*/

*/

Source

"ጥቁሩ ኮዳይ”

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ (May 5, 1938 - May 5,1998)

------------------------

ከሠርፀ ፍሬስብሐት
(ኅዳር ፰ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.)

በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መታሰቢያ 'የሳይንስ አካዳሚ' መድረክ ላይ የቀረበ፤
=================

ማናችንም እዚህ መድረክ ላይ የተገኘን ታዳምያን ኹሉ እንደምናውቀው፤ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ትልቅ የሙዚቃ ሰው፣ የሙዚቃ ተመራማሪ፣ እና የኢትዮጵያን ሙዚቃ “ረቂቅ” በሚባል ደረጃ ቀምረው ያሳዩ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡

ነገር ግን፥ እኚህን የመሰሉ የሙዚቃ ሊቅ፣ በሀገራችን ሙዚቃ ውስጥ በምናደንቃቸው፣ በምንወዳቸው፣ ሥራዎቻቸውንም ዘወትር በምናዳምጥላቸው "የፖፒውላር" ሙዚቃ አቀናባሪዎች ወይም ድምፃውያን ልክ፤ ማንነታቸውን እና የሞሉትን ሙዚቃዊ ክፍት ቦታ መረዳት የቻልን አይመስለኝም።

በዚህም የተነሳ፥ -አርአያነታቸውን የሚከተል ለመፍጠር፣ - ባለውለታነታቸውን ለመዘከር፣

- በስማቸው የደከሙለትን የረቂቅ ሙዚቃ እና የምርምር ውጥን ሊተገብር የሚችል የምርምር ወይም የማስተማሪያ ተቋም ለመመሥረት እንዳንችል ኾነናል(ዳርጎናል)፤ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፤ የእኚህን ታላቅ ሊቅ እና የሙዚቃ ጥበበኛ ታሪክ እና ሥራዎች እንድንዘክር የዛሬውን መድረክ ማመቻቸቱ፤ የማስታወስ፣ የመቀስቀስ፣ የምርምር መነሳሳትን እንደሚፈጥር አንድ ተግባር ልንቆጥረው እንችላለንና አካዳሚው ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ እኔንም፥ ለመድረኩ መነሻ የሚኾን ሐሳብ እንዳቀርብ ስለተፈቀደልኝ በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡

---------------------


መነሻዎቼ:-

የመጀመሪያው፥ የእኔው የራሴ ለፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የነበረኝ የግል አድናቆት ሲኾን፡ በዚህ አድናቆት ሰበብ ስለ እርሳቸው የተጻፉ፣ በብዙኃን መገናኛ የቀረቡ፣ ከሚያውቋቸው ወዳጆቻቸው አካባቢ የተገኙ መረጃዎች መነሻ ኾነውኛል፡፡

ከእነዚህ የመረጃ ምንጮች በተለይ፥ ጠለቅ አድርገው የሊቁን ታሪክ የዘገቡ ጥናቶች ያቀረቡልን፥ - ፕ/ር ሲንቲያቴ ኪምበርሊንን፣ - ፕ/ር ኬይ ኮፍማን ሸለሚን፣ - ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን፣

- ስሜነህ በትረ ዮሐንስን ዋና ምርኩዝ አድርጌያቸዋለሁና- እጅግ አድርጌ በእናንተ ፊት ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ፤ በየትኛውም መድረክ ፕ/ር አሸናፊ ከበደን ሳያመሰግን፣ አርአያ እንደኾኑት ሳይገልጽ፣ መንገዳቸውን እንደሚከተል ሳይናገር ያለፈበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡

ይህንን ኹሉ አድርጎም አልረካም፡፡ “ባለዋሽንቱ እረኛ” የተሰኘውን የአሸናፊ ከበደን የመጀመሪያ ቅማሬ፣ ለፒያኖ ዳግም ጽፎት (Rearrange) ለእርሳቸው በመታሰቢያነት በመጀመሪያ ኮምፓክት ሲዲው አስቀርፆት ነበር፡፡

