*/

*/

Source

በጋራ የመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ባሉ ጫኝና አውራጆች ነዋሪዎች እየተማረሩ መሆናቸውን ገለጹ
ሪፖርተር 20 January 2021

በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ዕጣ የደረሳቸው ነዋሪዎች፣ ዕድሉ ስለገጠማቸው ደስተኛ ቢሆኑም፣ ደስታቸውን አጥፍቶ ‹‹ምነው ባልደረሰኝ›› እስከ ማለት ድረስ የሚያማርር የጫኝና የአውራጆች ፈተና እየገጠማቸው መሆኑን በምሬት እየተናገሩ ነው፡፡

መንግሥት የነዋሪዎችን ችግር ተረድቶና ከግምት ውስጥ አስገብቶ የገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት 20 በመቶ ከፍለው በማጠናቀቃቸው ቁልፍ የተረከቡ ቢሆንም፣ ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ ዕቃቸውን አስጭነው ሲሄዱ፣ ‹‹መንግሥት አደራጅቶናል፣ ፖሊስም ማረጋገጫ ሰጥቶናል›› የሚሉ ወጣቶች፣ ለደረሳቸው ቤት ከከፈሉት ቅድመ ክፍያ ያልተናነሰ ዕቃ ማውረጃ እንደሚጠይቋቸው፣ ለመክፈል ግን አቅም እንደሌላቸው ሲነግሯቸው ካስጫነው ባለቤት ውጪ ቤተሰቦቹ እንኳን ማገዝ እንደሚከለከሉ ይናገራሉ፡፡

በኮዬ ፈጬ፣ ቂሊንጦ፣ ሰሚትና ቦሌ አራብሳ የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው ዕድለኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በወረዳዎች አደራጅነት ‹‹ተደራጅተናል›› ባሉ ጫኝና አውራጆች አማካይነት ዕቃን ለመጫንና ለማውረድ የተጋነነ ሒሳብ እየተጠየቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጋራ የመኖሪያ ቤቶቹ አካባቢ ባጅ ያንጠለጠሉና ‹‹ወረዳው ነው ያደራጀን›› የሚሉ ጫኝና አውራጆች፣ የመኖሪያ ቤት ዕቃ ለማውረድና ለመጫን ከ3,000 እስከ 10,000 ብር እንደሚጠይቁና ነዋሪዎቹ በዋጋ የማይስማሙ ከሆነ ዕቃዎቻቸውን ለማውረድና ለመጫን እንደማይችሉ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በራሳቸው የሰው ኃይል ዕቃን ለመጫንና ለማውረድ እንደማይችሉ አስታውቀው፣ በዋጋ አለመስማማት ምክንያት በሚፈጠረው ችግር የሚመጣው የፖሊስ የፀጥታ ኃይልም ‹‹ተስማሙ›› ከማለት ውጪ ምንም እልባት ሊሰጥ አለመቻሉን በማስረዳት፣ የሚመለከተው አካል ለችግሩ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ወረዳዎቹ ወጣቶችን በማደራጀታቸው ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌላቸው የሚገልጹት በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የሚኖሩት ነዋሪዎች፣ እነሱም በመረጡት አካል ንብረታቸውን የመጫን፣ የማውረድና የማዘዋወር መብታቸው ሊጠበቅላቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ እንደሚሉት፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ተከራይቶም ሆነ ገዝቶ ለመግባት፣ አንድ ነዋሪ ለዕቃ ማጓጓዣ ከ500 እስከ 800 ብር እንደሚያወጣ አስታውቀው፣ በተጨማሪ ዕቃ ለማውረድ ከ3,000 እስከ 10,000 ብር መጠየቁ ነዋሪውን ለከፍተኛ ምሬት እንዳጋለጠው አስታውቀዋል፡፡ አያይዘውም የሚመለከተው አካል ለችግሩ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ወይም መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀው፣ አለበለዚያ ይህ አካሄድ እየጎለበተ መጥቶ ነገ ተነገ ወዲያ ‹‹እኛ ሳንፈቅድ ከቤት መውጣት አትችሉም›› ወደሚል ሊሸጋገር እንደሚችል መታወቅና ከእንጪጩ ሊስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የየአካባቢዎቹን የፖሊስ መምርያ ኃላፊዎችና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ሪፖርተር ለማነጋገር ያደረገው ጥረት፣ ኃላፊዎቹ ምላሽ ለመስጠት በመቆጠባቸው ምክንያትና አንዳንዶቹም ‹‹የተከለከሉት እነማን ናቸው›› በማለት ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈጋቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Report Page