*/

*/

Source

በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዮ ዞን ወረዳዎች ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ
***********************************
በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዮ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልልና ከፌዴራል ፀጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ኢፊዲሪ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቀ፡፡

ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ፀጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ ይሰራል ተብሏል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት በአጣዮ ከተማና አካባቢው በታጠቁ ሀይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰማውን አዘን ገልጾ ለተጎጂ ወገኖች መጽናናትን መመኘቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

በዚህም መሰረት የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል፡፡

1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪ/ሜ ውስጥ የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የእምነት ተቋማት እና የመንግስት ተቋማትን የግለሰብ መኖርያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጥልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለህብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት የመንግስት መዋቅር እና በድኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን መታወቅ አለበት፡፡

በመጨረሻም መላው ህብረተሰብ እንደወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ ለሀገሪቱ ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት መከላከያ ሚኒስቴር ጥሪውን አቅርቧል ፡፡

Report Page