በዚህም አልበቃውም፤ ወደ ተማረበት የቡልጋርያ ሶፊያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በሔደበት ጊዜ ባገኘው የሪኮርዲንግ ዕድል እንደገና የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደን ሥራ በሶፊያ ፊልሐርሞኒክ ኦርኬስትራ በልዩ ኹኔታ አስቀርፆ እንደገና መታወሻቸውን ሠርቶላቸዋል፡፡

እኔም በተለይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስጄ ስለ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ሥራዎች ካነጋገርኳቸው ሙዚቀኞች መካከል አንዱ ነውና እርሱን ማመስገን እጅግ የተገባ ነው፡፡

የፕ/ር አሸናፊ ከበደን ታሪክ እና ሥራዎች ማቅረብ (እውነት ለመናገር) ከበድ የሚል የቤት ሥራ ነበር የኾነብኝ፡፡ ሙዚቀኛ ብቻ ቢኾኑ ደግ ነበር፣ የምርምር ሥራዎችም ስላሏቸው የጥናቶቻቸውን ትኩረት እና ዐቅድ ማወቅ የግድ ይለኝ ነበር፡፡ በአዝማሚያ እና በኑሮ ፍልስፍናቸው የሚያደንቁትን ነገር ዐውቆ የድርሰቶቻቸውን ፈለግ ማሳየትም ሌላው ትንሽ ከበድ የሚለው ሥራ ነበር፡፡

*አሸናፊ ከበደ በኢትዮጵያ የሙዚቃ የስኮላርሺፕ ታሪክ ውስጥ፣

----------------------

ስሜነህ በትረ ዮሐንስ፥ SCHOLARSHIP ON ETHIOPIAN MUSIC: PAST, PRESENT AND FUTURE PROSPECTS (African Study Monographs, Suppl.41:19-34, March 2010, በሚለው ጥናታዊ ጽሑፉ እንዳሳየን፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃን የተመለከቱ ምርምራዊ ወይም ዘጋቢ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎችን ብናይ፥ በጣም የተዘነጋ እና ብዙም ተሳትፎ ያልታየበት ርዕሰ ጉዳይ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ዲሲፕሊናዊ አጠናን እያደገ የመጣ ለውጥም እናያለን፡፡
- በሻህ ተክለማርያም፣ ኢዩኤል ዮሐንስ፣ አሸናፊ ከበደ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ተስፋዬ ለማ፣ ጸጋዬ ደባልቄ በዚህ ምድብ ውስጥ በምሁራዊ ሚናቸው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

- ከአብዮቱ በኋላ የመጡት ልኂቃን ደግሞ፡- ዘነበ በቀለ፣ ውቤ ካሳዬ፣ ትምክህት ተፈራ፣ ዕዝራ አባተ፤ ተጠቃሽ የሙዚቃ ተመራማሪዎች ናቸው፡፡

አሁን ዕያየነው ላለው የዘመናችን "የሙዚቃ ስኮላርሺፕ" አብነት አድርገን የምንጠቅሳቸውን፥ እነ ዘነበ በቀለን፣ ዶ/ር ውቤ ካሳዬን፣ ዶ/ር ትምክህት ተፈራን እና ዶ/ር ዕዝራ አባተን እንዲሁም አስከ እነ ስሜነህ በትረዮሐንስ ድረስ የሚታየው ምሁራዊ ጎዳና መሠረቱ የተጣለው ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ላይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኹነኛው ተመስጋኝ ፕ/ር አሸናፊ ከበደ ናቸው፡፡ በኋላ በታሪካቸው ገባ ብለን እንደምናየው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም ትልቁን ሚና የተጫወቱ ከመኾናቸው አንጻር፡፡

*የፕ/ር አሸናፊ ከበደ የሕይወት ታሪክ፣ (May 5, 1938- May 5,1998)

--------------------------------

አሸናፊ ከበደ፤ የትምህርትን ጥቅም ከሚረዳ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በነበሩ ኹነቶች ውስጥ ከተሳተፈ፣ ለነገሥታት እና ለቤተመንግሥት ቅርብ ከኾነ የዘር ሀረግ ከሚመዘዝ ቤተሰብ የተወለዱ ሰው ናቸው፡፡

