*/

*/

Source

* ከሠርፀ ፍሬ ስብሐት
ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

---------------
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ሰኔ ፴ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም. የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን መርቀው ሲከፍቱ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር፤ አስተዋይ ሰው ካነበበው፣ የሙዚቃ ትምህርት ዐቅድ ምን ዓይነት መልክ መያዝ እንዳለበት አመልካች ማዕሠረ ቃል ነው።

ሀገረ ሰብዓዊው "ነባሩ ጥንታዊ ዕውቀት"፣ "ከምዕራባዊው ዘመነኛ ዕውቀት" ጋር እንደምን ተዋዶ፣ ተዛምዶ እና ተዋሕዶ መጓዝ እንዳለበት በጥብቅ የሚያሳስብ ንግግር ነው።
ይህ ንግግራቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን መርቀው ሲከፍቱ ካደረጉት ንግግር ጋር ተመሳሳይ ነው።

ንግግራቸው፥ ፍሬድሪክ ሔግል፣ "መንፈስ"(Spirit) የሚባለውን አኃዝ ለያይቶ "Personal Spirit, Objective Spirit" እያለ:- "ብቻውን ስለቆመ ደካማ የግል መንፈስ" እና "ስምምነት ስለፈጠረ ከሌላ ጋር የተዋሐደ መንፈስ" (አንጻራዊ መንፈስ) የሚያስተምረውን ቁም ነገር ያስታውሰናል። ይህንን አመሥጥረው እና አራቀው ያስተማሩን ዶ/ር ዕጓለ ገብረ ዮሐንስ "በተዋሕዶ ከበረ" የሚለውን የነገረ መለኮት አስተምህሮ፥ ለትምህርት አስተማሣሊ አድርገው ያቀረቡበትን ታላቅ ምክረ ሐሳብ መረዳትን የሚያጠይቅም ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጥንታዊ የትምህርት መሠረት ያለው ሀገር፣ ዘመናዊ ተማሪ ቤት ሲያቋቁም፣ ሊያስተውል የሚገባው ቁም ነገር፣ ኹለት በየራሳቸው የቆሙ የትምህርት "መናፍስትን" [አንጻረ አድማሳትን] እንደምን ማዋሐድ ይቻላል? የሚለውን ጽሙና የሚጠይቅ ጉዳይ ሊኾን ይገባዋል። እኔ እንደማምነው፥ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትም ይህ ጉዳይ በብርቱ እንዳሳሰባቸው ቀጥሎ ከምናነበው ንግግራቸው እንገነዘበዋለን።

==============

“የኢትዮጵያ ሕዝብ በተፈጥሮው፣ የኪነ-ጥበብ ስሜትና ችሎታ እንዳለው ሥራው ይመሰክራል፡፡ ለታሪኩና ለኑሮው መታሰቢያ፣ ታላላቅ ሐውልቶችንና ሥዕሎችን የሠራና የሚሠራ ሕዝብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታውንም ኀዘኑንም በግጥም፣ በቅኔ፣ በዘፈንና በዜማ የመግለጥ ችሎታና ባህል ያለው ከመሆኑም በላይ፣ ከረጅም ዘመን አንስቶ የብሔራዊ ቋንቋ ባለቤት በመኾኑ፤ የቋንቋው ምሳሌያውያን ንግግሮች፣ የአነጋገር ፈሊጦችና ግጥሞች፤ የሕዝቡን ብስለትና አስተዋይነት ይመሠክራሉ፡፡

ሕዝባችን ከጥንት ከአባቶች ሲያያዝ በመጣው እንደ ዋሽንት፣ ክራር፣ በገናና መለከት በመሳሰለው የሙዚቃ መሣሪያ ደስታውንና ኀዘኑን በልዩ ልዩ ዜማዎች እየገለጠ እስካሁን አቆይቶናል፡፡

አንድን ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ የሚያሰኘው፣ በአካባቢውና በትምህርት ያገኘውን ዕውቀት፣ በአንድነት አዋሕዶና አጣምሮ ሲሠራበትና፣ ለአገሩ ክብርና ታሪክ በጊዜው መሥዋዕት ኾኖ፣ ለተተኪው ትውልድ ጥንታዊ ታሪኩንና ባህሉን አስተላልፎ ሲገኝ ነው፡፡

