዜ ቀዷውን ያወጣዋል፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን ከላይ የተጠቀሰው የቁርኣን አንቀጽ ነው፡፡ በተጨማሪም ተከታዩ ሐዲሥ ነው፡- አቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- "በረመዷን ከአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጋር ለዘመቻ እንወጣ ነበር፡፡ ከመሀከላችን የሚጾም አለ፡፡ የማይጾምም አለ፡፡ ጾመኛው የማይጾመውን (ባለመጾሙ) የማይጾመው ደግሞ ጾመኛውን (በሰፈር ላይ በመጾሙ) አይቃወመውም ነበር፡፡ ይልቁኑ ኃይልና ጉልበት አግኝቶ የጾመ ሰው መጾሙ ለሱ መልካም እንደሆነ፡ አቅምና ጉልበት አንሶት ያፈጠረ ሰው ደግሞ ለሱ ማፍጠሩ መልካም መሆኑን ይመለከቱ ነበር" (ሙስሊም 2674)፡፡ እነዚህ አምስቱ ወንድና ሴት በጋራ የሚመለከታቸው መስፈርት ሲሆን፡ ሴቷ ደግሞ በተጨማሪ፡- 6. ከሐይድና ከወሊድ ደም የጠራች መሆኗ፡- በወር አበባ ወቅትና በወሊድ ደም ጊዜ መጾም አይፈቀድም ሐራም ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃው፡- አቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "ሴት ልጅ ሐይድ ካየች አትሰግድም አትጾምም!..." (ቡኻሪይ 1951)፡፡ እነዚህ 5/6 መስፈርቶች የተሟሉለት ሰው የረመዷን ጾም ግዳጅ የሚሆንበት ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ በታች የሚጠቀሱት ደግሞ ጾም የማይወጅብባቸው ናቸው፡- 1. ሙስሊም ያልሆነ ካፊር 2. ለአካለ መጠን ያልደረሰ ህጻን 3. አእምሮው ያልተስተካከለ ህመምተኛ 4. ጾሙ የሚከብደው በሽተኛ 5. ከመኖሪያ አካባቢው የወጣ ሙሳፊር 6. እርጉዝና አጥቢ ሴት፡- ከጾምኩኝ ጽንሱ በምግብ እጦት ይጎዳል፡ ወይም እኔ አቅም ያንሰኛል ብላ ከፈራች መብላት አለባት፡፡ አጥቢዋም እንደዛው ለልጇ ወይም ለራሷ ከፈራች መብላት ትችላለች፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ በጾም ቀዷውን ትከፍላለች፡፡ 7. በእድሜ የገፉ አዛውንቶች፡- የረመዷንን ጾም ለመጾም አቅሙ ከሌላቸው መብላት ይፈቀድላቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ በሚበሉበት የጾም ቀን አንድ ምስኪን ማብላት (ማስፈጠር) አለባቸው፡፡ እሱ ማካካሻ ይሆናቸዋል፡፡ 8. ተስፋ የሌለው ህመምተኛ፡- መዳኑ ተስፋ የማይደረግበት ህመምተኛ እሱም በረመዷን መብላት ይችላል፡፡ ቀዷ የለበትም ፡፡ በምትኩ በእያንዳንዱ የጾም ቀን ምስኪን ያበላል (ያስፈጥራል) ወላሁ አዕለም፡፡

Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder

May 25, 2017 · Public · in Timeline PhotosView Full Size

ጀዛከለሀ ኸይር

Apr 15 at 7:53 AM

አሰላም አለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱሁ ኡስታዜ አላህ ይጠብቅህ ጀዛክ አላህ ኸይር ጀዛ

May 25, 2017

ጀዛከላህ ከይር ኡስታዝ

May 25, 2017

As wr wb Jezakalhu hiyire uzetazachen

May 25, 2017

Jezakumellah heyren Ustaz

May 26, 2017

ጀዛከላህ ኸይር ኡስታዝ

May 26, 2017

 View more comments…

Report Page