የአሸናፊ አያት፤ ሊቀ መኳስ አድነው ጎሹ የዐድዋ ዘማች የነበሩ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የጣሊያን ወታደሮች የማረኩ፣ በእቴጌ ጣይቱ ብጡል በኩል ከተሰለፈው ጦር ጋር የተዋጉ ጀግና ነበሩ፡፡
የእኚህ የዐድዋ ጀግና አባት (የአሸናፊ ከበደ ቅድመ አያት) ደጃዝማች ጎሹም በዐፄ ቴዎድሮስ ጦር እና በቤተመንግሥት ባለሟልነታቸው ታዋቂ እንደነበሩ ፕሮፌሰር አሸናፊ ለፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ነግረዋቸው፣ እርሳቸው ደግሞ በተባ ብዕራቸው "Ethiopian Review" ላይ ውብ አድርገው ጽፈውታል፡፡

በእናታቸው በኩል የነበሩት፤ አያታቸው አቶ ነከሬ ጉተማ ደግሞ፤ ዘመናዊ ትምህርት በወጉ የተማሩ፣ ከውጪ መንግሥታት ጋር ለሚደረጉ ስምምነቶች የቤተ መንግሥት አስተርጓሚ የነበሩ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ታላላቅ ስም ካላቸው ቤተሰቦቻቸው ኹሉ፤ የፕሮፌሰር አሸናፊን ማንነት የቀረፁ፣ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳደረጉባቸው ደጋግመው የሚናገሩላቸው፤ እናታቸውን ወ/ሮ ፈንታዬ ነከሬን ነው፡፡ የመንፈሳዊ ግጥም ችሎታቸው፣ የመንፈሳዊ ዝማሬ ችሎታቸው እና የድምፃቸው ውበት ከበገና ደርዳሪነታቸው ጋር ተደምሮ የአሸናፊን የሙዚቃ ስሜት ስለመፍጠሩ ራሳቸው አሸናፊ ይናገራሉ፡፡

እኚህን የመሰሉ እናት ከልጃቸው ከአሸናፊ ጋር በሕይወት የቆዩት ለዘጠኝ ዓመታት ብቻ ቢኾንም፤ "አንድ ሰው ምሉዕ ማንነቱ የሚሠራበትን ዋናውን ዕድሜ" አብረዋቸው ስለነበሩ፤ ትልቅ መሠረት እንደጣሉላቸው፣ ዕድሜ ልክ ከማይወጣላቸው ኀዘን ጋር በማስታዎሻዎቻቸው ላይ አስፍረውታል፡፡
አሸናፊ ከበደ በ1938 እ.አ.አ. ነበር የተወለዱት (1930 ዓ.ም.) መኾኑ ነው፡፡

*ትምህርት
-------------

አሸናፊ ከበደ የጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ኮከበ ጽባህ) አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱም ከአንጋፋው የሥነ ጽሑፍ ሰው አስፋው ዳምጤ እና ከዘመነኞቻቸው ጋር ተምረዋል፡፡ ኹሉም ስለ ፕ/ር አሸናፊ በሚሰጡት ምስክርነት፥ አሸናፊ ከበደ፤ ድንቅ ተማሪ፣ ፎቶ ግራፈር፣ ሥነ ጥበብ አፍቃሪ እና የሙዚቃ ስሜታቸው ከፍ ያለ ታዳጊ እንደነበሩ ይመሰክሩላቸዋል፡፡

፩- ሀረር መምህራን ኮሌጅ፤

አሸናፊ፤ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሀረር መምህራን ማሰልጠኛ ተከታትለዋል፡፡ በትምህርት ሥልጠና ዕድላቸው ጊዜ ያጠኑት ሙዚቃን ነበር፡፡ (ይህም፥ በጊዜው ለሙዚቃ ይሰጥ የነበረውን ትኩረት ራቅ ካለው ጊዜ ወዲህ አምጥቶ በንጽጽር ለማየት የሚረዳ ይመስላል፤)
ከመምህራን ትምህርት ማሰልጠኛው ከወጡ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡

