*/

*/

Source

“ከሕይቅ ወደ ምድር ከምድር ወደ ሐይቅ”

ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) የዚህችስ ልዩ ነው፣ መኖሪዋ ሐይቅ ነው። እንደዚህም ይከበራል። እንደዚህም ይዘመራል። እንደዚህም ይገለገላል ለካስ። ከአየናቸው ያላያናቸው፣ ከሰማናቸው ያልሰመናቸው፣ ከአወቅናቸው ያላወቅናቸው ይበልጣሉ።

በየብስ የሚኖሩ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባሕር ሲወርዱ፣ እርሷ ደግሞ ከሐይቅ ወደ የብስ ትወጣች። በዚያች ቅድስት ሥፍራ ዓይኔ መልካም ነገረን አየች። ልቤ ተመሰጠች፣ ነብሴ ሀሴትን አደረገች።

ኢትዮጵያ የማትመረመር መሶበወርቅ፣ የማትዝግ ወርቅ፣ ከክብርም በላይ የሆነች ጌጥ፣ ቃል ኪዳን የሆነች የልብ ፈርጥ ናት፣ ፈጣሪ ያከበራት፣ በፈቃዱ የፈጠራት፣ በፈቃዱ ያኖራት፣ በፈቃዱ የሚያኖራት፣ ለምስክር ያዘጋጃት ናት።

እኔስ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ተመስገን አልኩ። በተመረጠችው ምድር ተፈጥሬያለሁና። ጥሩንባው ተነፋ፣ ቀሳውስት ዘመሩ፣ ምዕመናን እልል አሉ፣ በዚያች ደብር የተገኙ ሁሉ ደስታ በደስታ ሆኑ። ረጃጅም ዛፎቹ ሳይቀር በማዕበል እየተገፉ ሲወዛወዙ ምስጋና የሚያቀርቡ ይመስላሉ።

ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። በተቀደሰው የጣና ሐይቅ ውስጥ ካሉ ገዳማትና አድባራት መካከል ቀዳሚዋ ናት ይሏታል። ይህች ቤተክርስቲያን በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት እንደተሰራች ይነገራል። በተቀደሰችው ሥፍራ የተቀደሰችውን ደብር የደበሩ፣ የእግዚአብሔርን ማደሪያ የሠሩ አቡነ ታዲዮስ ናቸው።

ሕንፃ ቤተክርስቲያኗ ከቅድስቲቱ ሀገር ኢየሩሳሌም በመንፈስ ቅዱስ ከመጣ ድንጋይና አፈር እንደተሠራች ይነገራል። ቤተክርስቲያኗ በመንፈስ ቅዱስ የተሠራች እፁብ ናት።

በዚች ጥንታዊት ቤተክርስቲያን አያሌ ሚስጥራት ይገኛሉ። ጥንታዊ የብራና መጽሐፍትና ቅዱሳን ቅርሶች ይገኙባታል።

ደብረ ማርያም ከጣና ገዳማት ውስጥ ለባሕርዳር ቅርቧ ናት። ግን በውል የሚያውቃት ጥቂቱ ነው። የበዓለ ጥምቀት ደብረ ማርያምን ማዬት ከደስታም ደስታ ከሀሴትም ሀሴት ነው።

ልባቸው ንጹሕ የሆኑ ሕፃናት፣ ንጹሕ በሆነው ሐይቅ፣ ንጽሕት ወደሆነችው እናታቸው እየቀረቡ “ማርያም ሆይ እንወድሻለን” ይሏታል።

የታንኳው ሽርሽር፣ የሕጻናት ፍቅር፣ ለእናታቸው ለማርያም፣ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር የሚገርም ነው።

ማገልገል ከልብ ሲሆን ስሜቱ ልዩ ነው። ፍቅራቸውን ለመግለፅ ሲሉ ከታንኳ ወርደው በሐይቁ እየዋኙ ምስጋና ያቀርባሉ። ዘመናዊ ጀልባዎች ታቦተ ማርያምን እየዞሩ ያጅባሉ። በጀልባውና በታንኳው ያሉ ምዕምናን እልል እያሉ፣ እያጨበጨቡ፣ በልባቸው እያደነቁ ታቦቷን ያጅባሉ።

