*/

*/

Source

#ካራማራ_ኢትዮጵያዊው_የድል_ቀን (ዳግማዊ ዓድዋ)

ክፍል 5 ( የመጨረሻ )

የካቲት 23 /1970 ዓ.ም የዓድዋ ድል እለት የኢትዮጵያ ጦር በጭናቅሰን እና በቆሬ በኩል ወደ ጅጅጋ አቅጣጫ የተጠናከረ ቅንጅታዊ የጎህ መጥቃት ዘመቻ ከፈተ ። የሶማሊያ ጦርም ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ብሎ ካልጠበቀው አቅጣጫ በመወጋቱ ተደናገጠ ። ጅጅጋንም ላለመልቀቅ ተሟሟተ ። ሶማሊያ በዚህ መደናገጥ ውስጥ እያለች ከጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ተከፈተባት ። የሶማሊያም ሰራዊት ጅጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል ። በመሆኑም ከጅጅጋ በስተምእራብ በኩል ባለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን በመስራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላከለ ። ሆኖም በለስ አልቀናውም ።

ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመሆኑ አጋዥ ሰራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም ። በውጤቱም የካቲት 26 ረፋድ ላይ በካራማራ ከባድ ሽንፈት ተጎነጨ ። በውጤቱም ከሞትና መቁሰል የተረፈው የጠላት ሠራዊት መሳሪያውን እያንጠባጠበ ጅጅጋን በመልቀቅ ወደ ሀርጌሳ መስመር ፈረጠጠ ።

እሁድ የካቲት 26/1970 ዓ/ም ላይ በአከባቢው የነበረ ሰራዊት ወድቃና ተዋርዳ የነበረችውን 💚💛❤ ሰንደቃችንን መልሶ ከፍ አድርጎ በክብር ሰቀለ ። የዛሬ 42 አመት እንዳይድን እንዳይሽር ተደርጎ የተሰበረው የዚያድባሬ ተስፋፊ ኃይል በቀጣይ ቀናቶች ጦርነቱን በይፋ አቁሞ በወረራ ተቆጣጥሯቸው ከነበረው ከቀሪ የኢትዮጵያ ሉኣላዊ መሬቶች ተጠቃሎ ወጣ ። ይህ ድል እውን እንዲሆን ግን የበርካታ ውድ ኢትዮጵያዊያን የደምና የአጥንት መስዋእትነት አስፈልጎ ነበር ። ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪም የወንድም ህዝብ ልጆች የሆኑት የኩባዊያንና የደቡብ የመናዊያን ውድ የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበታል ።

የደረሰው ጉዳት በአጭሩ ይህን ይመስላል ።

ሠራዊት የሞተ የቆሠለ የተማረከ

ኢትዮጵያ 18,000 29,000 450 ኩባ 163 1 የመን 100

ሶማሊያ 15,900 26,200 1,785

የካራማራ ድል ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሉአላዊነት ያላቸውን ቀናኢነት ቀፎ እንደተነካ ንብ በህብረት በመቆም ገልፀውታል ። ለሠንደቃቸው ያላቸውን ልባዊ ፍቅር ውድ መስዋዕትነት በመክፈል በደማቅ የደም ቀለም ፅፈውታል ። ለዘመናት የተገመደው የማይበጠስ አንድነታቸውን በደም ፍሳሻቸውና በአጥንት ፍላጫቸው በድጋሚ በፅኑ መሠረት ላይ ገንብተውበታል ።

ከታላቁ የዓድዋ ድል ቀጥሎ የኢትዮጵያዊያን ህብረትና አንድነት ማሳያ የሆነው የካራማራ ጦርነት ለማመን የሚቸግሩ በጀብድ የተሞሉ ጀግንነቶች በተናጠልና በቡድን ተከናውነውበታል። ተዘርዝረው ከማያልቁ የሠራዊቱ ጀብዶች መካከል ለምሳሌ ያህል ሁለቱን ልጥቀስ ።

የሀረር አካዳሚና የበረራ ት/ቤት ጥምር ምሩቅ የሆኑት የአዲስ አበባው ፍሬ የአየር ኃይሉ ነብር ጀግናው ብ/ጀ ለገሰ ተፈራ በF5-E ጀታቸው አማካይነት በአየር ላየር ላይ ውጊያ አምስት የሶማሊያ ሚግ 21 ጀቶችን በመምታት ከአየር ወደ መሬት አራግፏቸዋል።

በርካታ ጀብድ ፈጽመው የድሉ መጨረሻ ሰአት ላይ በፊልቱ ግንባር ላይ አውሮፕላናቸው ተመትቶ በጠላት ተይዘው ለ11 አመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች የስቃይ ህይወት አሳልፈው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ለወደር የለሽ የጀግንነት ስራቸውም በጊዜው የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ የሆነውን የህብረተሠባዊት ኢትዮጵያ ወደር የለሽ የጀግና ሜዳይ ተሸልመዋል ።

ሌላው ጀግና ደግሞ የእናት ሀገር ጥሪ ሰምቶ በለጋ እድሜው ከቀድሞ ወለጋ ክ/ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ የመጣው ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ነው።

ጀግናው አሊ በአቡሸሪፍ ግንባር ሶስት የጠላት ታንኮችን በእጅ ቦንብ በማቃጠል በግንባሩ ለነበረው ድል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ። ለዚህም ስራው የላቀ የጀብድ ሜዳይ ተሸላሚ ሆኗል ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአራቱም የሀገራችን ማዕዘናት የብሔርና የሀይማኖት አጥር ሳያግዱት በጠነከረ የአንድነት መንፈስ በመላበስ ደሙን አፍስሶ ፣ አጥንቱን ከስክሶ ነው ይህንን ታላቅ ድል ማስመዝገብ የተቻለው።

ይህ ድል ዕውን እንዲሆን ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪም የወንድም ህዝብ ልጆች የሆኑት የኩባዊያን የሩሲያውያንና የደቡብ የመን ውድ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበታል።

ዘንድሮ 43 ዓመት የሚሞላውን የካራማራ ድል የመታሠቢያ በዓል ነገ አርብ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት የመታሠቢያ ፓርክ (ትግላችን ሐውልት) ከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ ሀገር ወዳድ እና ታሪክን ዘካሪ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በዕለቱ በቦታው በመገኘት የድሉን በዓል ላይ እንድትታደሙ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

መንግስት በቀጣይ ይህንን ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መንፈስ በህይወትና በአካል መስዋዕትነት የከፈሉበትን ታላቅ ሀገራዊ የህዝብ ድል ትኩረት ሰጥቶት በቀጣይ ጊዜያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲከበር እና ትውልዱ አባቶቹ ከሰሩት ከዚህ የጋራ የድል ታሪክ ተምሮ አንድነቱን እንዲያጠነክር አበክሮ እንዲሰራ ጥሪ እናስተላልፋለን።

ተፈፀመ!!!!

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖቹ የካራማራ ሠማእታት ይሁን !!!

ኢትዮጵያ ምንግዜም በክብር ትኑር !!!

#ካራማራ_43
#ዳግማዊ_ዓድዋ
#የአንድነት_ተምሳሌት
#የጋራ_የድል_ታሪክ
#የደም_አሻራ_ውርስ
#የኢትዮጵያ_ህዝብ_ድል
#ኮረማሽ
#Ethiopia

#አብዮታዊው_ሰራዊት_ገፅ

Report Page