፪- Eastman School of Music-
B.A,in Music, 1962

የአሸናፊ ከበደ ሙዚቃን በከፍተኛ ደረጃ የማወቅ ፍቅር በጊዜው በሀገር ውስጥ ትምህርት የሚሟላ አልነበረም፡፡ ኒውዮርክ 'Eastman School of Music' ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.1954 ዓ.ም.) በምዕራብ ክላሲካል ሙዚቃ ትምህርት አጠናቀዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው "ብሔራዊ የሙዚቃ ትምህርት" ቤት የሚባለውን፣ ኋላ ላይ፤ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመከፈቱ መሠረት የኾነውን ማሰልጠኛ፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፯ ያህል ክፍሎችን በውሰት በመጠየቅ ማስተማር ጀመሩ፡፡

ይህ ሥልጠና እየተካሔደ እያለ፤ ንጉሠ ነገሥቱን በማሳመን "ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት" እንዲከፈት ከፍተኛ የማሳሰብ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ቡልጋሪያ በነበራቸው ጉብኝት፣ "ምን እናድርግልዎ” ተብለው ሲጠየቁ፤ 'ሶፊያ ስቴት ኮንሰርቫቶሪን' የመሰለ (ጎብኝተውት ነበር) የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሠራላቸው፣ ጠይቀው የአሸናፊ ከበደን ምኞት ዕውን አድርገዋል፡፡

አሸናፊ ከበደም የመጀመሪያው የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በመኾን፣ ሥርዓተ ትምህርቱን ቀርፀዋል፡፡ (እዚህ ላይ፥በወቅቱ የሙዚቃ መምህራኑ ሙሉ በሙሉ ምዕራባውያን እንደነበሩ ልብ ይሏል፡፡) የሚገርመው፤ ይህንን ኹሉ ያደረጉበት ዕድሜ የ25 ዓመት ወጣት በነበሩበት ጊዜ መኾኑ ነው፡፡

፫- Wesleyan University-
M.A.1969;Ph.D.1971

ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን በርዕሰ መምህርነት ከመሩ በኋላ፤ በሌላ ሕንዳዊ ዳይሬክተር ተተክተው፣ አሸናፊ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ 'Wesleyan University' በመሔድ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. (1969 እ.ኤ.አ.)፣ እንዲሁም፤ የዶክቶሪያል ጥናታቸውን እና ትምህርታቸውን ደግሞ፤ በ፲፱፻፷፬ ዓ.ም. (1971 እ.ኤ.አ.) 'ኤትኖሚውዚኮሎጂ' በሚባለው የጥናት መስክ አጠናቀዋል፡፡

ዶክተሬታቸውን የሠሩበት፤ The music of Ethiopia: Its Development and Cultural Setting. Ph.D. Dissertation, Wesleyan University. 1971፣ የተሰኘው ጥናት ብዙዎች የሚጠቅሱት ትልቅ ጥናት ነው፡፡

ከማስትሬት ትምህርታቸው በኋላ አሸናፊ ከበደ በረዳት ፕሮፌሰርነት በኢትኖሚውዚኮሎጂ ፕሮግራም ዳይሬክተርነት 'በኩዊንስ ኮሌጅ' (1970-1976 እ.ኤ.አ.) አገልግለዋል፡፡