የማርያም ታቦት ከመንበሯ ወጥታ ሐይቅ እስክትገባ፣ ከሐይቅ ወጥታ እስከ ማደሪያዋ ድንኳን እስክትደርስ ድረስ በየብስ ላይ ስትጓዝ ለአገልግሎት በሚፋጠኑ ወጣቶች ስጋጃ እያነጠፉ በክብር እንድታልፍ ያደርጓታል።

ያከበራቸውን ያከብሩታል፣ የጠበቃቸውን ይጠብቁታል፣ ዝቅ ብለው ሰግደው ከፍ ብለው ይከብራሉ። “አይተዋትም አይተዋትም ሀገራችን ኢትዮጵያን” እያሉ ይዘምራሉ። አዎን እውነት ነው። ለመልካሞቹና ለደጎቹ ሲል ኢትዮጵያን አይተዋትም፤ አይረሳትም፤ ይጠብቃታል እንጂ።

ያን ያዩ ሁሉ ደስታን ገብይተዋል። መንፈሳቸውን አርክተዋል። አንቺ ምድር ምንኛ የታደልሽ ነሽ ማለታቸው አይቀርም። ከታደሉት የታደለች፣ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ከተቀደሱት የተቀደሰች ውብ ሀገር - ኢትዮጵያ።

የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የቅዱሳን ሀገር፣ የታሪክ ማህደር፣ የኃያልነት መንበር፣ የስልጣኔ መውጫ የምስራቅ በር ናት። ኢትዮጵያ ታይታ አትጠገብም፣ በቀላል አትመረምርም፣ በጠላት አትሸነፍም፣ ለምስጋና አታርፍም፣ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ አታጥፍም። በንጽሕና እየለመነች፣ በቅድስና እየተቀበለች፣ ቃል ኪዳኗን እያከበረች ትኖራለች እንጂ።

ደብረ ማርያምን የተመለከተ ሁሉ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የነበረውን ሁሉ ያዬ ይመስለዋል።

ቀደም ባለው ጊዜ ደብረ ማርያም በጥምቀት ስትነግሥ ታንኳ ብቻ ያጅባት እንደነበር ሰምቻለሁ። አሁን ግን ዘመናዊ ጀልባም አጃቢ ሆኗል። “ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት ለአንድ ቀን ነው ብሎ ዘላለም ሄደበት” እንደተባለው ፈጣሪ ውኃን በውኃ ላይ አሳልፎ በሰደደበት ታዕምራዊ ቦታ አጠገብ የምትገኝ ውብና ድንቅ ደብር ናት። የፈጣሪን ልዩ ጥበብ ያዩባታል። ውኃ በውኃ ላይ አልፎ የሚሄድበት ሀገር ከዚያ ውጭ ሌላ ያለ አይመስለኝም።

በጣና ገዳማት ሰባቱ ከዋክብት ከሚባሉት አንደኛዋ ናት ደብረ ማርያም። ደብረ ማርያም ጥምቀቷ ልዩ ነው፣ አከባበሯ እፁብ ነው፣ ምስጋናዋ ድንቅ ነው።

ታዲያ በመልካም ሀገር ተወልደን፣ መልካም ታሪክ ይዘን፣ ለማወቅ ዘግይተናል። ደብረ ማርያምን የሚያውቃት ጥቂቱ እንደሆነ ሰምቻለሁ። በበዓለ ጥምቀት በቅርቡ ያለው የባሕርዳር ሕዝብ እንኳን በደንብ እንደማያውቃት ነው የሰማሁ። ይህ ሕብስት ቀርቦ አልበላም እንደማለት፣ ዓይን መልካሙን እይ ሲባል አላይም እንፈማለት ይቆጠራል። ደስታም፣ ሀሴትም፣ ፍቅርም፣ ክብርም፣ ተድላም፣ ታሪክም ያለው ከዚያ ውስጥ ነው። ይይዋት ይረኩባታል። የመንፈስም ስንቅ ይገበዩባታል።

በሐይቅ ተከባ የምትኖረው ደብረ ማርያም በበዓለ ጥምቀት ከማደሪያዋ ወጥታ ሐይቁን እየባረከች ወደ የብስ ትሄዳለች። በዚያው አድራ ሐይቁን እየባረከች ወደ መንበሯ ትመለሳለች። እኔ በታንኳው ሽርሽር፣ በሰው ፍቅር፣ በእግዚአብሔር ክብር ተደምሚያለሁ፣ ረክቻለሁም፣ እናንተስ? እንኳን አደረሳችሁ።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Report Page