*/

*/

Source

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
-----------------------------------------------------------------------
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 94ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ በአፈጻጸም ያጋጠሙ ስህተቶችን ማረም ተገቢ በመሆኑ፣ እንዲሁም አሁን ዘርፉ ከደረሰበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊነቱ ስለታመነበት የህጉን ክፍተቶች በጥናት በመለየትና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመፈተሽ የማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ተብሏል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ መክሮ ግብአቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

በኢትዮጵያ እና በኡጋንዳ መካከል በተደረጉ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነቶችን ለማጽደቅ በቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይም ተወያይቷል፡፡

በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነቱ በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር በመሆኑ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነም ምክር ቤቱ አስታውቋል።

በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነቱ ደግሞ በተደራጁና ድንበር ዘለል ወንጀሎች እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ግዛት ውስጥ በሚፈጸሙ ሌሎች ወንጀሎች ምርመራ፣ የክስና የፍርድ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ መረጃና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲሁም የወንጀል ፍሬዎችን ከመያዝና ከማገድ ጀምሮ የሚወረሱበትን ሂደት የሚያግዝ የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረቡት የስምምነት ሰነዶችና የማጸደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወያየ በኋላ ይጸድቁ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል፡፡

ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል የተፈረመው የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን የማስቀረት ስምምነት ማጸደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይም መክሯል፡፡

ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ቪዛና መሰል ስርዓቶችን ለማሟላት የሚባክነውን ጊዜ የሚያስቀር ነው ብሏል፡፡

በስምምነት ሰነዱ እና ማጸደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

እንዲሁም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ለሚሰጡ አገልግሎቶች የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያን ለመወሰን በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ ቦርዱ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በመንግስት በሚወሰን ተመን መሠረት ክፍያዎችን እንደሚያስከፍል መደንገጉን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ቦርዱ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያወጣውን ወጪ ከተገልጋዩ በሚሰበስበው ክፍያ ለመሸፈን የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ የአገልግሎት ክፍያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ቀርቦ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ ተወይይቶ ውሳኔ ያሳለፈበት ጉዳይ የኢትዮ-ቴሌኮም ማቋቋሚያ ደንብን ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ነው፡፡

ከኢንዱስትሪው ፈጣን ዕድገትና ተለዋዋጭ ባህሪይ ጋር አብሮ መሄድ እንዲችል፣ በሚዘረጉ የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ተጨማሪ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ እና ኩባንያው በመደበኛነት እየሰጠ ከሚገኘው ከተለመደው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር ተዛማጅነት ባላቸው የአገልግሎት መስኮች እንዲሰማራ መፍቀድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም የኢትዮ ቴሌኮም ማቋቋሚያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር ለአምስተኛው ምእራፍ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እንዲውል የተፈረመውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡

ከ2013 እስከ 2017 ድረስ ለሚተገበር የልማታዊ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ200 ሚሊየን ዶላር ከወለድ ነጻ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በብድር ስምምነቱ ላይ ተወያይቶ ከሀገሪቱ የብድር ስትራቴጂ ጋር የሚሄድ፣ ወለድ የማይከፈልበት፣ የ6 ዓመት እፎይታ ያለው እንዲሁም በ38 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የብድር አይነት በመሆኑ ይጸድቅ ዘንድ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል፡፡

Report Page