*የሙዚቃ ቅማሬዎች
--------------------------

'አማራ ሩምባን` ወደ ባለ ዋሽንቱ እረኛ፣ 1967

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት የባህል ቡድን “አማራ ሩምባ” የምትባል ባህላዊ ጨዋታ ይጫወቱ ነበር፡፡ ያቀነባበራት አሌክሳንደር ሀገር የተባለ የባህል ቡድኑን የመሠረተ ትልቅ ሙዚቀኛ ነበር፡፡ አሸናፊ ከበደ- የዚችን ሙዚቃ ቲም፤ እንደ ርዕስ በመዋስ፤ ወይም እንደ ጥቅስ በመውሰድ፤ “ባለዋሽንቱ እረኛ” ብለው፤ ኮምፖዚሽኑን አራቅቀው፣ ለፔንታቶኒክ ሙዚቃ ሞዴል የሚኾኗቸውን የሀንጋሪ ሙዚቀኞች የቤላ ባርቶክን እና የዞልታን ኮዳይን የኦርኬስትሬሽን አስተሳሰብ በመውሰድ፣ ከሩቅ ምሥራቅ ሜሎዲካል አካሔድ ጋር በማዋኀድ ዐዲስ ድርሰት አድርገው አቀረቡት፡፡

እዚህ ውስጥ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር፤ አሸናፊ ከበደ የምዕራቡን ክላሲካል ሙዚቃ ቢማሩም፤ የሀገራቸውን ዜማዊነት የሚጎላበት ፔንታቶኒካዊ ሙዚቃ በምን ዓይነት ዘይቤ እንደሚያቀርቡት በጥልቀት መመርመራቸውን ነው፡፡
ይህን ሲያስቡ፡- ለዚህ ዓይነቱ ፍልስፍና ቅርብ የኾኑትን በፔንታቶኒክ ኦርኬስትሬሽን እና ኮምፖዚሽን የታወቁትን የሀንጋሪ ሙዚቀኞችን ነበር በሞዴልነት የመረጡት፡፡

ምንም እንኳ ለቅንብር ፍልስፍናው የሀንጋሪን ታላላቅ ኮምፖዘሮችን አርአያ ቢያደርጉም፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባሕርይ እና አድራሻ ፔንታቶኒክ ስኬል እና ሞድ በመጠቀም ብቻ ከሐንጋሪ ጋር እንደማይመሳሰል በማሰብ፤ ሰፊ ጥናታቸውን ደረጉት በጃፓን 'ኩቶ' ክላሲካል ሙዚቃ ላይ ነበር፡፡

ይህን የሦስት ባህሎች ውኅደት የያዘ ሥራ፤ በ1967 እ.አ.አ. ሀንጋሪ ቡዳፔስት መድረክ ላይ ባቀረቡበት ጊዜ ብዙዎች ወደ አዳራሹ የገቡት በአንድ ጥቁር ሙዚቀኛ ለመሳቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰሙት ሙዚቃ ለዚህ ምኞታቸው የተመቻቸ አልነበረም፡፡

በ1968 እ.አ.አ. ይህንን እና ሌሎች አራት ሙዚቃዎችን በኤል.ፒ. ለማስቀረጽ የተጫወተው 'Hungary State Orchestra' የነበረ ሲኾን፤ ሎረንት ኮቫቼ የተባለው ታላቅ ፍሉት ተጫዋች ዋናዋን ቴም የኾነችውን ዜማ በፍሉት ከኦርኬስትራው ጋር ተጫውቶ አስቀርፆታል፡፡ -Koturasia for Koto,Violin and B-flat clarinet- 1974 - Peace Ethiopia - Shoes of Ladder - The Ulcer of Love - The life of our Nation

- Minuet for flutes and Pipes(in the spirit of Ethiopian Washint and embilta, በተጨማሪ የደረሷቸው፣ የክላሲካል ሙዚቃ መሠረት ያላቸው ቅማሬዎቻቸው ናቸው።

* "ጥቁሩ ኮዳይ"

የአሸናፊ ከበደ “ባለዋሽንቱ እረኛ” በሀንጋሪ ቡዳፔስት መድረክ ላይ በቀረበበት ጊዜ፤ ብዙዎች ይህንን ተአምር ማመን አልቻሉም፡፡ ኦርኬስትራው ቦታውን ከያዘ በኋላ፣ የኦርኬስታራው መራኄ ሙዚቃ (ኮንዳክተር) ኾኖ የቀረበው ወጣት፤ በፍፁም ሙዚቃውን ይመራል፣ ሙዚቃውንም ጽፎታል ብለው ለማመን ተቸግረው ነበር፡፡ የክላሲካል ሙዚቃ ለአፍሪቃውያን ባህል ሩቅ ነው ብሎ ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ከመድረኩ ተአምራዊ ክዋኔ በኋላ ግን፤ የሀንጋሪ ጋዜጦች የአሸናፊን ምስል፤ “Black Kodaly`` (ጥቅሩ ኮዳይ) በሚል ቅጽል ይዘው ወጡ፡፡

