*/

*/

Source
Ortodox የእመብርሀን ወዳጆች
12. ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያው ማትያስ ጌታን በሸጠው በአስቶርቱ ይሁዳ ምትክ የተሾመ ሐዋርያ ነው ። ሐዋ 1 : 15 - 26 በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊነቱ የታወቀው አውሳብዮስ ቅዱስ ማትያስ ከ72ቱ አርድዕት ወገን እንደነበረ ጽፏል ። አውሳብዮስ 1 : 13 ማትያስ ለሐዋርያነት እንዲመረጥና ዮስጦስ በርስያ ከተባለው ከዮሴፍ ጋር ዕጣ እንዲጣጣል ሐሳብ ያቀረበው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስካረገበት ቀን ድረስ ከሐዋርያት መካከል ሆኖ በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ማትያስ ከሐዋርያት ጋር ነበር ። ሐዋ 1 : 21 - 22 በገድለ ሐዋርያት እንደተጻፈ ቅዱስ ማትያስ ይሰብክ ዘንድ ዕጣ የደረሰው " በላዕተ ሰብእ " የሚባሉ ሰዎች ወደሚኖሩበት ሀገር ነው ። የይህ ሀገር በእስኩቴስ ( ሩሲያ ) ሳይሆን አይቀርም ፤ አውሳብዮስ በቤተ ክርስቲየን ታሪክ መጽሐፉ ይህ ቦታ በጥንቱ ዓለም አጠራር በርባሮስ ይባል እንደ ነበረ ሲጽፍ ዜና አይሁድን የጻፈው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ደግሞ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ጨካኞችና ከአራዊት ያልተሻሉ አረመኔዎች እንደነበሩ ጽፏል ። ቅዱስ ማትያስ እዚያ ደርሶ ሲያስተምር እነዚህ ሰዎች ይዘው ዓይኑን አውጥተው በእስር ቤት እንደ እንሰሳ ሣር ያበሉት ጀመር ምክንያቱም የዚያ ሀገር ሰዎች ሰውን ከመብላታቸው በፊት ዓይኑን አጥፍተው ለ40 ቀናት ያህል ሣር ማብላት ልማዳቸው ስለ ነበር ነው ። ሐዋርያው ማትያስ ለ40 ቀናት ያቀረቡለትን ሣር ሳይበላ ጊዜውን በጾምና በጸሎት አሳለፈ ፣ በ40ኛው ቀን ሣሩን ከፊቱ ከምሮ ሲዘምር እንድርያስ በተዘጋ በር ገብቶ " እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኃለሁ " የሚለው የጌታ ቃል ዛሬ በአንተ ተፈጸመ ብሎ በደስታና በናፍቆት ሰላምታ ሰጥቶት ይዞት ከሥር ቤት ወጣ አብረው ከእርሱ ጋር ታስረው የነበሩ 123 ሰዎችም አብረው ወጡ ፤ ይህንን ተዓምር ያዩት የሀገሪቱ ሰዎች በትምህርቱ አምነው ተጠመቁ ፣ ለእነዚህም ሰዎች መጽሐፍ ጽፎ እንደሰጣቸው ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ መስክሯል ። ከዚህ በኃላ ሐዋርያው ማትያስ ደማስቆ ገብቶ ወንጌል ሲሰብክ በአይሁድና በአረማውያን ቅስቀሳ ተቃዋሚዋች ተነስተው በብረት አልጋ ላይ በማስተኛት ከሥሩ ለሰባት ቀናት ያህል እሳት ለቀቁበት በሰባተኛው ቀን ሲመለሱ አንዳች ጉዳት ሳይደርስበት በማግኘታቸው በትምህርቱ አምነው ተጠምቀዋል ። በመጨረሻም በሀገረ ይሁዳ ሲያስተምር ከኖረ በኃላ ፊላዎን በተባለች ቦታ ሸምግሎ እድሜ ጠግቦ አርፏል ጸሎትና በረከቱ በሁላችን ላይ ይደር አሜን ። ❖ ወዳጄ የዚህ ዘመን ሰማዕትስ ማነው ? " ሃይማኖቱን የጠበቀ ፣ ራሱን የገዛ ሰው የዚህ ዘመን ሰማዕት እርሱ ነው ። " የኤልያስ መንፈስ በኤልሳ ላይ እጥፍ ድርብ ሆኖ እንዳደረ ፣ የእነዚህ የቅዱሳን ሐዋርያት ጣዕማቸውና ፍቅራቸው ፣ ረድኤትና በረከታቸው ፣ ጸጋቸውና ክብራቸው በሁላችን ላይ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደር ። እንደነሱ በመልካም ሥራ ተጋድለን ፣ ሃይማኖታችን ተዋሕዶን ጠብቀን የማያልፈውን ዘላለማዊውን ክብር ለመቀናጀት ያብቃን አሜን ። ያለሱ ሌላ አምላክ ለሌለ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ። ሰውን ወዳጅ የምህረት አማላጅ ቅዱስ ሚካኤል አይለየን ።

✞ ሚካኤል ዘየካ ✞

Feb 17, 2016 · Public · in Timeline PhotosView Full Size

Report Page