ጌታ እኮ ነው

ጌታ እኮ ነው

Solicious18 Wallpapers™

ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ በታምር መያዛቸው

1ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር21፥1 የገሊላ ባሕር ማለት ነው

 እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ 2ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ 3ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም።

4ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር።

5እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው።

እነርሱም፣ “የለንም” አሉት።

6እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው።

7ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘ጌታ እኮ ነው!’ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘሎ ወደ ባሕሩ ገባ። 8ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል21፥8 ዘጠና ሜትር ያህል ነው

 ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። 9ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ።

10ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው።

11ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። 12ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። 13ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤

ዓሣውንም ሰጣቸው። 14እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።

ኢየሱስ ጴጥሮስን ወደ ቀድሞ ቦታው መለሰው

15በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወደኛለህን?” አለው።

እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።

16ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወደኛለህን?” አለው።

እርሱም፣ “አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው።

17ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወደኛለህን?” አለው።

ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ ‘ትወደኛለህን?’ ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው።

ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። 18እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” 19ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።

20ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ ራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። 21ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ።

22ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው። 23በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም።

24ስለ እነዚህ የሚመሰክረውና ይህን የጻፈው ይኸው ደቀ መዝሙር ነው፤ ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።

25ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።


Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum)

Copyright © 2001 by Biblica, Inc.®

Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.

 

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.®

ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።

Learn More


Report Page