ዞልታን ኮዳይ፤ በሀንጋሪ ሙዚቃ ውስጥ ትልቁ ብሔራዊ ሙዚቀኛቸው ነው፡፡ “ኮዳይ ሥነ ዘዴ” ተብሎ የሚታወቅ ዓለማቀፋዊ ሙዚቃ የማስተማሪያ ዘዴም አለ፡፡ የሀንጋሪን ሙዚቃ ትልቅ ያደረጉት ኮዳይ እና ባርቶክ ናቸው፡፡ የዚህን ትልቅ ሙዚቀኛ ስም በቅጽልነት ለአሸናፊ ከበደ መስጠት እንደ ትልቅ ክብር የሚታይ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፤ አፍሪቃውያን ከምዕራባዊ ሳይነጻጸሩ በራሳቸው መደነቅ አይችሉምን? የሚል ጥያቄም የሚስነሳ ነው፡፡

*የጥናትና ምርምር ሥራዎች፣
----------------------------------

ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፥ በእርሳቸው ትጋት እና ሥራ ልክ ተከታይ አላፈሩበትም እንጂ ትልቅ ሥራ ያበረከቱት በሙዚቃ በምርምሩ ዘርፍ ነው፡፡ ከመመረቂያ ጽሑፎቻቸው በተጨማሪ፣ በበርካታ ስመ ጥር ጆርናሎች ላይ የወጡ አርቲክሎች፣ እና 'Roots of Black Music' የተሰኘው መጽሐፋቸው እጅግ ታዋቂነት ያላቸው፣ የበርካታ ተመራራማሪዎችን ትኩረት የሳቡ ምርምሮቻቸው ናቸው፡፡

- የዶክትሬት መመረቂያ ጥናት; The music of Ethiopia: Its Development and Cultural Setting. Ph.D. Dissertation, Wesleyan University. 1971ሲኾን፣ ሌሎች ጥናቶቻቸው ደግሞ፥ - `The Azmari, Poet-musician of Ethiopia` The Musical Quarterly, 1975, Oxford University Press.

- `Zemenawi Muzika: modern trends in traditional secular, music of Ethiopia` The Black Perspective in Music, Vol 4, No 3., pp291-301,1976 ከዋና ዋናዎቹ የሚጠቀሱት ናቸው።

*መጻሕፍት፤ ---------------

1- Confession `ንስሐ`፦

የአንድ አሳዛኝ ኢትዮጵያዊ ታሪክ በአሜሪካን የሚተርክ ልቦለዳዊ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራ፣ 1960 እ.ኤ.አ.
“ይህኛው ሥራቸው ከራሳቸው ሕይወት እና መጨረሻ ላይ በሕይወታቸው ማምሻ ጋር ከተከሰቱ ገጠመኞቻቸው ጋር ይመሳሰላል፤” በሚል አንዳንዶች የራሳቸው የአሸናፊ ከበደን ሕይወት የሚተርክ ሥራ ነው እስከማለት ይደርሳሉ፡፡

2- የሙዚቃ ሰዋስው፦

የሙዚቃ ሰዋስው ፤ ምዕራባዊ መሠረት ያላቸውን ከግሪክ፣ ከላቲን እና ከጀርመን የቃል ሥርው የተፈጠሩ ሙዚቃዊ ቃላትን በአማርኛ ለመተርጎም፣ ሙዚቃዊ ጽንሰ ሐሳቦችንም ከቋንቋችን ለማዋኀድ ጥረት የተደረገበት፤ "ምንም በሌለበት" የተገኘ የፕ/ር አሸናፊ የወጣትነት ዘመን ሥራ ነው፡፡ እንደ “ሙዳየ ቃል” ሊያገለግል የሚችል ኅትመትም ነው፡፡ አስፋው ዳምጤ ለዚህ ሥራ ትልቅ አድናቆት አላቸው፡፡