የጊዜው ኹኔታ እና አስቸጋሪነት ምክንያት ካልኾነ በቀር፣ ለኢትዮጵያ ታላቅ ሥራ ያልሠራ ንጉሠ ነገሥት አይገኝም፡፡ አባቶቻችን ጊዜው በሚፈቅደው መጠን ለአገራቸው ሠርተው አልፈዋል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ደግሞ፤ ባለፈው ዘመን የታቀደው እና የተጀመረው የሥልጣኔ ሥራ ሁሉ፣ በተግባር በመዋል ላይ ኾኖ ይገኛል፡፡ እኛም ለአገራችን ልማት እና ዕድገት፣ ለሕዝባችን ደህንንት እና ሰላማዊ ኑሮ፣ በየጊዜው ያደረግነውና የምናደርገው ድካም፣ እንዲህ እንደዛሬው ፍሬ ሰጥቶ ሲገኝ፣ የሚሰማን የመንፈስ ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡

በመሠረቱ፤ ታሪክም ኾነ የአገር ባህል፣ በየጊዜው እንደገና እየዳበረ የሚሔድ ነገር በመኾኑ፣ በዚህ በሙዚቃ ትምህርት ቤት ላሉትና፣ በሌላውም የትምህርት ድርጅት ውስጥ ለሚገኙት ኹሉ፣ ጥንታዊ ባህላችንን እና ታሪካችንን መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ፣ ከፍተኛ ደረጃ እንዲይዝ መትጋትና መጣር እንዳለባቸው፣ በዛሬው ቀን ደግመን ልናስገነዝባቸው እንወዳለን፡፡

ያለፈው ትውልድ፣ በጊዜው በነበረበት ችግርና እንቅፋት ምክንያት፣ ያሰበውን ሥራ ከፍጻሜ ሳያደርስ፣ ለኛ ለተተኪው ትውልድ ያስተላለፈው ደግሞ፣ የጅምር ውዝፍ ኾኖ እንዳይገኝ፣ በርትቶና ተግቶ መሥራት አስፈላጊ መኾኑንም ደጋግመን ልንገልጠው እንፈቅዳለን፡፡

ይህ ትምህርት ቤት እንዲቋቋም ያሰብንበት ምክንያት፣ ለውጪው ሀገር የሙዚቃ ትምህርት ብቻ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ፤ የአገራችን የዜማ ባህልና ሥርዓት ተጠናቆ በዚሁ እንዲደረጅ በማሰብ ነው፡፡ ከዚህም በላይ መንፈሳዊ ዜማችን እና ባህላችን፣ ከዓለማዊው ጋር ተባብሮ እንዲገኝ ለማድረግ ነው፡፡

ስለዚህ ተማሪዎች የኾናችሁት፣ በርትታችሁ እንድታጠኑ፣ እናንተም መምህራን፣ የተጣለባችሁን ኃላፊነት ተገንዝባችሁ፣ በሥራችሁ እንደትተጉና መልካም ውጤት እንደታስገኙ ይጠበቃል፡፡

ወዳጃችን የቡልጋሪያ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት፣ ይኽንን ሕንጻ አሠርቶ፣ ለዚህ ቁም ነገር ላለው የሙዚቃ ትምህርት ሥራ እንዲውል ስለሠጠንና፣ የወዳጅነት ስሜቱንም ስለገለጠልን ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ሥጦታው ከፍ ያለ ግምት የሚሠጠው ነው፡፡ ሕንጻውም ‘ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት’ ተብሎ እንዲጠራ ፈቅደናል፡፡

ኹሉንም አስጀምሮ የሚያስፈጽም ፈጣሪያችን፣ የዚህን ትምህርት ቤትና፣ የሌሎችንም ትምህርት ቤቶች ሥራ፣ እዚህ ደርሶ ለማየት እንዳበቃን ኹሉ፣ ወደፊትም፤ በበለጠ ተስፋፍቶ ለማየት እንዲያበቃን እንለምነዋለን፡፡” ብለዋል፡፡
..................................

ከንግግር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የማሠልጠኛውን ክፍሎች እና ከቡልጋሪያ መንግሥት የተሰጡትን የሙዚቃ መሣሪያዎች ተመልክተዋል፡፡ በመጨረሻም፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በተገኙበት፣ የምረቃ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው፣ የሙዚቃ ሥልት እና የድራማ ትርኢት ታይቷል፡፡ በምርቃቱ በዓል ላይ፤ ክቡራን ሚኒስትሮች፣ የውጪ አገር መንግሥታት እንደራሴዎች፣ ታላላቅ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

-----------------

ዐዲስ ዘመን፡ ኀምሌ ፩ (1) ቀን ፲፱፻፷፪ (1962) ዓ.ም.

------------------

Report Page