3- Roots of Black music፡ the vocal, instrumental, and dance heritage of Africa and Black America. 1982፡-

“የአንድን ሕዝብ የሕይወት ዘይቤ በሙዚቃ ውስጥ ማሳየት የጥናት ግቡ የኾነውን 'የኤትኖሚውዚኮሎጂን' የጥናት ግዴታ በሚገባ የተወጣበት ምሁራዊ ሥራው ነው” በማለት ፕሮፌሰር ዴቪድ አሊስተር (የዌስሊያን ዩኒቨርሲተ ፕሮፌሰር) የሚመሰክሩለት ግሩም የፕ/ር አሸናፊ ከበደ የጥናት ሥራ ነው፡፡

የመጽሐፉ ዋና ትኩረት፤ በብዙ የአፍሪቃ ሙዚቃ አጥኚዎች ትኩረት የተነፈገውን 'የኦሪየንታል አፍሪቃ' ሙዚቃን ይመለከታል፡፡ በርካታ የሙዚቃ ሊቃውንት፣ የአፍሪቃ ሙዚቃን ሲያጠኑ ትኩረት የሚያደርጉት፤ ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ሙዚቃ እና የከበሮ ሚና ጎልቶ የሚሰማባቸውን ሕዝቦች ባህል ነው፡፡ ይህ የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ጥናታዊ ኅትመት ግን፤ - “Oriental Africa` The Islamic Culture of the North, - The Nile cultures of North east Africa- pre- Islamic traced elements of North Africa,

- Madagascar with its South east Asian Influence. ላይ አተኩሮ የሚያጠና እና ያልተዳሰሱ የድምጽ፣ የሙዚቃ መሣሪያ፣ እና የዳንስ ቅርሳዊ ሀብቶችን በጥልቅ ፍተሻ የሚያሳይ ጥናት ነው፡፡

ይህንን በሚያጠኑበት ወቅት፡- "ለምዕራቡ ዓለም የቅኝ ግዛት ተጽዕኖ ተዳርጓል፤" የሚሉትን የአፍሪቃ ሙዚቃ ዓይነታ በተለይ፥ በምዕራብ አፍሪቃ ሙዚቃ ውስጥ ያለውን ገጽታ ሊያሳዩን ይሞክራሉ፡፡
ይህንን የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ተቋቁመው ዓለማቀፋዊ ዕውቂያ ለማግኘት የበቁትን ሙዚቀኞች፤ እነ፦ Akin Euba, Fela Sowande, J.H. Kwabena Nketia, Halim El-Dabh ታሪካቸውን እና ከትግላቸው ጋር ያስተዋውቁናል፡፡

በእኔ አስተያየት፡- በዚህ ጥናታቸውም ኾነ በሙዚቃ ቅንብሮቻቸው 'ለኦሪየንታል ባህል' ያሳዩትን አዝማሚያ ተከትለን ስንጓዝ፤ የአፍሪቃ ሙዚቃ ከቶውንም ከቅኝ ገዢዎቹ ሐሳብ እና ባህል ነጻ አለመውጣቱን፤ አሳታሚ እና አስተዋዋቂ ኾነው ለዓለም የሚያስተዋውቁትም ቅኝ ገዢዎቹ መኾናቸውን ካወሱ በኋላ፤ ከዚህ ችግር ነጻ ሊኾን የሚገባው በቅኝ ያልተገዛ ሕዝብ መሐል የተፈጠረው የኢትዮጵያ ሙዚቃም እንኳ ቢኾን ከዚህ ተጽዕኖ አለማምለጡን ይነግሩናል፡፡

የባህል አድራሻችን ሊኾን የሚገባው የሩቅ ምሥራቆቹ እና የመካከለኛ ምሥራቅ ባህል መሠረት “ኦሪየንታል ካልቸር” ሊኾን እንደሚገባው በዲስኮርሳቸው ይሞግታሉ፡፡
የራሳቸው ፍልስፍና እና የኮምፖዚሽኖቻቸው አዝማሚያም 'ኦሪየንታሊዝም' ላይ ያተኩራል፡፡ በኋላኛው ዘመናቸው የቡዲስት ሃይማኖት ተከታይ መኾናቸውን እዚህ ጋር ከደመርነው፤ በዚህ ፍልስፍና ፍፁም መመሰጣቸውን እንረዳለን፡፡

*ቤተሰባዊ ኹኔታ፡
------------------

ፕ/ሮ አሸናፊ ከበደ ከኹለት ትዳሮቻቸው፥ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ከመጀመሪያዋ ባለቤታቸው ወ/ሮ ዕሌኒ ገብረ መስቀል፤ ኒና አሸናፊን (የሕግ ባለሙያ) እና ሠናይት አሸናፊን (አክትረስ) ሲያፈሩ፤ በኋላ ካገቧቸው ፖሊሽ አሜሪካዊቷ ኢትኖሚውዚኮሎጂስት ዶ/ር ሱዛን ሚትኮቪች ደግሞ፤ ያሬድ አሸናፊ የተባለ ወንድ ልጅ አላቸው፡፡

*የመጨረሻው ስንብት
-------------------------

አስገራሚ ኹኔታ ፕ/ር አሸናፊ ከበደ ወደ'ዚች ምድር የመጡባት ዕለት እና የተሰናበቱባት ዕለት “ሜይ-5” መኾኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የአሟሟታቸው ኹኔታ “ይህ ነው” የሚባል የተጨበጠ ነገር የለውም፡፡

አብሮ አደጎቻቸው፤ ዳግማዊ ምኒልክ አካባቢ ነዋሪ የኾኑት እነ አባባ አበራ ሞልቶትን የመሰሉ ወዳጆቻቸው፤ እንደሚሉት፡-

“ኹለት ወረቀቶች እንዳይለት ልኮልኝ ነበር፤ አንዱ አዲስ የጀመረው ጥናት ነበርና - ስለዚህ ምን ትላለህ? ይህ ዐዲሱ ሙከራዬ ነው፡፡ ግን እንደ ራዕይ እንደሚታየኝ ከመጪው ሐምሌ በፊት ወደ ሌላ አሕጉር እሔዳለሁ፤ ሞቼ ሥጋዬን ትቼ ወደ ኒርቫና እሸጋገራለሁ፡፡ ከአምላኬ ጋር አንድ ላይ እኾናለሁ፡፡” እንዳሏቸው ይገልፃሉ፡፡

አቶ በቀለ አሳምነው የሚባሉ ከአሸናፊ ጋር የአንድ አያት ልጆች የኾኑት ወንድማቸው እንደሚሉት፤
“ለታናሽ ወንድማቸው ደውለው፤ ከሳምንት በኋላ የለሁም ማለታቸውን፣ ስለመንፈሳዊ ጉዞ እየተናገሩ፤ ከ60 ዓመታት በኋላ መኖር ጥቅም የለውም እንዳሏቸው፤” ከታናሽ ወንድማቸው ለቅሶ ላይ መስማታቸውን ዋቤ አድርገው ገልፀዋል፡፡

ከቤተሰብ በኩል፤ ለፖሊስ ደውለው ያገኙት የተጨበጠ መረጃ ባይኖርም፤ “አዝማሚያው ራስን ማጥፋት ይመስላል፤” እንዳሏቸው ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል እንደሚባለው ወደ 'ኒርቫና' ለመሔድ ለቀናት ሳይቀመጡ እና ምግብ ውኃ ሳይውዱ በመቆም በድንገት ራሳቸውን ስተው ወድቀው ሕይወታቸውን አጥተዋልም ይባላል፡፡ በአስደናቂ ኹኔታ፥ ይህ የኾነበት ዕለት፥ May 5,1998 እ.ኤ.አ.(በ፲፱፻፺ ዓ.ም.) የ፷ኛ ዓመት የልደት ቀናቸው ላይ ነበር፡፡

Report Page